ጥር እና ቱሪዝም

0
223

በ2012 ዓ.ም የተከሰተው ዓለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት፣ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አማራ ክልል የተከሰተው ውስጣዊ ግጭት የክልሉ ጸጋ የሆኑት ሁሉም የመስህብ ሐብቶች በሚፈለገው ልክ ጎብኝዎችን እንዳይስቡ እክል ሆነው ዘልቀዋል:: የሰሜኑ ጦርነት ለቱሪስት መስህብነት የተፈጠሩትን የተራራ ሰንሰለቶች የጦርነት አውድማ በማድረግ የመስህብ ቦታዎች የደህንነት ስጋት እንዲጋረጥባቸው ማድሩን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የ2015 ዓ.ም መረጃ ያመላክታል::

ክልሉ ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በፊት 207 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን የመሳብ አቅም እንደነበረው የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል:: በ2016 ዓ.ም 20 ሺህ የውጭ ሀገር እና ስምንት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ሐብቶችን ጎብኝተዋል::

ቱሪዝሙ የሚፈጥረው የሥራ ዕድል መቀዛቀዙን ተከትሎ በሕጋዊ መንገድ በተናጠል ወይም በመደራጀት መተዳደሪያቸው ጎብኝዎችን በማጓጓዣ፣ በሆቴል፣ የሰጦታ እቃዎችን  በመሸጥ ጓዛቸውን  በበቅሎ በማድረስ፣ መንገድ በመምራት…   ያደረጉ  ወገኖች ዛሬ ላይ የክልሉን ሰላም መሆን አብዝተው እየጠየቁ ነው:: ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ዛሬም ድረስ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ተቆጥሯል:: የክልሉ መንግሥት የክልሉን ሰላም ወደተሟላ ሁኔታ ለመቀየር እየተሠራ ካለው ሥራ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እና ሌሎች የክልሉን ገቢ የሚያሳድጉ ተግባራት እንዲሠሩ እያደረገ ነው:: ያለንበት ወቅት ደግሞ የክልሉ ገጽታ መገንቢያ ጊዜ ነው::

ክልሉ በልዩ እና ውብ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው የብዙኃኑን ቀልብ መሳብ በሚችሉ በስው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስእብ ሀብቶች የታደለ ነው:: ከዚህም ባሻገር ከታህሳስ 29 ቀን ጀምሮ በየዓመቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት እና የባሕላዊ ትውፊት ክዋኔዎች ለበርካታ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች መናኸሪያ እንዲሆን ያደርጉታል:: ለቀጣይ የቱሪዝም እንቅስቃሴው መነቃቃትም የጎላ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ይታመናል::

ገናን በላልይበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር እና ኢራንቡቲ፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ መርቆርዮስን በደብረታቦር፣ የአገው ፈረሰኞች ዓመታዊ በዓል እና ሌሎችም የአማራ ክልል የወርሀ ጥር በረከቶች ናቸው:: ታዲያ ክልሉ በየዓመቱ ይህንን ወቅት ለክልሉ ገጽታ ግንባታ እና ለቀጣይ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት እንደ መሳሪያ ይጠቀመዋል:: ዘንድሮም እነዚህ በዓላት እና ክዋኔዎች በልዩ ድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅቶች እየተደረጉ፣ ለጎብኝዎችም ጥሪ እየተደረገ ይገኛል::

ሃይማኖታዊ በዓላትን እና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለመታደም እንዲሁም በከተማዋ የሚገኙ የመስህብ ሐብቶችን ለመጎብኘት በርካታ ጎብኝዎች በወርሀ ጥር በታሪካዊ የጉዞ መስመር ላይ የምትገኘውን ባሕር ዳርን ዋና መዳረሻቸው ያደርጋሉ:: የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም መምሪያም ወሩን ባሕር ዳርን ለማስተዋወቅ፣ ለከተማ ገጽታ ግንባታ እና የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት ማስመስከሪያ አድርጎ ለማለፍ ከወዲሁ በልዩ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ::

እንደ ከተማ አስተዳደሩ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ከተማዋ ያሏትን ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሠራሽ እና ሃይማኖታዊ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በሚፈለገው ልክ ለጎብኝዎች ለማስተዋወቅ ጥርን በባሕር ዳር ክብረ በዓላት ትልቅ ትርጉም አላቸው:: በዘንድሮው ጥርን በባሕር ዳር መርሀ ግብር በርካታ ሁነቶች ይዘጋጃሉ:: ባሕር ዳር ውብ ሆና እንግዶቿን እንድትቀበል በሁሉም ክፍለ ከተሞች የጽዳት ዘመቻ እንደሚከናወን ታውቋል:: የተቀዘቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የንግድ እና ባዛር ትርኢት እንደሚከፈትም ተመላክቷል::

የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የክልሉ ሕዝብ የሚገለጽበት ባሕላዊ የገና ጨዋታ ክዋኔ የጥርን በባሕር ዳር መክፈቻ ሁነት እንደሚሆን አቶ ጋሻው ጠቁመዋል:: የባህል እና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል የክልሉን ሕዝብ ወግ እና ባህል በሚያስተዋውቅ አግባብ በከፍተኛ ድምቀት እንደሚዘጋጅም ተጠቁሟል::

የቱሪዝም መዳረሻ መሰረተ ልማት ጉብኝት ሌላው የጥርን በባሕር ዳር አንዱ አካል ነው። የከተማዋ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለቱሪዝም የተመቸ ሆኖ መከናወኑን አቶ ጋሻው ገልጸዋል። ለአብነትም አዲሱን የዓባይ ወንዝ ድልድይ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን አንስተዋል። የባሕረ ዳር ታሪክ አንዱ መታወቂያ ብስክሌት ነው ያሉት አቶ ጋሻው፣ ይህንን የታሪክ መገለጫ ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል የኮሪደር ልማት ሥራው ትልቅ እቅም እንደሚሆን አመላክተዋል። በዘንድሮው የጥርን በባሕር ዳር መርሀ ግብርም የብስክሌት ሽርሽር ይካሄዳል::

በጣና ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት ውስጥ በተፈጥሮ አቀማመጡ ልዩ የሆነው የእንጦስ እየሱስ ገዳምን ተፈጥሯዊ የቦታ አቀማመጥ ለጉብኝት እንደሚውልም ታውቋል:: ይህ ስፍራ በገዳምነቱ ከመጎብኘቱ ባሻግ የቦታ አቀማመጡ የአሳ፣ የመርከብ እና የልብ ቅርጽ ያለው መሆኑን ለማሳወቅ ይጎበኛል::

የጥምቀት ከተራ በዓልን በከተማ አስተዳደር ደረጃ ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት እንዲዘጉ በማድረግ በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። የቃና ዘገሊላ፣ የአቡነ ዘራብሩክ፣ ሰባሩ ጊዮርጊስ እና አስተርዮ ማርያም በዓላትን በልዩ ድምቀት በማክበር ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ለማዋል ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተመላክቷል:: የታንኳ ቀዘፋ ትርኢት የጥርን በባሕር ዳር ልዩ ድምቀት ሆኖ ይሠራበታል:: የፈጠራ ምርቶች ለኤግዚቢሽን ይቀርባሉ::

የከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ መነቃቃት እየታየበት መሆኑን አቶ ጋሻው አስታውቀዋል:: ዘንድሮ የሚዘጋጀው የጥርን በባሕር ዳር ፕሮግራም ደግሞ በከተማው ያለውን የንግድ መቀዛቀዝ እና የማኅበዊ መስተጋብር መፋዘዝ የበለጠ ለማነቃቃት ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው ጠቁመዋል:: ከጫማ ማሳመር ጀምሮ እስከ ሆቴሎች ድረስ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት በመሆኑ ፋይዳውን ያጎላዋል ብለዋል:: በመሆኑም የጥርን በባሕር ዳር መርሀ ግብር ለሕዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በበዓሉ ከመሳተፍ ጀምሮ የእንግዶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ከዚህ ቀደም ይታወቅበት የነበረውን የእንግዳ አያያዝ እሴት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል አሳስበዋል::

እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እያጋጠሙ ያሉ የጸጥታ ችግሮች የቱሪዝም ዘርፉ እንዲፈተን ማድረጋቸውን የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ተናግረዋል:: ዳይሬክተሩ ማሳያ አድርገው ያነሱት ክልሉ በ2011/12  ከቱሪዝም ዘርፉ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው:: በ2016 ዓ.ም ግን ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ብቻ ማግኘት የተቻለው ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አቶ መልካሙ ገልጸዋል:: በዚህ ቁጥራዊ አኃዝ መሠረት ክልሉን ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ከቱሪዝም ዘርፉ ብቻ ከ865 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አሳጥቶታል ማለት ነው::

እንደ አቶ መልካሙ ክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት በፊት 10 ሚሊዮን ለሚሆኑ ጎብኝዎች መዳረሻ ነበር:: በ2017 ዓ.ም ግማሽ ዓመት አምስት ሚሊዮን ጎብኝዎችን ለመሳብ በዕቅድ ተይዧል:: በሩብ ዓመቱ በተጨባጭ ማሳካት የተቻለው ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝን ሲሆን ከዚህም  ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል:: ስድስት ሺህ 338 የውጭ ሀገር ጎብኝዎችም የክልሉን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በመጎብኘታቸው ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል::

በክልሉ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ለተቀዛቀዘው የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል:: የልደት በዓል በላልይበላ፣ የጥምቀት በዓል በጎንደር እና ምንጃር ሸንኮራ (ኢራንቡቲ) እንዲሁም ሌሎች ክልሉ የሚታወቅባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት እና ባሕላዊ ክዋኔዎችን በድምቀት ለማክበር እንደ ክልል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ መልካሙ ጠቁመዋል:: ላልይበላ እና ጎንደርን ጨምሮ በዓላቱ በሚከበርባቸው አካባቢዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም በርካታ ታዳሚዎች ወደ ክልሉ እንዲገቡ የሚቀሰቅሱ የማስታወቂያ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ  14 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here