በኵር ጋዜጣ ከተመሠረተችበት ታህሣሥ 7/1987 ዓ.ም ጀምሮ በ30 ዓመታት ጉዞዋ በተለያዩ ዓመታት የገፅ፣ የአዳዲስ ዓምዶች ጭማሪ እና ስያሜ ለውጥ አድርጋለች፡፡ ለአብነት ቀደም ባሉት ዓመታት “ተፈጥሮ” በሚል አምድ “እፅዋት” እና “እንስሳት” በየሳምንቱ እየተፈራረቁ ለሕትመት ይበቁ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ በዞን እና በወረዳ ከሚገኙ ለአንባቢያን በተሰጠ መጠይቅ ከተሰበሰበ ምላሽ እና የአዘጋጆች ትንተና አዳዲስ ዓምዶች ተከፍተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል” አግራሞት” አንዱ ነው፡፡
አግራሞት በመፅሔት አቀራረብ አራት ይዘቶችን ሁለት አስገራሚ ወይም ድንቃ ድንቅ፣ አንድ ተፈጥሮ እና አንድ የሳይንስ ግኝቶችን አካቶ ሲወጣ ነበር፡፡ በሂደቱ በባለሙያዎች የቀረበው የለውጥ መነሻ ወደ ድርጅቱ መሪዎች ቀርቦም ተቀባይነት አግኝቶ ለአንባቢ በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡
አግራሞት ለዓምዱ የሚመጥኑ ፅሁፎች ከተለያዩ ድረ ገጾች ተተርጉመው የሚቀርቡበት አምድ ነው፡፡ ፅሁፎቹ ገላጭ እና ሳቢ ይሆኑ ዘንድም በፎቶ ግራፍ ይደገፋሉ፡፡ የፅሁፍ፣ የፎቶ አቀማመጥ እና ቅንብሩ በሂደቱ ፐብሊሸር ኦፊሰር ባለሙያዎች ነው የሚከወነው፡፡
ለአብነት በአግራሞት ዓምድ ተስተናግደው ለህትመት ከበቁ ተፈጥሮ፣ ድንቃ ድንቅ እና ሳይንስ ነክ ይዘቶች ጥቂቶቹን እስኪ እንጥቀስ፤
ተፈጥሮ ከውጪ ሀገራት
– ሳቮ ምእራብ ብሔራዊ ፓርክ እና ሳቮ ምሥራቅ ብሔራዊ ፓርክ /መገኛ ሀገር ኬኒያ/
– ቾቤ ብሔራዊ ፓርክ – መገኛ ሀገር – ቦትስዋና
– ክሩገር ብሔራዊ ፓርክ – መገኛ ሀገር- ደቡብ አፍሪካ
– ታራንጊር ብሔራዊ ፓርክ – መገኛ ታንዛኒያ ወ.ዘ.ተ ሽፋን ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ ደግሞ
• ሎካ ዓባያ ብሔራዊ ፓርክ – ደቡብ ኢትዮጵያ ሲዳማ
• ሻላ ሐይቅ /ደቡብ ኢትዮጵያ ከሞያሌ 225 ኪሎ ሜትር ርቀት
• ያቤሎ ብሔራዊ ፓርክ – ኦሮሚያ ክልል – ቦረና
• ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ – ደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ
• የባሕር ዳር ዓባይ ወንዝ ሚሊኒዬም ፓርክ – መገኛ አማራ ክልል ባህር ዳር ዓባይ ከጣና መውጫው እስከ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ ይጠቀሳሉ፡፡
ሳይንስ
በቀን ከሰባት ሰዓት ያነሰ የእንቅልፍ ጊዜን ለወራት እና ዓመታት የሚያሳልፉ ሴቶች ለደም ግፊት ይዳረጋሉ፤
– በጠፈር ላይ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የሳተላይት ወይም የጠፈር ላይ ወይም የማምጠቂያ ስብርባሪ ብዛቱ በእጅጉ መጨመሩ፤ ስብርባሪው በሙቀት ፈራርሶ ከባቢ ዓየርን መበከሉ በተጨማሪ ለቀጣይ ከባቢ ዓየርን ከመበከሉ በተጨማሪ ሳተላይት የማምጠቅ ሂደትን ማስተጓጐሉ እና ወደ ፊትም እንደሚያስተጓጉል ተጠቁሞበታል፡፡
– በዓየር ንብረት ለውጥ በየሀገራት እና ቀጣናዎች ሙቀት በመጨመሩ በተለይም በሰሜን ዋልታ ግግር በረዶ መቅለጡ በአካባቢው የሚኖሩ ድብን የመሣሰሉ እንስሳት መሰደዳቸው፤
– በውቅያኖስ የባህር ዳርቻ የውኃው ከፍታ መጠኑ በመጨመሩ ባስከተለው መጥለቅለቅ ጉዳት መድረሱ፤
– በየፋብሪካዎች ለቁስ መያዣ ወይም ማንጠልጠያ እና ለፈሳሽ ማሸጊያ የሚውሉ የኘላስቲክ ጠርሙሶች በዘፈቀደ መጣል በአካባቢ በሰው እና በእንስሳት ላይ የሚያደርሱት የጤና እክል፤
– ተፈጥሯዊ ያልሆኑ “ነን ኦርጋኒክ” የምግብ ይዘቶች ላልታፈለገ ውፍረት እንደሚዳርጉ በዚሁ ሳቢያ ከመጠን በላይ የወፈሩ ሰዎች በመድሃኒት ለመቀነስ ከመጣር በተሻለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በባለሙያዎች መመከሩ ተመላክቷል፡፡
ድንቃድነቅ
በአግራሞት ዓምድ ስር በተካተቱ ድንቃ ድንቅ መጣጥፎች፣
• በስልሳ ዓመት እድሜ “ለወይዘሪትነት” በሚል ርእስ ለቁንጅና ውድድር የተሳተፉ ሴት፤
• ትንሿ “የሿኦሊን ኮከብ” በቻይና “ኩንግፉ” አክሮባት ወይም የመገለባበጥ ትርኢት ተሸላሚዋ የ14 ዓመቷ ታዳጊ፤
• በቻይና ረዢም ርቀት ውሎ እና አዳር ለሚያሽከረክሩ ሾፌሮች እንቅልፍ እንዳይጥላቸው ከአደጋ እንዲጠበቁ ማንቂያ “የሌዘር ብርሃን” የሚረጭ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ስለመዋሉ ቀርቧል፡፡
• የ103 ዓመቱ አዛውንት ባለቤታቸውን አዝለው ከዘጠኝ ሺህ ጫማ ከፍታ በ “ፓራሹት” ስለመዝለላቸው፤
• በቻይና በረሃማ ቀጣና በሚገኝ የመስህብ ስፍራ በግመል ተጓጉዘው ለሚጐበኙ በመተላለፊያ መንገዱ ላይ መጨናነቅን ለመግታት የትራፊክ መብራት በመትከል ለችግሩ መላ መዘየዱ፣
• በአሜሪካ ዴንቨር ኮሎራዶ በአንቅልፍ ላይ እያሉ የእለት አደጋ የተከሰተበትን ቤተሰብ ቀድማ የተመለከተች ውሻቸው ቀስቅሳ ከቃጠሎ መትረፋቸው አጀብ ማሰኘቱ ለንባብ በቅቷል፡፡
• እርጅናን መርታት ይቻላል? እንዴት? የመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ለንባብ በቅተውበታል 2/11/2010ዓ.ም የስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ማዘጋጃ ቤት በማህበራዊ ድረ ገፅ ለንባብ እንዳበቃው ፖንቾ የተሰኘው ስልጡን ውሻ አውቆ ራሱን የሳተ መስሎ የተኛ ፖሊስ ጓዳኛውን ትንፋሹ እንዳይቋረጥ ሲረዳውና የልብ ምቱን ሲያዳምጥ የተነሳውን ምስል ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገፅ ለዕይታ አብቅቶታል፡፡
• ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ለንባብ በበቃችው በኲር በባህር ዳርቻ ላይ ከነፋስ ኃይል ማመንጨት በዓለማችን በስፋት የተለመደ እንዲሁም በባህር ላይ ተንሳፋፊ የሀይል ማመንጫን እውን ለማድረግ በሙከራ ላይ ስለመሆኑ ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግን ጠቅሳ አስነብባለች፡፡
• ዙንግ ኮንግሩንግ በቻይና ቾንግኩንግ ከተማ የተሰካለት ነጋዴ ሲሆን ከዚህ ስኬቱ ባሻገር በሚኖርበት ከተማ ጐዳናዎች ላይ በእግሩ ሲንቀሳቀስ በዓይኑ የገቡ የተጣሉ ቆሻሻዎችን በመልቀም እና በማጠራቀሚያዎች ውስጥ በመክተት ተዋቂ ነው፤ ልምዱን እና ተነሳሽነቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገፅ ዘግቦት በኲርም አስነብባናለች፡፡
በአግራሞት አምድ አንባቢን የሚስቡ እና የሚማርኩ፣ አዲስነት ያላቸው ይዘቶች በአንድ ገጽ ተቀንብበው ለህትመት የሚበቁበት በመሆኑ በቀጣዮቹ ዓመታትም ተመራጭ ሆኖ እንደሚቀጥል እምነታችን ነው፡፡
መልካም 30ኛ ዓመት!
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታኅሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም