“ሞክሼ ፊደላት ሞክሼ ይባሉ እንጂ የተለያየ ትርጉም አላቸው”

0
155

የኅዳር 7 ቀን 2017 እትም እንግዳችን  ከነበረው ባልደረባችን አባትሁን ዘገየ ጋር በነበረን ቆይታ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ እንዴት እና መቼ እንደገባ፣ የበኲር ጋዜጣ እንዴት እና መቼ እንደተመሠረተች፣ በወቅቱ ይከተሉት የነበረው አሠራር እንዲሁም በጋራ የመሥራት ባህላቸው… ምን ይመስል እንደነበር ጠይቀነው የሰጠንን ምላሽ ማስነበባችን እና ቀሪውን ክፍል በዚህ እትም ልናስነብባችሁ በቀጠሮ መለያየታችን ይታወሳል:: እነሆ በዘገባ ቀጠሯችን መሠረት በዘገባ ወቅት ያጋጠሙትን ገጠመኞቹን፣ የበኲር ጋዜጣ ተሳታፊዎችን፣ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ከበኲር ጋር የዘለቀበትን ምስጢር፣  በሕትመት ጋዜጠኝነት  ለረዥም ዘመን በመቆየቱ ያገኘውን ጠቀሜታ፣  በቋንቋ አጠቃቀም የሚስተዋሉ ችግሮችን፣    ወደ ሥነ ጽሑፍ ዓለም የገባበትን አጋጣሚ፣ የድርሰት ሥራዎቹን እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ላነሳንለት ጥያቄዎች የሰጠንን  ምላሽ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል::

መልካም ንባብ!

 

በዘገባ ወቅት ከተከሰቱ ገጠመኞችህ እስኪ እንነሳ…

የክልሉ ፕሬዝዳንት መግለጫ ይሰጣሉ ተብለን መቅረጸ ድምጾቻችንን፣ ካሜራዎቻችንን፣ ማስታወሻ ደብተሮቻችንን… አዘጋጅተን ወደ ክልል ምክር ቤት ሄድን::  መግለጫውን ከሰጡ በኋላ ጥያቄ ካላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ አሉንና ጥያቄዎችን አቀረብን:: እኔ ሁለት ጥያቄዎችን ማቅረቤን አስታውሳለሁ:: አብረውኝ የነበሩት ባልደረቦቼም ጥያቄዎችን አቀረቡ:: መግለጫው እና ቃለ ምልልሱ ተጠናቀቀና የሥራ መሣሪያዎቻችንን ሰብስበን ተመለስን::

ቢሮ እንደገባሁ በድምጽ የያዝሁትን የርዕሰ መስተዳድሩን መግለጫ እንዲሁም ለጥያቄዎቻችን የሰጡንን መልስ ወደ ጽሑፍ ገልብጨ ዜና እንዲሁም ሀተታ ለመሥራት ቴፔን ከፈትሁት::  ባጋጠመኝ ነገር በጣም ደነገጥሁ፤ መቅረጫውን ተጫንሁ ብየ ካሴቱ እንዳይዞር የሚያደርገውን ቁልፍ ለካ ተጭኜው ኖሮ ሳይቀርጽ አገኘሁት::  ለጊዜው በጣም ብደነግጥም አብረውኝ የሬድዮ እንዲሁም የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ስለነበሩ ድምጹን ከእነሱ ወስጄ ያሰብሁትን ዘገባ ሠራሁ::   ብቻየን ሄጄ ቢሆን ኖሮ ሊደርስብኝ የነበረውን ውርደት ሳስብ ዛሬም ድረስ ችግሩ ገዝፎ ይታየኛል::

 

በኲር እንደተመሠረተች እንዲሁም ከዚያ በኋላ ስለነበረው የተሳታፊዎች ሚና እስኪ አጫውተን…

በኲር ሕዝባዊ መሠረት ኖሯት ለሠላሳ ዓመታት ትዘልቅ ዘንድ ቀደምት ተሳታፊዎች የማይተካ ሚና ተጫውተዋል:: በተለይም ከተመሠረተች ጀምሮ  አንደኛ ዓመቷን እስካከበረችበት ታህሣሥ 7 ቀን 1988 ዓ.ም. ድረስ  በየቀኑ ባማካኝ ሦስት ደብዳቤዎች ለዝግጅት ክፍሉ ይደርሱ ነበር፤ ከፓዊ፣ መቀሌ፣ ቴፒ፣ አዲስ አበባ፣ ዲላ፣ ባሕር ዳር፣ ደባርቅ፣ አዴት፣ ጎንደር፣ ወልድያ፣ ደሴ፣ ቆቦ፣ ደብረ ታቦር፣ ቻግኒ፣ ኮሶበር፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዳንግላ፣ ወረታ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች::

የተለያዩ ጽሑፎችን በመላክ ንቁ ተሳትፎ ካደረጉት የበኲር ባለውለታዎች መካከልም ታምሩ ዳኛቸው፣ ስለሺ ደምሴ፣ ከበደ እጅጉ፣ ዑመር መሐመድ፣ ስለሺ አምባው፣ አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ)፣ እንደሻው ሺፈራው፣ ፀሐየ መሰለ፣ ከበር ጌታቸው፣ ዓለምሸት ምህረቴ፣ ጐራው ሳልለው ሞያው አስናቀው፣ ታቦር ገብረ መድኅን፣ አሻግሬ ጉግሳ፣ ጃክ ሲራክ… ተጠቃሾ ናቸው::

እነዚህና ስማቸውን ያልገለጽናቸው ተሳታፊዎች ጽሑፍ በመላክ  ክፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ብርሃኑ ክንዱ ደግሞ ካሥር ዓመት በላይ የካርቱን ሥዕሎችን በሥራ ጫና ውስጥ ሆኖ ያለማሰለስ እየሳለ በመስጠት ለበኲር ተነባቢነት የማይተካ አስተዋጽኦ አበርክቷል:: እንዲሁም ሠርፀ ድንግል ጣሰው የካርቱን ሥዕሎችን በመሳል እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በኲር ተነባቢ ሆና ለረዥም ዘመን ትዘልቅ ዘንድ በእርግጥም የእነዚህ ተሳታፊዎቻችን ውለታ መቼም ቢሆን የሚዘነጋ ኤይደለም::

የመጀመሪያው የበኲር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌጠነው ዘውዱ፣ ከእሱ በመቀጠል የዋና አዘጋጅነቱን ኃላፊነት እየተረከቡ የመሩት ኡስማን መሀመድ፣ አባትሁን ዘገየ፣ አበረ አዳሙ፣ ቻላቸው አቻምየለህ፣ ያዕቆብ ሲራክ፣ መዝሙር ሀዋዝ፣ፋንታየ ዘገየ፣ በቀለ አሰጌ፣ ሀብቴ ነጋ፣ ይህዓም መለሰ፣ ጥላሁን ቸሬ እንዲሁም የመጀመሪያዋ  ሴት የበኲር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆና እየሠራች ያለችው ስንቅነሽ አያሌውም ስለበኲር ጋዜጣ ታሪክ ሲወሳ ስማቸው አብሮ የሚነሳ ባለውለታዎች ናቸው::

ተሳታፊዎች፣ ዋና አዘጋጆችም ሆኑ ስማቸውን እዚህ ያልተጠቀሰው በኲር ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በሪፖርተርነት፣ በአዘጋጅነትም ሆነ በምክትል አዘጋጅነት የሠሩ እንዲሁም እየሠሩ ያሉ የበኲር ጋዜጠኞች  በደማቁ ብዕራቸው ምንጊዜም የማይደበዝዝ ደማቅ አሻራ በኲር ላይ  አትመው አኑረዋል፤ ደግሞም እያተሙ ነውና በዚህ አጋጣሚ በእጅጉ ልናመሰግናቸው እንወዳለን::

በኲር 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን አክብራለች:: አንተ ደግሞ በኲርን ከተቀላቀልህ 28 ዓመታት ተቆጥረዋል:: ይህን ያህል ዘመን ከበኲር ጋር የመቆየትህ ምስጢር ምንድነው?

“የሚፈልገውን ያጣ ልብ ዘወትር መንገደኛ ነው” ይባላል::   በሌላ አገላለጽ  ያባባሉ ትርጉም የሚፈልገውን ያገኘ ልብ አንድ ቦታ ተረጋግቶ ሥራውን ይሠራል  የሚል ሆኖ እናገኘዋለን:: እኔም ይህን ያህል ዘመን በበኲር ተወስኘ የኖርሁት  አልመው የነበረው ጋዜጠኛ የመሆን ህልም በበኲር እውን ሆኖ ስላገኘሁት ነው::

እስኪ ቦረቦር ዘዳር አገር ስለሚለው የብዕር ስምህ አጫውተን…

ቦረቦር ዘዳር አገር ከመደበኛው ስሜ ባልተናነሰ ደረጃ የምወደው የብዕር ስሜ ነው:: ይሄን የብዕር ስም የወሰድሁት በተወለድሁበት አካባቢ ከሚገኝ እጅግ ማራኪ የተፈጥሮ ገጽታ ካለው የገጠር ቀበሌ ስያሜ ነው:: በዚህ የብዕር ስም መጠቀም ከጀመርሁ የጋዜጠኝነት ዘመኔን ያህል አስቆጥሬያለሁ:: በተለያየ መንገድ ከሚደርሱኝ አስተያየቶች መረዳት እንደቻልሁትም በስሜ ከምጽፋቸው ጽሑፎች ባልተናነሰ ደረጃ በዚህ የብዕር ስሜ የምጽፋቸው መጣጥፎች ባንባቢያን ዘንድ ቅቡል ሆነው አግኝቻቸዋለሁ:: የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዚህ የብዕር ስም ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣፣ፖለቲካዊ  እንዲሁም መዝናኛ  ነክ እንከኖቻችንን እየነቀስሁ የማስነብብበት ስለሆነ ነው::

በኲር ለረዥም ጊዜ በመሥራትህ አተረፍሁ የምትለው ነገር ምንድነው?

በኲር ለረዥም ጊዜ በመሥራቴ የቋንቋ እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ ችሎታየን አሳድጌያለሁ ብየ አስባለሁ:: እውነት ለመናገር በዩኒቨርሲቲ ቆይታየ ካገኘሁት ዕውቀት ይልቅ በኲር ላይ በቆየሁባቸው ዓመታት የቀሰምሁት ዕውቀት ይበልጣል:: በኲር ጋዜጣን ስናዘጋጅ በትንሹ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንማማራለን፤ በቅድመ ህትመት እንዲሁም በድኅረ ህትመት ውይይት:: በቅድመ ህትመት ዘገባዎቻችንን ከቅርጽም ሆነ ከይዘት አንጻር እንዴት መዘገብ እንዳለብን፣ የዘገባችንን ጥራት፣ ወቅታዊነት፣ ሚዛናዊነት… እንዴት ማስጠበቅ እንዳለብን  በስፋት እንወያያለን:: ጋዜጣዋ ከተዘጋጀች በኋላም በተነጋገርነው መንገድ ምን ያህል ሠርተናል በማለት ጥንካሬ እንዲሁም ድክመቶቻችንን እየነቀስን እንማማራለን:: እንዲህ ዓይነቱ መማማር ከተግባር ጋር የተገናኘ ስለሆነ ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰው ከዩኒቨርሲቲ ያልተናነሰ ዕውቀት እንዲሁም ክህሎት የሚጨብጥበት ነው::

ብዙ ጊዜ ፊደላት በትክክለኛ ቦታቸው ሊገቡ ይገባል፤ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ ወቅት ባዕድ ቃላትን ያለቦታቸው ከመጠቀም መቆጠብ አለብን በማለት ስትሞግት እንሰማለን:: በሌላ በኩል ግን መግባባት እስከተቻለ ድረስ ይሄ ነገር ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም የሚሉ አሉ:: ስለዚህ ጉዳይ እስኪ አጫውተን…

ቀደምቶቻችን ሞክሼ ፊደላትን የፈጠሩት በምክንያት ነው:: ሁሉም ሞክሼ ፊደላት ሞክሼ ይባሉ እንጂ የተለያየ ትርጉም አላቸው:: ያ ትርጉማቸው ሳይፋለስ የተፈለገውን መልዕክት ማስተላለፍ ይችሉ ዘንድ በተገቢው ቦታቸው መግባት ይኖርባቸዋል:: ለምሳሌ አመት እና ዓመት፣ ሠረቀ እና ሰረቀ፣ በአል እና በዓል የተለያየ ትርጉም አላቸው:: ዘመንን ለማመልከት አመት ብለህ ብትጽፍ፣ የፀሐይን መውጣት ለማመልከት ሰረቀ ብለህ ብትጽፍ ወይም አገልጋይ የሚለውን ትርጉም ለማመልከት በዓል ብትል የምታስተላልፈው መልዕክት የተዛባ ይሆናል:: ስለዚህ ፊደላቱን በትክክለኛ ቦታቸው መጠቀም ግድ ይላል::

በንግግርም ሆነ በጽሑፍ ወቅት ባዕድ ቃላትን መቀላቀልም ምርቅን እና መረቅን የመቀላቀል ያህል ጤናን የሚነሳ ነገር ነው:: እኔ ያማርኛ አቻ ቃል እያለ ባዕድ ቃሉ አላስፈላጊ ተቀላቅሎ ተጽፎ ሳነበውም ሆነ ሲነገር ስሰማው ውስጤ በጣም ነው ሰላም የሚያጣው::  አያት ቅድመ አያቶቻችን ያማርኛ ቋንቋን አሳድገው እና  አበልጽገው አስተላልፈውልናል:: የተለያዩ አገራት አማርኛን በክብር ተቀብለው በዩኒቨርሲቲዎቻቸው በትምህርትነት እየሰጡት ነው:: እኛ ግን ቀደምቶቻችን  ያሳደጉ ያበለጸጉትን፣ ዓለም እጁን ዘርግቶ የተቀበለውን የሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ሀብት የሆነውን አማርኛ ቋንቋችንን እየገደልነው እንገኛለን:: ማሳደግ እና ማበልጸግ ቢሳነን እንዴት ያደገ እና የበለጸገ ቋንቋችንን እንገድላለን? ይሄ ፈጽሞ ያልተመለሰልኝ፣ ደግሞም ውስጤን ሁሌም የሚያሳምመኝ ጥያቄ ነው::

ወደ ድርሰቱ ዓለም መቼ እና በምን ሥራ ገባህ?

ወደ ድርሰቱ ዓለም የገባሁት በ2007 ዓ.ም. አጋማሽ ነው:: በወቅቱ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ኃይለ ጊዮርጊስ ማሞ የበኲርን ተነባቢነት ማሻሻልን ዓላማው ያደረገ የአሥራ አምስት ቀን ሥልጠና ሰጥቶናል:: ሥልጠናው የጋዜጠኝነት ይባል እንጂ የሥነ ጽሑፍም ነበር ማለት ይቻላል:: ለምን ቢሉ ያን ሥልጠና መውሰዳችን በኲር ጋዜጣ ውስጥ እንሠራ ከነበርነው  ጋዜጠኞች ቁጥራችን ቀላል የማይባለው አጫጭር ልቦለዶችን እንዲሁም ወጎችን ወደ መጻፍ ገብተናል:: የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የጋዜጣዋን ተነባቢነት ለማሳደግ ከሥልጠናው በኋላ አጫጭር ልቦለዶች እንዲሁም ወጎች የሚጻፉበት “ጥበብ” የተሰኘ አምድ መከፈቱ ነው:: ይህ ሳምንታዊ አምድ ከተከፈተ በኋላ ቀለበቱ የተሰኘች አጭር ልቦለድ ድርሰት ጽፌ በኲር ላይ ታትማ ወጥታለች::

በቀለበቱ የጀመርሁትን አጭር ልቦለድ የመጻፍ ጅምር ገፍቼበት አምስት መድብሎች የሚወጣቸው አጫጭር ልቦለዶች ጽፌያለሁ:: ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ለሕትመት ተዘጋጅተው የፈጠራ ባለቤትነት መብት አግኝቸባቸዋለሁ:: ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የታተሙ ሲሆን አንዱን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን  በደማቅ ሥነ ሥርዓት በማስመረቅ አስተዋውቆልኛል:: ሁለተኛው ድርሰት በ”ኢ ቡክ” ቅርጽ ታትሟል::

በነጻነት እንዲሁም በእርካታ ለረዥም ዘመን የሠራሁበት፣ የሙያ ፍቅርን ያዳበርሁበት፣ ዕውቀት የቀሰምሁበት፣ ወደ ድርሰቱ ዓለምም የገባሁበት መሥሪያ ቤቴ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የበኲር የመንፈስ ልጄ የሆነውን መጽሐፌን ማስመረቁን ለረዥም ዘመን በማገልገሌ የተሰጠኝ ዕውቅና አድርጌ ነው የማየው:: እናም በዚህ አጋጣሚ መሥሪያ ቤቴን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን በእጅጉ ማመስገን እፈልጋለሁ::

በኲር ስትመሠረት የነበረውን የሙያ ፍቅር እንዲሁም ተነሳሽነት ካሁናዊው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እንዴት ታየዋለህ?

በቀደመውም ሆነ ባለንበት ዘመን መንፈሳዊ ቅናት የሚያሳድር የሙያ ፍቅር እንዲሁም ተነሳሽነት ያላቸው ጋዜጠኞች አስተውያለሁ፤ እንዲህ ዓይነት ጋዜጠኞች  ምናልባትም የላቁ ዛሬም ቢሆን አሉ::  በኲር ስትመሠረት የተሟላ የሰው ኃይልም ሆነ የተመቻቸ የሥራ ሁኔታ አልነበረም:: ሥራው እጅግ አድካሚ፣ ኋላ ቀር እና ፈታኝ ነበር:: ሆኖም ከፍተኛ የሥራ ፍቅር ነበር:: የነበሩት ጥቂት ሠራተኞች ሥራን ተሻምተው የሚሠሩ፣ እጃቸው  እየተቆረጠ እየደማ፣ ልብሳቸው በሙጫ እየተበላሸ ሳያማርሩ፣ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ የሚሠሩ ታታሪ ሠራተኞች ነበሩ፤ በስንዴ መሀል እንክርዳድ እንደማይጠፋው ሁሉ አንዳንድ ከዚህ በተቃራኒው የቆሙ ፈጽሞ አልነበሩም ባይባልም:: ዛሬም ቢሆን ምንም እንኳን ሁሉ ነገር ዘምኖ ሥራው የቀለለበት ወቅት ላይ ብንገኝም ይህንን ዘመኑ ያመጣውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም እጅግ አስደማሚ ጥራት ያላቸው፣ ወቅታዊነታቸውን፣ ሚዛናዊነ ታቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን፣ መጣጥፎችን የሚሠሩ እሳት የላሱ ወጣት ጋዜጠኞች አሉ፤ ምነው እኔም እንደ እሱ፣ እንደ እሷ በሆንሁ የሚል መንፈሳዊ ቅናት የሚያሳድሩ፤ ቢሄዱ ሄዱብን እንጂ ሄዱልን የማይባሉ:: ብትሄድ ሄደብን እንጂ ሄደልን አለመባል በእርግጥም መታደል ነው::  እንዲህ ዓይነት ብዙ ሰዎችን አጥተናል፤ በዚያው ልክም አግኝተናል:: እንደእነዚህ ካሉ ታታሪ፣ ቅን፣ ብቁ… ወጣት ጋዜጠኞች ጋር በመሥራቴም ሆነ እየሠራሁ በመሆኔ ዕድለኛ ነኝ ብየ አስባለሁ፤ ሁለተኛ ዩኒቨርሲቲዎቼ ናቸውና::

ዘመናዊው የብዙኃን መገናኛ አውታር (ዲጂታል ሚዲያ) የሕትመቱን ዘርፍ ኅልውና አደጋ ላይ ጥሎታል የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ይሄን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?

የዘመኑ ቴክኖሎጂ  ፈተና ብቻ ይዞ አልመጣም፤ መልካም ዕድልን ጭምር እንጂ:: ስለሆነም በፈተና ውስጥ ሆኖ ያንን መልካም ዕድል መጠቀም ያስፈልጋል:: ለምሳሌ በቀደመው ዘመን ጋዜጣ ታትሞ በጥቂት ቅጅ ለጥቂት አንባቢያን ይደርስ ነበር:: አሁን በበይነ መረብ እንዲሁም በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ባለም አቀፍ ደረጃ የመሠራጨት ዕድል አግኝቷል:: በኲር ጋዜጣም ይህን ዕድል እየተጠቀመች ነው::  ይህን አጠናክሮ መቀጠል ነው የሚያሻው:: የዚህ ዘመን ትውልድ የሚፈልገውን ዘገባ፣ በሚፈልገው የገጽ እንዲሁም የጥራት መጠን እያዘጋጁ ተፎካካሪ እንዲሁም ተመራጭ ሆነን ለመገኜት ከጣርን ለ60ኛ ዓመታችን የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም::

ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም እናመሰግናለን!

እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!::

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here