በኩር ማሕበራዊ

0
202

በክልሎች ታሪክ የመጀመሪያዋ በኵር ጋዜጣ በ30 ዓመት ታሪኳ የማህበራዊ ጉዳዮችን ስትተነትን ቆይታለች:: 1987 ታህሳስ ሰባት ቀን  ለህትመት የበቃችው በኵር ጋዜጣ በማሕበራዊ ዓምዷ ማህበራዊ ችግሮችን በማንሳት   ለአንባብያን ተደራሽ ሆናለች:: ለአብነት በየካቲት ወር 1987 ዓ.ም ጋዜጣዋ የጣናነሽ መርከብን ችግር ጋዜጠኛው መንገደኞችን፣ ሠራተኞችን እና ኃላፊዎችን አነጋግረሮ እንዲሁም የራሱን ምልከታ አካቶ ዘግቧል:: በሳምንቱ በወጣው ዘገባ ደግሞ በድሮው ሥያሜ የጣና ኃይቅ ትራንስፓርት ድርጅት  ስለጣናነሽ ሰፊ አገልግሎት፣ ችግሩን ሊፈቱ የሚችሉ ባለሙያዎች ስለመኖራቸው እንዲሁም     በተነሳበት ችግር ዙሪያ ምላሻቸውን የሰጡበት ሙሉ ጽሑፍ ነበር የተስተናገደው:: በኩር በማህበራዊ ዓምድ የሴቶች፣ የጤና፣ የወጣቶች፣ ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን የተመከለቱ ዘገባዎችም  በየሳምንቱ ተስተናግደውባታል::

ጤና

በኵር  በጤና አምዷ የኤች አይ ቪ ስርጭት እንዲገታ፣ ስለ ወባ በሽታ፣ ስለ ካንሰር ፣አተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት) እንዲሁም ሌሎች በርካታ የጤና እክል የሚያመጡ ልዩ ልዩ በሽታወችና በቅርቡ ስለተከሰተዉ  የኮሮና  በሽታ ከቅድመ ጥንቃቄ  እስከ መፍትሔው    ተከታታይ ሽፋን ሰጥታለች፤ አሁንም እየሰጠች ነው::

በኩር በ1987 ዓ.ም እትሟ  በጤናው ዘርፍ ወባ በወረርሽኝ ደረጃ በመከሰቱ ስለ በሽታው ምንነት እና ያስከተለውን ስጋት በተመለከተ የክልሉን ጤና ቢሮ ሪፖርት በማካተት ይዛው የወጣችው ዘገባ አንዱ ነው:: በዚህ ዘገባም የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ሰዎች አጎበር እንዲጠቀሙ በተካታታይ ዛሬም ድረስ እየሠራች ትገኛለች:: በኤች አይቪ ዙሪያም የሕዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ ምርመራ እንዲያደርግ፣ ማግለል እና መድሎ እንዲቀር እንዲሁም   ቫይረሱ የተገኘባቸው ግለሰቦችን ምስክርነት    መሰረት አድርጋ አስተማሪ ዘገባዎች ሠርታለች::

ስለሥነ – ሕዝብ ዘላቂ ልማት፣  ጤና አጠባበቅ ትምህርት፣ የሕፃናት ጉዳቶች፣  በክልሉ ያሉ የጤና ተቋማት ግንባታ እና ችግሮች፣ አሠራሮች  እንዲሁም  በጤና አጠባበቅ ዙሪያ ያሉ የግለሰብ መልካም ተሞክሮዎች፣ የግብዓት እና መድኃኒት አቅርቦት በተመለከተም በኵር በዝርዝር አስነብባለች::

ማህበረሰቡ በጤና ዙሪያ ሊያደርግ ስለሚገባው ጥንቃቄ የአተት፣ የወባ፣ የኮሮና… በሽታ በተከሰተበት ወቅት የሚመለታቸውን ባለሙያዎች በማነጋገር እንዲሁም  ተያያዥ የውጭ ዘገባዎችን በመተርጎም ህብረተሰቡ በጤናዉ ዘርፍ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ   መረጃ  በማቅረብ እያስነበበች ቆይታለች::

ሴቶች

በጋዜጣዋ ጅማሬ በማህበራዊ አምድ ሥር  የሴቶች ጉዳይ ተዘግቧል:: ለአብነት በልማቱ መስክ የሴቶች ተሳትፎ ማነስ፣ በትምህርት ተጠቃሚ ካለመሆን  ጋር ያለውን ተጽኖ  እና በፆታዊ የሥራ ክፍፍል ምክንያት እየደረሰ ያለውን ችግር ከመጋቢት 29 ቀን 1987  እትም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ዓመታት በኵር ዘግባለች::

ከ1997 ዓ.ም ደግሞ የገጹ ስያሜ ወደ ሔዋን ተለወጠ:: አምዱ የሴቶችን እኩል መብት የማግኘት ጥያቄን፣ ለለውጥ ያደረጉትን ጉዞ ከግለሰብ ጀምሮ ያሉ ምርጥ  ተሞክሮዎችን  እና ችግሮቻቸውን ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በማቅረብ የሚሰጡ ምላሾች   ትንታኔ ተሰጥቷቸዋል:: በሔዋን አምድ ከተዘገበዉ ውስጥ እንደ አብነት የመሥራት ፍላጎት ቢኖራትም በመሥሪያ ቦታ እጦት ተጠቃሚ ያልነበረች ወጣት ችግር አንዱ ነበር:: የበኩር የሔዋን አምድም የአካል ጉዳተኛዋን ችግር የሚመለከተውን አካል አነጋግራ በመዘገቧ    የመሥሪያ ቦታ ማግኘት ችላለች::

በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም  በተጎዱ የክልሉ አካባቢዎች የበኩር ሪፖርተሮች  በአካባቢዉ እየተዘዋወሩ  የሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ የአስገድዶ መድፈር አደጋ የደረሰባቸውን ሴቶች የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በማነጋገር  ከችግሩ ሊወጡ  ስለሚችሉበት  መንገድ  በዝርዝር እና በተከታታይ  በበኵር ሔዋን አምድ ዘግበዋል:: አሁንም ካለው ወቅታዊ የሰላም እጦት ችግር ለመውጣት የሴቶች ሚና ምን ሊሆን ይገባል? የሚለውን ሩዋንዳን ከመሰሉ ሀገራት ተሞክሮን በማንሳት በኩር አስተማሪ ዘገባዎችን በመሥራት ላይ ናት::

በግለሰብ ደረጃ በርካታ ስኬታማ ሴቶች በመኖራቸው በክልል፣ በሀገር ብሎም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ ሴቶች ያለፉባቸውን መንገዶች የሚያስረዱ ጽሑፎችን ይዛ እየወጣች ቀጥላለች::

ወጣቶች

የወጣቶች ጉዳይ ከማህበራዊ አምድ ወጥቶ  ራሱን ችሎ “አፍለኛ”  በሚል ዓምድ በየሳምንቱ ሲስተናገድ የነበረው  ወጣቶችን የተመለከቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ፣ በመደራጀት ልምድን ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው በማስፋት፣ በሀገር ግንባታ ሊያደርጉት የሚገባውን አስተዋፅኦ… በመተንተን ነበር:: በተለይም በ1987 ዓ.ም መጋቢት 29 በወጣው የበኵር ጋዜጣ ስለአደንዛዥ እፆች በተለይም ጫት እና ሌሎች ሱስ አምጭዎች  ከተስፋፉ “ሀገርን ማን ሊረከብ ይችላል?” በሚል ርዕስ ሊገጥም ከሚችለው ችግር አንፃር ሊወጣ ስለሚገባው ሕግ እና በሕጉ ዙሪያ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን እንደነበረ ተዳሷል::

ዛሬም ላይ በወጣቶች እና ማሕበራዊ አምድ ሱስ ያስከተለው ጉዳት፣ በሱስ ዙሪያ ቤተሰብ ውስጥ እየገጠመ ያለው ፈተና እና ከተሞች ይሕንን ለመከላከል እያወጡት ያለውን ሕግ ዛሬ ከገጠመው ፈተና አንፃር በኵር ሽፋን ሰጥታለች፤ እየሰጠችም ነው::

በኩር ባለፈው ዓመት /2016 ዓ.ም/ ማሻሻያ ከተሠራ በኋላ ደግሞ አምዶቿ አንድ ሆነው ከ30 ዓመት በፊት በነበረው ማሕበራዊ የሚል መጠሪያ   የሴቶች፣ የወጣቶች፣የቤተሰብ እና የጤና ዘገባዎች እየተፈራረቁ ሽፋን እየተሰጣቸዉ ቀጥለዋል::  ከዚህ በተጓዳኝ የማህበራዊ ችግሮች /ስለልጆች አስተዳደግ፣ ማህበራዊ  ሥነ ልቦናዊ እና ሌሎችም ይዘቶች በበኩር ጋዜጣ  እየተስተናገዱ ተደራሽነታም አለማቀፋዊ እየሆነች  ቀጥላለች::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here