ኢትዮጵያ ለአትሌቲክስ ስፖርት የማይነጥፍ የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት። በየርቀቱ እንደ አብሪ ኮከብ የሚወረወሩ አትሌቶች የሚፈለፈሉባት ሀገር ጭምር ናት። በአበበ ቢቂላ የተጀመረው ገድል በትውልድ ቅብብሎሽ በወንዶች ማሞ ወልዴን፣ ምሩጽ ይፍጠርን፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴን፣ ቀነኒሳ በቀለን በሴቶች ደራርቱ ቱሉን፣ መሰረት ደፋርን እና ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉ ድንቅ አትሌቶች ወጥተዋል።
አሁን ላይ ግን የእነዚህን ብርቅዬ አትሌቶች ገድል የሚያስቀጥል ትውልድ እየጠፋ ይገኛል:: በጊዜ ሂደት ዘርፉ እየደበዘዘ ስለመሆኑ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል:: ለአብነት ባለፉት ሁለት የኦሎምፒክ መድረኮች ሀገራችን ዝቀተኛ ወጤት ማስመዝገቧ አይዘነጋም:: በዓለም ሻምፒዮናም ቢሆን ያን ያህል የሚያኩራራ ውጤት አልተመዘገበም::
ዛሬም በቆየው ባህላዊ የስልጠና ሂደት እና አስተሳሰብ መመራታችን እና አስተዳደራዊ ችግሮች መኖራቸው ዓለም ከደረሰበት በብዙ ወደ ኋላ ቀርተናል። ስፖርተኞች ሜዳ ውስጥ ተወዳድረው እንዲያሸንፉ ከሚያግዟቸው አሰልጣኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች በተጨማሪ ስፖርቱን በቅርበት የሚመሩት እና የሚከታተሉት ጠንካራ መሪዎች ያስፈልጓቸዋል።
የስፖርት ተቋሙ የአሠራር መንገድም ስፖርቱ ለሚገኝበት አውንታዊም ሆነ አሉታዊ ቁመና ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አያጠያይቅም። ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ያላት የተፈጥሮ ፀጋ ብዙ ቢሆንም በአሠራር ደካማ በመሆኗ ለዘመናት በዘርፉ መሻሻል አልቻለችም።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በቀጣይ አራት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት እና በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ግለሰቦች ተመርጠዋል።
28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ተደርጓል። ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሲመርጡ ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በፕሬዚዳንት ተመርጧል። አትሌት መሠረት ደፋር፣ወይዘሮ ሳራ ሀሰን፣ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ፣ ዶክተር ኢፍረህ መሀመድ፣ አቶ አድማሱ ሳጂ፣አቶ ቢኒያም ምሩፅ፣ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው እና ዶክተር ትዕዛዙ ሞሴ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በመሆን የተመረጡ ግለሰቦች ናቸው። ከሳምንታት በፊት በአትሌቶች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተመረጡት ኮነሬል አትሌት የማነ ፀጋይ እና አትሌት በላይነሽ ኦልጂራ በጉባኤው ተገኝተው ቃለ መኃላ ፈፅመዋል።
እነዚህ መሪዎች በተቋሙ ዘንድ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን የተወሳሰበ ችግር የማስተካከል ትልቅ ኃላፊነት ይዘው ነው በቦታው የተቀመጡት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ምንም እንኳ በሁሉም ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መሳተፍ ብንችልም በተቋሙ ዘንድ ብዙ የአሠራር ክፍተት እንደነበር ግን አይዘነጋም።
በዘርፉ ሀገራችን በሚመጥናት ቁመና ላይ እንዳትገኝ ያደረጋት ደግሞ መሪዎቹድክመት እንደሆነ ይታመናል። ከኢቢሲ ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ መሪዎች የተዘጋጁ ደንቦች፣ ሕጎች፣ መመሪያዎች እና መስፈርቶች ግልጽነትን ባስፈነ አሠራር የማስፈጸም ክፍተት እንደነበረባቸው ያስታውሳል። በተለይ አንዳንድ ውድድሮች ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች መንስኤው ከአሠራር ዝርክርክነት የመጣ መሆኑንም ያስረዳል። በእነዚህ ምክንያቶች በየርቀቱ የሚወጡ አትሌቶች ሲባክኑ ወይም ደግሞ ሲሰደዱ ማየት የተለመደ ነው።
60 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያውያን አትሌቲክስ እንደ ስሙ እና እንደ ታሪኩ በሚመጥነው መልኩ እየተመራ አለመሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። አትሌቲክሳችን በተገቢው መንገድ እየተመራ ባለመሆኑ ከዚህ በፊት በዘርፉ የማይታወቁ ሀገራት ከእኛ ብዙ ልምዶችን በመቅሰም እኛን በብዙ እጥፍ በመብለጥ በዘርፉ ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ሌላኛው ከኢቢሲ ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተመራማሪ ታሪኩ ተመቸ ነው።
ታዲያ ከአዲስ አመራሮች ምን ይጠበቃል? ተቋሙ በጥሩ እና ጠንካራ አመራር ካልተመራ ስፖርቱን ከዓለም ጋር ማገናኘት እና ብቁ የሆኑ ወይም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አትሌቶችን ለማፍራት እንከን ይፈጥራል። ጥሩ ዕይታ ያለው አመራር ብቁ ስፖርተኞች እና ሙያተኞችን ለማፍራት መንገዱን ይዘረጋል። በዘርፉ ዓለም የሚከተለውን የፕሮፌሽናሊዝምን መንገድ እንድንከተል ተቋሙን የሚመሩ አዲስ አመራሮች በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው ነው የተባለው።
ስፖርቱን የሚወድ፣ የተገነዘበ እና በደንብ የተረዳ ባለሙያ በማቅረብ በጋራ መሥራት በችግር ተተብትቦ የቆየውን ተቋም ያነፀዋል ብሏል አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ። ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ባሰፈነ መልኩ ተቋሙን በክህሎት መምራት ከአመራሮች የሚጠበቅ ሌላኛው ተግባር መሆኑን አሰልጣኙ ይጠቁማል። ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብን መከተል፣ ግምገማን እንደጦር የማይፈራ እና ሙያተኛን በትክክለኛው መንገድ የሚመራ መሪ መሆን ከአዲስ አመራሮች እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተመራማሪው ታሪኩ ተመቸ ይናገራል።
በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ለውጥ ለማምጣት ከፈለጉም ዕቅድ፣ ትግበራ እና ግምገማን አብዝተው ባህላቸው ማድረግ እንዳለባቸውም አቶ ታሪኩ ይመክራል። የአንድ ሀገር ስፖርት የሚያድገው በአሠራር ስርዓት (System) ነው። ታዲያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም በችግር ጊዜም የማይናወጥ የአሠራር ሥርዓት መገንባት ከአመራሮች የሚጠበቅ ተግባር ነው ተብሏል። ከአሰልጣኞች እና ከአትሌቲክስ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራትም ከመሪዎች የሚጠበቅ ሌላኛው ተግባር መሆኑን ባለሙያው አቶ ታሪኩ ያብራራል።
አሰልጣኝ ተሾመ በበኩሉ እርስ በእርሳቸው የመገፋፋት ወይም የመሳሳብ አዙሪት ውስጥ እንዳይገቡ ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል ባይ ናቸው። ሀገራዊ ጥቅምን ወደ ጎን በመተው ወደ ግል ጥቅማቸው እንዳይዞሩም የግልጽነት እና የተጠያቂነት አሠራርን መዘርጋት ለነገ የማይተው ተግባር ነው። የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር አሁን ላይ የአትሌቶች እና የአሰልጣኞች ትልቁ የራስ ምታት እንደሆነ አያጠያይቅም። በሀገራችን ብቁ የሆኑ መም (Track) ያላቸው የማዝወተሪያ ስፍራ በመዲናችን እና አቅራቢያ ቦታ ሁለት ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ግቢ ውስጥ የሚገኘው የመሮጫ መም( Track) በማርጀቱ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል። አሁን ላይ ብቸኛው አገልግሎት እየሰጠ ያለው የመሮጫ መምም ሱሉልታ የሚገኝው የቀነኒሳ በቀለ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ነው። ታዲያ በማዘውተሪያ ስፍራ እጦት ለሚቸገሩ አትሌቶች እና ባለሙያዎች አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል ባይ ነው- አሰልጣኙ። ሙያተኛን ሊያቀራርብ እና ለሥራ ሊጋብዝ የሚችል ከባቢ አየር እና ስርዓት መዘርጋትም አትሌቲክሱን አሁን ካለበት ውጥንቅጥ ለማውጣት ያግዛል።
አትሌቶች ጋር የሚታየው ቴክኒካዊ ችግር በምን መንገድ መሰልጠን እንዳለባቸው ፍኖተ ካርታ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል። ታዲያ ለፕሮጀክቶች፣ ለማሰልጠኛ ማዕከላት እና ለክለብ አሰልጣኞች በምን መንገድ ማሰልጠን እንዳለባቸው የሚያመላክት እና አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ስርዓተ ትምህርት ሊኖር ይገባል ባይ ነው አሰልጣኝ ተሾመ። ከብዛት ጥራት ላይ ያተኮረ ሥራ ለመሥራት አትሌቲክሱ በትክክል የሚፈልገውን ሙያተኛ መፍጠርም ከአዲስ አመራሮች የሚጠበቅ ተግባር ነው።
አሁን ላይ ተተኪዎችን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት የተቀዛቀዘ በመሆኑ ከታች ከታዳጊዎች ለመሥራት እንደሀገር የተቀመጠ ሰነድ ባለመኖሩ ተቋሙ በእውር ድንብር ሲጓዝ እንደ ነበር ባለሙያዎች አስታውሰዋል። በቀጣይ ዓመታት ትልቁን የአትሌቲክስ ተቋም የሚመሩት አዲሶቹ አመራሮች ግን ሰነድ ማዘጋጀት እና ተግባራዊ ለማድረግ መጀመር አለባቸው- የባለሙያዎች አስተያየት ነው። አትሌቶች ዜግነት እንዲቀይሩ የሚያደርገው የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ጭምር ነው ተመራማሪው የተናገረው። አቶ ታሪኩ የአሰራር ግልጽነትን መዘርጋት ያስፈልጋልም ብለዋል::
ማናጀሮች የአትሌቶችን ጉልበት እንዳይበዘብዙም ልጓም ማበጀት ከአዲስ አመራሮች ይጠበቃል ተብሏል። በዓመት ሁለት ውድድር በቂ ባለመሆኑ በርካታ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ማሰብ ያስፈልጋልም።
ቋንቋቸው አትሌቲክስ እና እና ስፖርት የሆኑ አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ዕድል መስጠት ተገቢ መሆኑን ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም