የ30 ዓመታት የውጪ ሰፖርት አምድ ሲዳሰስ

0
132

እንደ ዛሬው ዓለም አቀፍ የስፖርት ምረጃዎችን በእጅ ስልካችን በማናገኝበት ዘመን በኵር ጋዜጣ ከታህሳስ ሰባት ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች መረጃዎችን በመሰብሰብ ለአንባቢያን ታደርስ ነበር። ማህበረሰቡ፣ ስፖርት አፍቃሪያን፣ ስፖርተኛው፣ ባለሙያው እና የስፖርት አመራሩ ስለ ስፖርት ያለው ግንዛቤ ከፍ እንዲል፣ በጎ ነገሮችን እና ተሞክሮችን እንዲቀስም በኵር ጋዜጣ በአምዷ ሠርታለች።

አዳዲስ ስፖርቶች እንዲለመዱ እና የተሻሻሉ የስፖርት ሕግ እና ደንቦች በሀገር ውስጥ እንዲተዋወቅ በውጪ ዘገባ ሽፋን ሰጥታ ዘግባለች። በ30 ዓመታት የበኵር ጉዞ በስፖርት አምድ ከውጪ ያልተነካ፣ ያልተዳሰሰ የስፖርት ዓይነት እና ርዕሰ ጉዳይ የለም። ከቤት ውስጥ እስከ ቤት ውጪ ውድድር በአጭር እና በትንታኔ ዘገባ ተሠርቷል።

በተለይ ደግሞ በሀገራችን የሚታወቁ እና የተለመዱ ሁሉም የስፖርት ዓይነቶች፣ አልፎ አልፎ ልዩ የሆኑ የስፖርት ሁነቶችም  በውጪ ዘገባ ተዳሰዋል። እነዚህ ዘገባዎች ከስፖርት አምድ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በተሳታፊዎች እንደተዘገቡ ጭምር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ጋዜጣዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህትመት ስትበቃ የውጪ ዘገባ አልተካተተም ነበር። በአምዱ የውጪ ዘገባ መካተት የጀመረውም ከይካቲት ሦስት ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

በወቅቱም ከተሳታፊዎች የተላከ አጭር የውጪ ዘገባ ነበር የተካተተው። በተከታታይ በስፖርት አምደኛነት  ይሳተፍ የነበረው ባርክልኝ (ከባሕር ዳር) “ክሊንተን የስፖርት ምርኮኛ ናቸው”። የሚል ጽሁፍ ነበር ያስነበበው። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢን ክሊንተን የአሜሪካ እግር ኳስ (NFL) ይወዱ እንደነበር ዘገባው ያስነብባል።

በዚሁ እትም የተካተተው ሌላኛው የውጪ ዘገባ “በ1994 እ.አ.አ ትልቁ ዜና በአሜሪካ- የዓለም ዋንጫ የሚል አርዕስት ያለው ነው። 1994 እ.አ.አ አሜሪካ ስላስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ዘገባው ያስረዳል። ታምሩ ዳኛቸው ከአዴት ደግሞ ስኔ ሁለት ቀን 1987 ዓ.ም “በዓለም ዋንጫ ኮከብ የነበሩ ተጫዋቾችን ያስቃኘበትን ጽሁፍ እናገኛለን።

የስፖርት ጽሁፎች አጫጭር ሲሆኑ እንደተገኘ ሁለትም ሦስትም ረዕሰ ጉዳዮች በገጹ ይስተናገዱበታል። ምናልባት የሀገር ውስጥ ዘገባ በአምዱ ካልተካተተ እስከ ሦስት የሚደርሱ የውጪ ዘገባዎች በአምዷ ሊስተናገድ እንደሚችል ተገንዝበናል። ነሐሴ አምስት ቀን 1987 ዓ.ም “ፈረሰ ፈጅ- አዲሱ ውድድር” የሚል ዘገባ ጋዜጣዋ በስፖርት አምድ  ይዛ መውጣቷን ተመልክተናል። በዚህ ዘገባ በፈረስ እሽቅድድም ስፖርት ፈረሶች መሰናክሎችን ለመዝለል ተቸግረው ህይወታቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ ያስነብባል። በአንድ ዓመት ብቻ 13 ፈረሶች ህይወታቸውን እንዳጡ እና ጉዳት እንደደረሰባቸው ያስነብበናል።

በወቅቱ ፈገግ ከሚያሰኙ እና ድንቅ የዘገባ አርዕስቶች በተጫማሪ አልፎ አልፎ ግልጽ ያልሆኑ የዘገባ አርዕስቶችንም ተመልክተናል። ግንቦት 22 ቀን 19997 ዓ.ም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሊቨርፑል ኤስሚላንን አሸንፎ ዋንጫ ሲያነሳ “ግመል በመርፌ ቀዳዳ ባያልፍም ሊቨርፑል ሻምፒዮን ሆኗል” የሚል ፈገግ የሚያሰኝ አርዕስት ለህትመት በቅቷል።

ይካቲት ዐስር ቀን 1987 ዓ.ም በወጣው እትም “ኦ.ኤዩ ፊፋን አወገዘ” የሚል የዘገባ ርዕስ እናገኛለን። ኦ.ኤዩ( OAU) የእንግሊዘኛ ምህዳረ ቃል ሲሆን በአማረኛ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ነው። የዘገባው አንድምታም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፊፋን ያወገዘበት መሆኑን ያትታል።

በዚሁ ቀን በውጪ ደግሞ “ስፖርት እና አስገራሚ ታሪኮች” በሚል ርዕስ ለዓለም ሰላም እና አንድነት የስፖርት ኃይል በስፋት ተዳሶበታል። እስከ 2006 ዓ.ም በስፖርት ዓምድ የሀገር ውስጥ ዘገባ ያልተካተቱባቸው እትሞችንም ተመልክተናል። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም ስለ ዓለም ዋንጫ አስገራሚ ታሪኮች እና ስለ ዓለም ዋንጫ አጀማመር ሁለት የውጪ ዘገባዎች ብቻ ተስተናግደዋል። በተመሳሳይ ጳጉሜ ወር 2006 ዓ.ም ሁለት የውጪ ዘገባዎች ብቻ መሠራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ልክ እንደ ሀገር ውስጡ የውጪ ዘገባው ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ በተለይ ከ2005 ዓ.ም በኋላ ከአጫጭር ዜናዎች በተጨማሪ በጥልቀት በትንታኔ ዘገባዎች ይሠሩ ነበር። ሚያዚያ ስድስት ቀን 2006 ዓ.ም “ስፖርት እና አስገራሚ ታሪኮች” በሚል ርዕስ ለዓለም ሰላም እና አንድነት የስፖርት ኃይል በስፋት ተዳስሶበታል። እስከ 2006 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ዘገባ ካልተካተተ ሙሉ አምዱ በውጪ ዘገባ ይሸፈን እንደነበር መረጃዎችን አግኝተናል።

ለአብነት ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም ስለዓለም ዋንጫ አስገራሚ ታሪኮች እና ስለ ዓለም ዋንጫ አጀማመር በስፖርት አምዱ የተስተናገዱ የውጪ ዘገባዎች ናቸው። በተመሳሳይ ጳጉሜ ወር 2006 ዓም በአምዱ የውጪ ዘገባዎች ብቻ የተስተናገዱበት ወቅት ነበር። በዚህ እትም “ዘረኝነትን ድል ነስቶ የደመቀ ተጫዋች” በሚል ርዕስ የቀድሞው ካሜሮናዊው ኮከብ የሳሙኤል ኤቶ ታሪክ በትንታኔ ቀርቧል።

ስለደቡብ አፍሪካው ዝነኛው የራግቢ ስፖርት በባህሪያቸው ተሰጥኦቸውን የቀበሩ ተጫዋቾችን፣ የቦቢ ሰር ቻርልተን ህልፈተ ህይወት፣ አካል ጉዳት ያልበገራቸው ስፖርተኞች ታሪክ፣ የእውቁ የቀድሞ ዓለም አቀፍ ዳኛ ፔርሉጂ ኮሊና ታሪክ፣ ስለድምጸ መረዋው የቀጥታ የጨዋታ አስተላላፊ (ኮሜንታተር) ፒተር ዱሩሪ የህይወት ታሪክ፣ ስለአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ስኬት እና ውድቀት፣ በአውሮፓ እግር ኳስ የዝውውር ጉዳዮች፣ ስለ 20ኛው እና 21ኛው ክፍለ ዘመን ቡጢኞች፣ አሜሪካውያን የጅምናስቲክ ስፖርት፣  የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ውድድር፣ ኮሌጅ የበጠሱ ስፖርተኞች ታሪክ እና እያደገ ሰለመጣው የሳውዲ የስፖርት ገበያ ከብዙ በጥቂቱ በጥልቀት በውጪ የሰፖርት አምዳችን የተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታኅሳስ 7  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here