ጥሩ ወይስ መጥፎ፤ ጨለማ ወይስ ብርሀን፤ ሰላም ወይስ ግጭት? ዓለም ሁለት በተቃርኖ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ይዛለች:: ትኩረትህ የህይወትህን አቅጣጫ ይወስነዋል:: “ልብ ካላየ ዓይን አያይም” የሚለው የአበው አነጋገር እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነው:: ልብ ማስተዋያ ነው:: ልብህ ክፉን ከደግ መርምሮ ይይዛል:: ዓይን መመልከቻ መሳሪያ እንጂ ዋናው መርማሪው ልብ ነው:: ልብህ የሚሻውን ዓይንህ ይመለከታል:: ልብህ ደግሞ ከአዕምሮህ ጋር በእጅጉ የተቆራኜ ነው:: አእምሮህ የሚያተኩርበትን ልብህ ይመረምረዋል፤ ይመዝነዋል:: ማሽተት፤ መቅመስ፤ መዳሰስ፤ መመልከት፤ ማድመጥ የስሜት መሳሪያዎችን ይጠቀማል::
ዓለምን እንዴት ነው የምትመለከታት የሚለው የሕይወትህን ፍሬ ይወስነዋል:: ሁለት ዓይነት አተያዮች አሉ:: ጥቂት ሰዎች ዓለምን መልካም፤ የደስታ ሜዳ፤ የሳቅ ምንጭ አድርገው ይመለከቷታል:: ብዙኀኑ ግን ዓለም የጦርነት߹ የግጭት߹ የመፈናቀል እና የመጥፎ ነገር መፍለቂያ አድርገው ይመለከቷታል:: ሰው በምልከታው ይወድቃል ወይ ይነሳል:: ስለዚህ ምልከታህ ምንድን ነው? በተፈጥሮ የሰው ልጆች ለአሉታዊ ነገሮች የማዘንበል ልማድ አላቸው:: አንድም የቀደመ ጠባሳ እና ያለፉት መጥፎ መስመር ሊሆን ይችላል:: ሁለትም አሸናፊ በሚኖርባት ዓለም ውስጥ ሲኖሩ ከመጥፎ ነገሮች ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የግድ ለአሉታዊ ነገሮች ትኩረት እንዲሰጡ ይገደዳሉ::፡ ጥንቃቄ ለማድረግ ከመከራ መማር እንዳለባቸው በሕይወታቸው ያያሉና::
ሳይኮሎጂ ቱዴይ ድረገጽ የሚዲያ ተቋማት የሰው ልጆች ዓለምን በሸውራራ መልኩ መጥፎ አድርገው እንዲመለከቷት ከፍተኛ ሚና መጫዎታቸውን በአብነት ያነሳል:: የሚዲያ ተቋማት አሉታዊ ነገሮችን ደጋግመው ማቅረባቸው የስርዓት እና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የዲሞክራሲ ጠበቃዎች ነን ብለው በማሰባቸው ነው:: እንዲያውም የሚዲያ ተቋማት ከሶስቱ የመንግሥት አካላት ከህግ አውጪ߹ ህግ ተርጓሚ߹ ሕግ አስፈጻሚው ቀጥሎ አራተኛ መንግስት ነን ብለው ያስባሉ:: ይህንን ስልጣናቸውን ለመጠቀምም ሲሉ ጉድለት߹ ብልሽት߹ ጦርነት߹ መፈናቀል߹ አደጋ እና ሌሎች መሰል አሉታዊ ጉዳዮችን ይዘግባሉ::
የወንጀል መቀነስ በብዙ ሀገራት በዘገባነቱ ተነስቶ አያውቅም:: ብዚ ሺህ ሰዎች በሰላም ከቤታቸው ወደ ስራ ቦታ ገብተዋል፤ ይህ ግን ለሚዲያ ጉዳዩ አይደለም:: አንድ መኪና መስታዎቱ መሰበሩ ዜና ይሆናል:: በሚሊዮን የሚቆጠሩ የባንክ ሰራተኞች ሀቀኞች ናቸው:: አንድ ሰራተኛ መስረቁ ግን ዜና ሆኖ ይነገራል::
የሰዎችን ለአሉታዊ ሀሳቦች ማዘንበል እንደ መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የሚዲያ ተቋማት ግጭት߹ ጦርነት߹ ኪሳራ߹ መፈናቀል߹ የጎርፍ አደጋ߹ ብሄር ግጭት߹ እና ሌሎችንም ርእሰ ጉዳዮች በዘገባነት ይጠቀሙባቸዋል:: እንከን እና ጉድለትን ነቅሰው በመዘገብ ገንዘብ ይሰሩባቸዋል:: ለዚህ ደግሞ የዘመኑ ማህበራዊ ሚዲያ አንዱ ተጠቃሽ ነው:: ሁልጊዜ ሰበር ሰበር እያሉ አሉታዊ አስተሳሰቦችን እንድታዳብር ይነግሩሃል:: መልካም ነገሮች ሲሰሩ አያዩዋቸውም:: ምልከታቸው አሉታዊ ነገሮች ማሰሰስ ላይ ያተኩራል:: በሌላ በኩል ደግሞ አዎንታዊ ወይም መልካም ነገሮች ብቻ የሚዘግቡት ሚዲያ የህዝብን እልቂት እና ሰቆቃ አያዩትም::
የሰው ልጆች የሚገነቡት በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች ነው:: የእምነታችን እና የአመለካከታችን ውጤቶች ነን:: የምንሰማው߹ የምናየው߹ የምንመለከተው ነገር ዓለምን የምናይበትን ዕይታ ይለውጠዋል:: ለዚህ ነው ከምንሰማው እና ከምናየው ነገር መጠንቀቅ ያለብን:: ብዙ ሰዎች በሰሙት እና ባዩት ተመርዘዋል:: እናም በሕይወታቸው ተስፋ ማጣት እና አሉታዊ ሀሳቦች ያጠቋቸዋል:: የሚቀዱበት ምንጭ ጤናማ ባለመሆኑ እነሱም ጤና ይርቃቸዋል:: ሳይኮሎጂ ቱዴይ ዓለምን ጨካኝ߹ አረመኔ߹ የአደጋ እና የግጭት ቦታ አድርገን የምናስባት ከሆነ ድምዳሜያችንም ጨካኝ እና አሉታዊ ይሆናል፤ ፍርሃት߹ ጥርጣሬ እና ስጋት ያድርብናል ይላል:: በተቃራኒው ዓለም የሰላም߹ የደስታ እና የመልካም እድሎች ቦታ ናት ብለን የምናስብ ከሆነ ሙሉነት ይሰማናል:: አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር እና እድሎችን ለመጠቀም የማንሰጋ እንሆናለን ብሏል::
ስለዚህ የትኛው ትክክል ነው ትላለህ? ከመጥፎ እና ከጥሩ የትኛውን ትመርጣለህ? ምርጫው የአንተ ነው:: የሰብእና ግናባታ߹ የህይወት ክህሎት߹ አሰልጣኝ እንዲሁም ደራሲ ታህሚድ ቾውድሃሬ “የሰው ልጅ ዓለምን የሚያይበትን አተያይ ለመለወጥ እንደሚያደርገው ዓይነት ከባድ ለውጥ የለም ”ይላል:: ቢሆንም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ዓለምን የመረዳት ጥበብ ማዳበር የመጀመሪያው ሂደት መሆን አለበት ይላል:: ዓለም ላይ ያሉ እውነታዎች በሰው ልጆች አኗኗር߹ በሚዲያ߹ በገጠመኝ߹ በፊልም߹ በወሬ߹ በቤተሰብ በትምህርት እና በሌሎች መሳሪያዎች ተለውጠዋል:: ብርሃናማውን ዓለም በአንዲት ቅጽበት ጨለማ ፤ የዘላለም ጨለማ አድርገን እንድናስብ ተደርገናል:: ሙለውን ጓዳችንን ጎዶሎ ሆኖ እንዲታየን ተሰርቶብናል:: ብዙ ሰላም እያለ ሚዲያው ጦርነት ላይ አተኩሮ መረጃ ይግተናል:: ብዙ ምርጥ ትዳሮች እያሉ አንድ የፈረሰ ትዳር በልቦናችን ውስጥ እንዲሰነቀር ይደረጋል:: መንቃት እና ነገሮችን ከውጤታቸው አንጻር መምረመር ታህሚድ ልንከተለው የሚገባ ጉዳይ ነው ይላል:: ነገሮች ከምን አንጻር እየተሰሩ እንዳሉ ማወቅ መዳኛው መንገድ ነው::
ላይፍስ ኖት ቡክ ገጽ አርተር እና ሊዛ የተባሉ ባል እና ሚስት ልጆቻቸውን በዓለም ብቁ እና ጠንካራ አድርገው ለማሳደግ ሲጨቃጨቁ ያስነብባል:: በዚህም አርተር ልጆች ዓለምን መጥፎ አድርገው ማየት አለባቸው ይላል:: በአንጻሩ ሊዛ ደግሞ ዓለምን መልካም አድርገው ማየት አለባቸው ትላለች:: በዚህ ሀሳብ መግባባት አልቻሉም:: (ፕራይማል ፋክተርስ) ስር ሰደድ ምክንያቶች ለሁለቱም ባል እና ሚስቶች ክርክር መነሳዎች ሆነዋል:: ያደጉበት እና እነሱ ዓለምን የሚረዱበትን መንገድም ለሚወዷቸው ልጆች ማስተላለፍ ይፈልጋሉ:: የህይወት መረዳታቸው በእነሱ የሚቀር አይደለም፤ ወደ ትውልድም የሚተላለፍ እንጂ::
አንድ ቀን ባል እና ሚስት በእግር እየተጓዙ አየሩን እያጣጣሙ ነበር:: ከፊት ለፊታቸው የሚመለከቷቸውን አበባዎች ቀለም በመለየት አልስማማ ይላሉ:: ሚስት ብርቱካናማ ቀለም ነው የማየው ትላለች:: ባል ደግሞ ፐርፕል ቀለም ነው ይላል:: ሚስት ባሌ ተሳስቷል ብላ ተከራከረች:: እናም በተሟሟቀ ክርክር ውስጥ ሳሉ ባልየው መነጽርሽን አውልቂው ብሎ እጁን ጠቆመ:: መነጽሯን ስታወልቅ አበባዎቹ ቀለማቸው ፒንከ ነበር::
ላይፍስ ኖት ቡክ ገጽ “ሁላችንም በቀደመው እድሜያችን የገዛነውን የሕይወታችን መነጽር አድርገናል::ይህ መነጽር ነገሮችን በትክክለኛ ማንነታቸው እንዳንመለከት አድርጎናል” ሲል ጽፏል:: ይህ መነጽር የመጥፎ ሕይወት ልምድ ነው:: እነዚህ ልምምዶች አድገው ጠቅላላዊ የህይወት መርሆቻችን ይሆናሉ:: “ደሀ መጥፎ ነው፤ ጋብቻ ስቃይ ነው፤ እኔ ለዚህ ስራ አልመጥንም” የሚሉ ሀሳቦች ወደ መርህነት ያድጉና በአኗኗራችን ላይ ጥላሸት ይሆናሉ:: በልጅነታቸው ስናድግ የሰበሰብናቸው መረጃዎችን ለዛሬ ኑሯችን ስበን እናመጣቸዋለን:: አትችልም ሲባል ያደገ ልጅ ትንሽ ነገር ሞክሮ ካልተሳካለት ደደብ ነኝ ማለት ነው ብሎ ከኋላ ታሪኩ የልጅነት ሰነድ ማረጋገጫ መምዘዝ ይጀምራል:: አልችልም የሚልን ግዙፍ ጎታች የህይወት መርህ ወደ እችላለሁ መቀየር ይከብዳል እንጂ የተከለከለ አይደለም:: አደናቃፊ የከረሙ ሀሳቦችን መለየት ወደ ፊት ለመራመድ መልካም ነው:: ለነገሮች ያለን ዕይታ ሲለወጥ ሕይወታችን ይለወጣል::መስመራችን ይቃናል::
ዓለምን መልካም አድርገን ስንቀበል ሙሉ አቅማችንን ለመጠቀም እንችላለን:: ሀሳብ߹ ስሜት߹ ድርጊት߹ ውጤት ሁልጊዜም በመጥፎም ይሁን በመልካም ዕይታችን ውስጥ አሉ:: የምናስበው ወደ ስሜታችን ይጋባል፤ ስሜታችን ደግሞ በድርጊታችን ላይ ተጽእኖ አለው:: ድርጊታችን ውጤታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ይወስናል:: አንዱ ከሌላው ጋር በእጁጉ የተሳሰሩ ናቸው:: ለምሳሌ በጠዋቱ ቀኑ ደባሪ ነው ብለህ አስብ:: ደባሪ የሚለው ሀሳብህ ወደ ስሜትህ ተሰራጭቶ ይደብርሃል፤ ፊትህ ጭፍግግ ይላል:: ቀጥለህ ስሜትህ ጥሩ ባለመሆኑ የምትሰራውን ስራ ለመጀመር ትቸገራለች:: ቡና ብትጠጣ߹ ሻይ ብትደግም߹ ቦታ ብትቀይር ለመጀመር በጣም ትቅበጠበጣለህ:: ሰው ጋር ትጋጫለህ:: ክፉ መናገር ትጀምራለህ:: እንጀራየ ነው መቼም ብለህ ስራውን ትጀምረዋለህ፤ ትናንት እንደነበረው ዓይነት አትሰራም:: በመሰላቸት የጀመርከው ስራ ውጤቱ እዚህ ግባ የማይረባ ተራ ይሆናል:: በአንጻሩ ቀንህን በመልካም ቃል ብትጀምረው ሊሆን የሚችለውን ገልብጠህ ተመልከተው:: መድከምህ ካልቀረ߹ መኖርህ ካልቀረ߹ በምድር ላይ በደስታ ኖሮ ማለፍ፤ ዓለምን በአዎንታዊ መልኩ ተረድቶ መልካም ፍሬዋን መብላት አይሻልም ? ምርጫው ያንተ ነው:: “መረረኝ እንደ እሬት” የሚለው ቀረርቶ ማንን ሲለውጥ አይተሃል? ብሶት ራሱን ይወልዳል߹ ደስታ ራሱን ይልዳል:: የምታዋልደውን መለየት ከአንተ ይጠበቃል::
ፍራንክ ሶኔንበርግ ድረገጽ የሰው ልጆች ዓለምን ለመረዳት ሊጠቀሙባቸው ይገባል የሚላቸውን ሓሳቦች አስፍሯል:: እናንተ ከየትኛው ወገን እንደሆናችሁ መመርመር ይበጃል ሲል:: ዓለም ብዙ የምትሰጠው አላት፤ መርጣችሁ ለመውሰድ የሰዎችን የእሳቤ መንገድ መረዳት ተገቢ ነው ይላል:: የመጀመሪያው የአዕምሮ ማጣራት አቅም ሁሉጊዜ በሰዎች አቅም ይወሰናል:: አንዳንዶቹ የራሳቸውን ብቻ ትክክል አድርገው የሌላውን ስህተት ነው ብለው በማመን ተቸክለዋል:: ጥቁር ወይ ነጭ ብቻ የሚሉ ሰዎች ይገጥሙሃል:: ከመሐል ምንም ነገር የለም ብለው ግትር ይላሉ:: አንደኛው ጫፍ ላይ ብቻ የሚቆሙ ሰዎች አሉ:: ማጠቃለል ደግሞ የሚወዱ ሰዎች አሉልህ:: አንድ ሰው ወስደው እገሌ አካባቢ ጀግና ነው ይሉሃል፤ የእገሌ ሰፈር ሰዎች የፍቅር ሰዎች ናቸው ይላል:: አንድ መምህር ሰነፍ ከሆነ መምህር ሰነፍ ነው ብለው ይከራከሩሃል:: የሰው ልጆች በፍረጃ ያስባሉ:: በቡድን ወይም በማንነት ወይ በባህሪ ይፈርጁሃል:: ድምዳሜ ሌላው ዓለም የሚመራበት ህጉ ነው:: ምንም ማስረጃ ሳይኖር ሰዎች ይደመድማሉ::
የሰው ልጆች ማጋነንን እንደ አስተሳሰብ መሳሪያ ይጠቀማሉ:: ከሚገባው በላይ ያገዝፉታል ወይም ያንኳስሱታል:: ከተሳሳትሁ በቃ አለቀልኝ ብሎ ማሰብ:: አንድ መስመር ብቻ ነው ትክክል ብሎ ማሰብም እንዲሁ የተለመደ ነው:: እነዚህ ሰዎች እነሱ ካሰቡት ውጪ ሌላው ገደል የሚከት ነው:: ይገባኛል ማለትም ሌላው የሰዎች እሳቤ መንገድ ነው:: በቃ እኔ በልዩነት ይገባኛል ብሎ ማሰብ፤ የእኔ ብቻ ነው አሪፍ ብሎ የራስን ማጉላት እሳቤ አለ:: የእኔ ልጅ የቆንጆዎች ቆንጆ ናት እንደሚል ሰው ዓይነት:: የጥቃት ሰለባነት እሳቤ፤ ሰዎች ብቸኛ እና ከንቱ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ሊያደርጋቸው ይችላል:: በሰለባነት ማሰብ የተለመደ ነው:: አእምሮ አነብባለሁ የሚሉም ሰዎች አሉ:: ሌሎች ምን እንደሚያስቡ አውቃለሁ ይላሉ߹ ግን አንድም አያውቁም:: ሰው ሁሉ የሚከዳቸው የሚመስላቸው ብዙዎች አሉ:: ለዚህም ዓለምን ከሀዲ አድርገው ይቆጥራሉ:: ሰው ማመን መጥፎ ነው ይላሉ:: ወቀሳ ቀጥሎ የሚመጣው የእሳቡቤ መንገድ ነው:: ለሆነባቸው ነገር ሁሉ ሰዎችን የሚወቅሱ አሉ:: በሌላ በኩልም ሌሎች ላይ ለሚሆነው ነገር ሁሉ ራሳቸውን እንደ ክርስቶስ ጠበቃ አድርገው ወስደው ለጥፋቱ ራሳቸውን የሚወቅሱ አሉ:: ራስን መጠራጠርም አለ:: አሸንፈው ሽልማቱ አይገባኝም ነበር የሚሉ አሉ:: አቅማቸውን ይክዱታል:: ሁልጊዜ ትክክል ነኝ የሚሉ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችም በዙሪያችን ያጋጥሙናል::
ፍራንክ ሶኔንበርግ ከላይ የቀረቡትን የአስተሳሰብ መንገዶች ዓለምን የምንረዳበትን መንገድ ይቀይሩታል:: ያስተካክሉታል ወይም ያዛቡታል:: የተጠቂት ስሜት ያለበት ሰው ጋር ስንሆን ፍርሃት እና ጥርጣሬን ያጋባብናል ይላል:: በስሜታችን߹ በውሳኔያችን߹ በአረዳዳችን እና የህይወት መርሃችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖም ያሳድርብናል:: ሁላችንም የግንዛቤያችን ውጤቶች ነን የሚባለው ለዚህ ነው:: እናስ ዓለምን እንዴታ ታያታለህ?
(አቢብ አለሜ)
በኲር የታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም