ወታደራዊ የደርግ መንግሥት ተወግዶ ኢሕአዲግ መንበር ሥልጣኑን ከተቆናጠጠ ብዙም ሳይቆይ በክፍለ ሀገር ተዋቅራ የነበረችው ኢትዮጵያ በአዲስ የክልል አመሰራረት ተከፋፈለች:: አዲሱን ሀገራዊ መዋቅር ተከትሎም የየክልሉ መሪዎች መንግሥታቸውን የሚያዋቅሩበት ወቅት ነበር – ከ1985 እስከ 1986 ዓ.ም::
በሀገሪቱ በአዲስ ከተሰየሙት ክልሎች መካከል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት / ክልል ሦስት/ አንዱ ነው:: የክልሉ መሪዎችም ክልላቸውን ካዋቀሩ በኋላ ሥራቸውን ለማሳለጥ ከሕዝብ ጋር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኛቸው ዘዴ እንደሚያስፈልጋቸው ተስማሙ፤ ምርጫቸውም ጋዜጣ ሆነ::
ይህን ተከትሎም በግዕዝ ቋንቃ የመጀመሪያ፣ ቀዳሚ የሚል ትርጉም የያዘችው በኵር ጋዜጣ ተመሰረተች:: ሀምሌ 9 ቀን 1986 ዓ.ም ጀምሮ በወር እና በሁለት ወር በልዩ ዕትም መዘጋጀት ጀመረች:: በ1987 ዓ.ም ደግሞ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ከኢትዩጵያ ቴሌቪዥን፣ ከኢትዮጵያ ኘረስ ድርጅትና ከሌሎች ተቋማት በተሰባሰቡ ባለሙያዎች በክልሎች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነችው በኵር ጋዜጣ ልክ የዛሬ 30 ዓመት ታህሳስ 7/1987 ዓ.ም ታትማ ለስርዕት በቃች:: በስድስት አምዶች እና በስምንት ገጾች – የፊት ገጽ ዜና፣ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ የአንባቢዎችን አስተያየት፤ እና የዞን ዜና በማካተት ለአንባብያን ተሰራጨች:: በወቅቱም በየሳምንቱ አራት ሺህ ቅጅ ስርጭት ነበራት::
ጋዜጣዋ በ30 ዓመት ጉዞዋ በይዘት፣ በቅርጽ፣ በገጽ እና በአምድ ብዛት… ሳምንታዊ ስርጭቷን ሳታቆራርጥ ዛሬ ላይ ደርሳለች:: በውስጥ ገጾቿ የሚስተናገዱ አምዶች በየጊዜው የሥያሜ ለውጥ፣ አንዳንዴ በሌላ የመተካት እና በነበረው የመዝለቅ ሁኔታም ነበር:: ከነዚህም መካከል የመልካም አስተዳደር መልካም ተሞክሮዎች እና የፍትሕ ጉዳይ የሚቀርብበት የፍትሕ እና መልካም አስተዳደር አምድ አንዱ ነው::
እኛም ልክ የዛሬ 30 ዓመት ታትማ ወደ አንባብያን ዘንድ የደረሰችው በኵር ጋዜጣ በፍትሕ እና መልካም አስተዳደር ጉዳይ ምን ምን ጉዳዮችን አነሳች? ለክልሉ ብሎም ለሀገራችን ምን አስተዋፅኦ አበረከተች? የሚሉትን ለማስታወስ ከ1987 እስከ 2017 ባሉት ሦስት አስር ዓመታት የታተሙትን ለትውስታ አለፍ አለፍ በማለት የአምዱን ይዘቶች ተመለከትን::
በኵር ጋዜጣ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የፊት ገጽ ዜናን ጨምራ በውስጧ ትኩረት፣ ማህበራዊ፤ አውደ ባህል፣ ከልማት ዙሪያ እና ስፖርት አምዶች ነበሯት:: ጋዜጣዋ የፍትሕና መልካም አስተዳደር አምድን ባታካትትም በየአምዶች የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በስፋት ተዘግቧል::
ለአብነት በኵር በየካቲት አንድ 1987 ዓ.ም ከፊት ገጽ ዜናዎቿ ከሦስቱ አምስቱ የፍትሕና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ናቸው:: ለአብነት “ደብረታቦር ከውኃ ጥሟ ልትረካ ነው፣ ከማረሚያ ቤት ለማምለጥ የሞከሩ ተገደሉ፣ ጽላቶችንና ንዋዬ ቅድሳትን የዘረፉ ተፈረደባቸው፣ ባለትዳሯ አሊቤርጐ ውስጥ ተገድላ ተገኘች፣ ቀለበት አልባው ቦምብ ሕይወት አጠፋ” የሚሉት ይገኙበታል:: በተደራሽነት በኩልም ዋግህምራ፣ አዊ፣ ባሕር ዳር፣ ጐንደር… የዞን ስብጥራቸው ተጠብቆ ሽፋን አግኝተዋል:: የፍትሕና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችንም በውስጥ አምዶቿም በስፋት ተዳሷል::
በክልሎች ታሪክ የመጀመሪያዋ በኵር ጋዜጣ ከ10 ዓመታት ጉዞ በኋላ ቅርጿን ቀይራ፣ የውስጥ አምዷን አስፋፍታ … ብቅ ብላለች:: ለዚህ ማሳያም በውስጥ አምዶቿ ከጨመረቻቸው መካከል “አስኳል” የተሸፈነው አንዱ ነው:: በኵር በመስከረም 1997 ዓ.ም እትሟ በአስኳል አምዷ በአብዛኛው የሽፈነችው የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር እና ፍትሕ ጉዳይ ነበር፤ ከእነዚህም ውስጥ “የጃን ተከል ዋርካ ውዝግብ” በሚል ርእስ የዋርካውን ሥር ተከራይታ የነበረች ግለሰብ የውል ጊዜዋን ሳትጨርስ ያለአግባብ እንድትለቅ መጠየቋን አስመልክቶ የተሠራ ዘገባ አንዱ ነው::
በየጊዜው የቅርጽ እና የይዘት ማሻሻያ እያደረገች እና አምዷን እያሰፋች ለአንባቢዎቿ በየሳምንቱ የምትደርሰው በኵር ጋዜጣ የዛሬ 20 ዓመት /1997/ ዓ.ም የመልካም አስተዳደር ተሞክሮዎችን ማጋራት፣ ወንጀል ፈጻሚዎች እነርሱም ሆኑ ሌሎች ከድርጊቱ እንዲርቁ በማጋለጥ፣ “በሕግ አላውቅም ማለት ከተጠያቂነት አያድንም” እንደሚባለው ኀብረተሰቡ የሕግ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስተማር የፍትሕና መልካም አስተዳደር ገጽ ከፍታለች፤ በገጹም የፍትሕ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በየሳምንቱ እየተፈራረቁ ይስተናገዱበት ነበር:: በአራተኛዋ ኮለመን ደግሞ ወንጀል ነክ ዜናዎች በቋሚነት ይካተታሉ::
ጋዜጣዎ የፍትሕና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመዳሰስ ከተከፈተበት አምድ ባለፈ በሰዎች ምን ይላሉ? በወጣቶች፣ በሴቶች /ሔዋን/፣ በዜናና በሌሎችም አምዶች በኵር ለተበደሉት ፍትሕ ስታፈላልግ እና መልካም ተግባራትን ከአንዱ ለሌላው ስታካፍል ቆይታለች::
ለአብነት በየትኛውም አቅጣጫ የገና በዓልን ለማክበር ወደ ላልይበላ ለሚሄዱ ምዕመናን የከተማዋ ወጣቶች በአንድ አይነት ልብስ ተውበው የሚሰጡት መስተንግዶ ከተዘገቡት አንዱ ነው:: ዘገባው እንደሚያመላክተው ወጣቶቹ ከረዢም እግር ጉዞ በኋላ ላልይበላ አቧራ ለብሰው፣ በላብ ተጠምቀው እና ድካም አዝለፍልፏቸው ለሚደርሱ ምዕመናንን ባዘጋጁት ቦታ በማስቀመጥ ያለምንም መሳቀቅና መጠየፍ እግራቸውን ተረባርበው ያጥባሉ:: አንድም መንገደኛ እግሩን ሳይታጠብ፣ የተዘጋጀውን እህል ውኃ ሳይቀምስ ወደ በዓሉ ቦታ አይሄድም::
የወጣቶችን በጎ ተግባርም ምዕመናኑ ሲመሰክሩ፤ “በሥራቸው እጅግ ልቤ ተነክቷል:: በመጀመሪያ ‘ይምጡ ወደዚህ!? ይቀመጡ!…’ እያሉ ሲንከባከቡኝ እነዚህ የከተማ ልጆች አታለው ስንቄን ሊቀሙኝ ነው በሚል ስጋት ላይ ወድቄ ነበር:: በኋላ ግን ሁሉንም መንገደኛ ከነአቧራው እና ጭቃው በክብር አስቀምጠው እግር ሲያጥቡ ሳይ ተገረምሁ! እጃቸውን የጤፍ እንጀራ ጠርዝ የሚቆርጣቸው የሚመስሉ ወጣቶች የኛን የገበሬዎችን የሻከረ እግር ተሻምተው ማጠባቸው እና ለርሀባችን ማስታገሻ ማቅረባቸው ሁሉን አስረስቶ እንኳን መጣሁ! አሰኝቶኛል! ከጐንደር አካባቢ በቡግና አድርገን ከሣምንት የእግር ጉዞ በኋላ ስንደርስ የነበረው ድካም ሁሉ ጥሎን ጠፍቷል” በማለት ነበር:: በዚህ ዘገባ ሌላ ስፍራ ያሉ ወጣቶች መከባበርን፣ ኢትዮጵያዊ እንግዳ አቀባበልን…እንዲማሩበት እድል ይሰጣል::
ሌላው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ሕዝብን እና መሪን ፊት ለፊት አገናኝቶ በሚያወያየው መድረክ በኵር በፍትሕ ዓምዷ ፊት ለፊት የሚል ርዕስ በመስጠት የሚነሱ ጥያቄዎችን እና የሚሰጡ ምላሾችን ቃል በቃል ዘግባለች:: ከወራት በኋላም ነዋሪው ላነሳቸው ጥያቄዎች አመራሩ ምን ምላሽ ሰጠ? በማለት በኵር በፍትሕና መልካም አስተዳደር ገጿ በስፋት ሽፋን ሰጥታለች፤ ችግሮች እንዲፈቱ ተከታታይ ዘገባዎችን ለአንባቢያን አቅርባለች::
ለአብነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ አስተዳደር አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባዘጋጀው የከተሞች መድረክ በኗሪዎች ዘንድ ሰነድ አልባ የመሬት ይዞታ በሥፋት የመልካም አሥተዳደር ችግር መንስኤ ሆኖ ቀርቦ ነበር:: በውይይቱ ከተሣተፉት ኗሪዎች መካከል አቶ እውነቱ ዘለቀ አንዱ ናቸው:: “አዎ ሰነድ አልባ ብዙ ተሠርቷል! ነገር ግን ዘመድ ያለው፤ ሳንቲም ያለው ነው የተሠራለት! ሳንቲም የሌለው፣ ዘመድ የሌለው ሰው ግን አላለቀለትም!” በማለት ሰነድ አልባ የይዞታ ቦታዎች ማረጋገጫ አሠጣጥ ሕጋው መንገድን ሳይሆን ዘመድ እና ገንዘብ ላለው ብቻ እንደሚሰጥ ቅሬታቸውን በድፍረት ተናግረው ነበር::
ወ/ሮ እታፈራሁ ምናሉ በበኩላቸው ትክ ቦታ ለማግኘት ወይም ደግሞ የነበራቸውን ቤት አፍርሰው እዚያው ላይ ለማደሥ ለሞጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ “እንኳን ልትሠሪ ድንጋይ እንኳ መጫን አትችይም! ይሄ ሀብታም የሚሠራበት ቦታ ነው” በመባላቸው የደረሰባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር አንስተው ነበር::
በወቅቱም የሞጣ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ሙኔ ለተነሡ ጥያቄዎች ነበር:: ሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን በማጣራት የባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ለመሥጠት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረው ነበር:: ነገር ግን ጉዳዩ በጣም ውሥብሥብ ነው፤ “300 ካሬ ሜትር ላይ የነበረው ባለይዞታ አሥፋፍቶ በመያዝ ‘500 እና 400 ካሬ ሜትር ነው ያለኝ፤ ትክ 500 ካሬ ሜትር ሊሠጠኝ ይገባል‘ የሚሉ ግለሠቦች መኖራቸው ችግሩን አባብሶታል:: ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ካርኒ የተቆረጠባቸው ይዞታዎች አሉ:: መረጃዎችን ሰብስበን ይዘናል:: እነሡን አቆይተናቸዋል” በማለት በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ባያገኙም ጅምር ሥራ መኖሩን በኵር ድጋሜ በቦታው በመገኘት ሕዝባዊ ወገንተኝነቷን ማረጋገጥ ችላለች::
በቡሬ ከተማ አስተዳደርም የከተማዋን ነዋሪዎች እና የአመራር አካላት ፊት ለፊት ባገናኘው መድረክ ከተነሱ ችግሮች የትኞቹ ተፈቱ? የትኞቹስ አልተፈቱም? ለምን?… “ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን ነበር:: አመራሮች ከሰጡት ምላሽ እንዲሁም በተደረገ ምልከታ የተወሰኑት ምላሽ አግኝተዋል:: ከእነዚህም አንዱ የኤሌክትሪክ ኀይል ማነስ ነበር:: ጥያቄውን ያነሳችው ነዋሪ የበኵርን ጨምሮ በቦታው የተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን ጥያቄዋ ምን ምላሽ እንዳገኘ ተጠያቃ “መጋቢት ወር ላይ ትራንስፎርመር (የኀይል ማስተላለፊያ) መጥቶልናል:: ስለሆነም ዛሬ የተስተካከለ ኀይል እያገኘን ነው” በማለት ተናግራለች:: ይህም አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት/በኵር/ ለበርካታ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መፍትሔ እንዳስገኘች ጠቋሚ ነው::
በኵር በሰሜኑ ጦርነት በሰው ሕይዎት እና በንብረት ላይ…የደረሰውን ችግር በቦታው ዘጋቢዎችን በመላክ ከፍትሕና መልካም አስተዳደር አምዷ ተጨማሪ “ህልውና” የተሰኘ አምድ በመክፈት፣ በሄዋን፣ በትንታኔ፣ በወጣቶች እና በውስጥ ዜና አምዶቿ የዜጎችን ሰቆቃ አስነብባለች፤ ምሁራንን በማነጋገርም መፍትሔ አመላክታለች:: ለአብነት የመልካም አስተዳደር ችግሩን በሔዋን አምድ “ከማይካድራ እናቶች አንደበት” በሚል ርዕስ አስነብባለች::
የዕድሜ ባለፀጋዋ የደረሰባቸውን በደልም ቀንጨብ አድርገን እናስታውሳችሁ፤ ጊዜው ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ነው:: ባለታሪካችን “አማራዎች በብሔራቸው ብቻ እየተለዩ ሲጨፈጨፉ አድረዋል፤ ሳምሪ የተሰኘው ገዳይ ቡድን ታዲያ ገጀራ በመያዝ በየቤቱ እየገባ ንፁሃንን ያርዳል። ቀሪው ደግሞ በገጀራ ከመቀላት በተአምር ተርፎ ሊወጣ ሲሉ በጥይት እሩምታ ይገደላል” በማለት ድርጊቱን ከዐይናቸው እንባ እንደ ጎርፍ እየወረደ ነበር ያጫወቱን:: ይሁንና በፍጥነት ከዚያ የሐዘን ስሜት በመውጣት “እነዚህን አጥፊወች ለመፋረድ ምንም የምንሰስተው ነገር የለም! እንኳን ገንዘባችንን ለሕይዎታችን አንሳሳም!” ሲሉ አጥፊወችን ለፍርድ ለማቅረብና ፍትሕን ለማግኘት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋ::
በጥቅሉ በኵር ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሕዝቡ የሕግ ግንዛቤውን እንዲያዳብር፣ በደሉን ፊት ለፊት እንዲናገር…አስተዋጾ አበርክታለች:: አሁን ላይም በኵር በፍትሕ እና መልካም አስተዳደር አምዷ የፍትሕ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን እያፈራረቀች ለንባብ ታበቃለች:: በአንድ ኮለመን ደግሞ ለዘገባው አጋዥ የሆነ የሕግ እንቀጽ እንዲሁም ወንጀል ነክ ጥቆማዎች እና መልካም ተሞክሮዎች ይስተናገዱበታል።
ባሁኑ ወቅትም በኵር በክልሉ በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያትም ግጭቱ በክልሉ እያስከተለ ስላለው ዘርፈ ብዙ ቀውስ እና መደረግ ስለሚገባው ተግባር፣ ስለ የሕግ የበላይነት እና በሕግ አንቀጾች ዙሪያም አንባቢው መረጃ እንዲያገጘ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳች ዙሪያ መረጃወችን በማቅረብና የሕግ ባለሙያወችን በመጋበዝ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለህብረተሰቡ በሕግና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች። ምንም እንካ በሰላሙ መደፍረስ ምክንያት እንደበፊቱ ተደራሽነት ላይ የውስንነት ችግር ያጋጠመ ቢሆንም እኛም መጭው ጊዜ ሰላም እንዲሆን ተመኘን!
( ሙሉ ዓብይ)
በኲር የታኅሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም