የ2024 የዓለም ቼዝ ሻምፒዮና በቅርቡ በሲንጋፖር ተደርጎ ተጠናቋል። እልህ አስጨራሽ የሆነው የፍጻሜ ውድድር ቻይናዊው ዲንግ ሊረን እና ህንዳዊው ጉኬሽ ዶማራጁን አገናኝቷል። የፍጻሜ ውድድሩንም ህንዳዊው ጉኬሽ ዶማራጁ አሸናፊ ሆኗል። የ18 ዓመቱ ህንዳዊ የዓለም ሻምፒዮናን ያሸነፈ በእድሜ ትንሽ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል።
ከዚህ በፊት በትንሽ እድሜው ክብረወሰኑን ይዞ የቆየው በዓለም ሻምፒዮና ታሪክ ጋሪ ካስፓሮቭ ነበር። እ.አ.አ በ1985 ስመጥሩ የቀድሞ የቼዝ ስፖርተኛ በ22 ዓመቱ በእድሜ ትንሽ የመድረኩ ንጉሥ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። የ18 ዓመቱ ታዳጊ ጉኬሽ የዓለም ሻምፒዮናን ያሸነፈ ሁለተኛው ስፖርተኛ ሆኗል።
ሌላኛው ህንዳዊ ቪስዊታና ወይም በቅጽል ስሙ “ቪሺያ” ከዚህ በፊት በመድረኩ አምስት ጊዜ መንገሡን ከግል የታሪክ ማህደሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። የጉኬሽ ድል ታሪካዊ እና ለሌሎች ምሳሌ እንደሆነ ሲ ኤን ኤን አስነብቧል- ጥንካሬው እና ቁርጠኝነቱ ሚሊዬን ወጣት ህንዳውያንን እንደሚያነቃቃ በመግለጽ። ባለፉት ሦስት ዓመታት ጉኬሽ አስደናቂ ድሎችን ተጎናጽፏል።
ጉኬሽ ሰባት ነጥብ አምስት ለስድስት ነጥብ አምስት በሆነ ውጤት ነው ተጋጣሚውን ያሸነፈው። የአምናው የመድረኩ አሸናፊ ዲንግ ሊረን ብርቱ ፉክክር ቢያደርግም በመጨረሻ ለህንዳዊው ታዳጊ እጁን ሰጥቷል። በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለው የ32 ዓመቱ ዲንግ ሊረን በ2023 እ.አ.አ የዓለም ቼዝ ሻምፒዮና አሸናፊ መሆኑ አይዘነጋም። ከዚያ በፊት በ2022 እ.አ.አ ደግሞ በኖርዋዊው የ34 ዓመቱ ማግነስ ካርልሰን ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ሊረን ምንም እንኳ በዘንድሮው ውድድር ቢሸነፍም አሁንም ብርቱ መሆኑን ግን ለደጋፊዎች አሳይቷል። ሽንፈቱን ተከትሎ በዓለም የቼዝ የደረጃ ሰንጠረዥ አንድ ደረጃ ወደ ታች ተንሸራቶ 23ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ሲንጋፖር ይህን የቼዝ የፍጻሜ ውድድር እንድታዘጋጅ በ2023 እ.አ.አ ነበር የተመረጠችው፤ ፍላጎት የነበራቸውን ህንድን እና አርጀንቲናን በማሸነፍ። የሲንጋፖር የቼዝ ፌዴሬሽንም በሲንጋፖር አኳሪየስ ሆቴል ውድድሩ እንዲከናወን አድርገዋል። ውድድሩን ስፖንሰር ያደረገውም ግዙፉ ጉግል ካምፓኒ መሆኑን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል። ለፍጻሜ ተፋላሚዎች ብቻ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። አሸናፊው ጉኬሽ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዬን ዶላር ሲሸለም ተሸናፊው ሊረን ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዬን ዶላር ሽልማት ተሰጥቶታል።
በስፖርት አፍቃሪያን በተሰበሰበ ድምጽ የ18 ዓመቱ ጉኬሽ በውድድሩ ምርጥ ብቃት ያሳየ ስፖርተኛ ተብሎ ተመርጧል። በአንፃሩ ቻይናዊው ሊረን ከባለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የአቋም መዋዥቅ አጋጥሞታል። ዲንግ ሊረን በእ.አ.አ በ2023 የዓለም ሻምፒዮና ከሆነ በኋላ ከፍተኛ ድካም እና ድባቴ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ተናግሯል። ይህንን ተከትሎም በወቅቱ በተከናወነው የእስያ ጨዋታዎች ላይ አልተሳተፈም። በ2024 የግራንድ ቼዝ ቱር ውድድርም እስከ አራተኛ ደረጃ እንኳ ይዞ ማጠናቀቅ አልቻለም።
አሸናፊው ጉኬሽ በዓለም አቀፉ የቼዝ ፌዴሬሽን ነጥብ አያያዝ በ17 ዓመቱ ከሁለት ሺህ 750 ነጥቦች በላይ የሰበሰበ ሁለተኛው በእድሜ ትንሹ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል። ጉኬሽ ገና በለጋ እድሜው ነበር ከቼዝ ስፖርት ጋር የተዋወቀው። ወጣቱ ኮከብ በቼዝ ታሪክ በ12 ዓመቱ “የዘርፉ ሊቅ” በሚል ተሞካሽቷል። ታዳጊው የቼዝ ስፖርተኛ በህንድ ታሚል ናዱ ግዛት በቼናይ ከተማ እ.አ.አ በ2006 ነው የተወለደው።
ገና በሰባት ዓመቱ የቼዝ ስፖርትን መጫወት እንደጀመረ የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። ታዳጊው ቼዝ እንዴት እንደጀመረ ሲጠየቅ ቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ ቼዝ ሲጫወቱ እመለከት ነበር። እናም ለዚህ ጨዋታ ፍላጎት አደረብኝ። ትምህርት ቤት ውስጥ ለመሰልጠንም ተመዘገብኩ፤ ከአሰልጣኛችን አንዱ ጥሩ ተሰጥኦ እንዳለኝ ነገረኝ ሲል ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
የቼዝ ተሰጥኦውን የተመለከቱት ሀኪም አባቱ እና ባዮሎጂስት እናቱ ሙሉ ትኩረቱን በሚወደው ስፖርት ላይ እንዲያደርግ ፈቀዱለት። እናም ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል በማቋረጥ የቼዝ ልምምድን የሙሉ ጊዜ ሥራው አደረገው። ቼዝ ብዙ ወራቶችን ወደ ውጪ ሀገር መጓዝ የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ አባቱ የልጁን ህልም ለማሳካት የህክምና ሥራውን አቁሟል። የልጃቸው የቼዝ ህይወት ይቃና ዘንድም ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች እንዲያማክሩት ይጠይቁ ነበር ተብሏል።
እ.አ.አ በ2017ም በዓለም አቀፍ መድረክ ለመሳተፍ የሚያስፈልገውን መስፈርት በማሟላት ከ12 ዓመት በታች ውድድር መሳተፍ ጀምሯል። ከዚያም በ2018 እአአ በዓለም ወጣቶች የቼዝ ሻምፒዮና እና በእስያ የወጣቶች ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል። ትንሹ ብላቴና በተሳተፈባቸው ሁሉም መድረኮች በዘርፉ አለቃ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። በ2022 በእስያ ጨዋታ ህንድ በወንዶች የቼዝ ቡድን የብር ሜዳሊያ ስታገኝ ታዳጊው የቡድኑ አካል እንደነበረ የሚታወስ ነው።
በዚሁ ዓመት በተደረገ 44ኛው የቼዝ ኦሎምፒያድ በቡድን የነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኝ በግሉ ምርጥ ብቃቱን በማሳየት የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ ወስዷል። ከውጤቱ በኋላም ከምንጊዜም የቼዝ ስፖርተኞች ውስጥ ስሙ በቀዳሚነት ተመዝግቧል። ይህም ላለፉት 37 ተከታታይ ዓመታት በሀገሩ ልጅ ቪስዋናታን ኢናን ተይዞ የነበረውን መግታት ችሏል። በዓለም ሻምፒዮና የጉኬሽ ዶማራጅ አስደናቂ ድል በቼዝ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሁለት የህንድ ግዛቶች መካከልም የጦፈ ክርክር አስነስቷል።
የ18 ዓመቱን ታዳጊ አንድራ እና ታሚናል ናዱ “የኔ ነው የኔ ነው” በሚል ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። በደቡባዊ ህንድ የሚገኙት ሁለቱ የህንድ ግዛት መሪዎች በኤክስ ገጻቸው በፍጥነት ወደ ኮከብነት የተቀየረውን ታዳጊ የራሳቸው ለማድረግ ሽሚያ ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳይ ጽሁፍ አስነብበዋል።
ልዩ የአጨዋወት ዘይቤው፣ አደገኛ እና ለተጋጣሚ ፈታኝ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንኳ የማይናወጥ ስሜትም እንዳለው ይነገራል። አፀፋዊ ጨዋታ ይጫወታል፤ በጊዜ ጫና ውስጥ ነገሮችን የማሰላሰል እና የማስላት ልዩ ችሎታም አለው፤ ለተጋጣሚ አስቸጋሪ የሆኑ ውስብስብ የጨዋታ ስልቶችን እንደሚፈጥርም የቢቢሲ መረጃ አመልክቷል።
ፍርሀት አልባ እና ደፋርም ነው፤ ለተጋጣሚዎቹም የተለየ ክብር ያለው የምስጉን ባህሪ ባለቤት ነው። ጉኬሽ ከቼዝ ልምምድ በኋላ በጥልቀት ያሰላስላል፤ ውሃ ዋና ስፖርት ይሠራል፤ ቴኒስም ይጫወታል። አላማው የወቅቱ ቁጥር አንድ የሆነውን ማግነስ ካርልሰንን በመተካት የዓለም ቀዳሚው የቼዝ ስፖርተኛ መሆኑን ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም