የጋላፓጎስ ብሔራዊ ፓርክ

0
129

የጋላፓጎስ ብሔራዊ ፓርክ በፓስፊክ ውቅያኖስ፣ በደቡብ አሜሪካ ከምትገኘው ኢኳዶር 1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው:: ፓርኩ 19 ደሴቶችንም አቅፏል:: የፓርኩ  መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሦስት የባህር ላይ የዓየር ሞገዶች መገናኛ  ቦታ ላይ መሆኑ በብዝሃ ህይወት የበለፀገ ልዩ ቀጣና አድርጐታል::

ደሴቶቹ አንዱ ከሌላው የተራራቁ እና የማይገናኙ መሆናቸው ለብርቅዬ እንስሳት እና እፅዋት  መገኛነታቸው  ተጠቃሽ ምክንያት ነው::

በኢኳዶር ስር የሚተዳደሩት የጋላፓጎስ ደሴቶች ጠቅላላ ስፋታቸው 7,995 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: ደሴቶቹ 45 ሺህ ኪሎሜትር ስኬዌር ስፋት በተንጣላለው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ቀደም ባሉት ዘመናት በተከሰተ እሳተ ገሞራ እንደጌጥ ተራርቀው የተፈጠሩ ናቸው::

በ1835 እ.አ.አ ቻርለስ ዳርዊን ለተሰኘው ተመራማሪ ደሴቶቹን የመመልከት እድል በማግኘቱ በዘመኑ ለፃፈው የዝግመት ለውጥ ፅንሰ ሀሳብ “survival of the fittest’’ መነሻ እና ማስረጃ ሆኖታል::

ከ1967 እስከ 1971 እ.አ.አ የደሴቶቹ ቀጣና በፓርክነት ቢመሠረትም እውቅና አግኝቶ በዓለም አቀፍ አካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት /UNESCO/በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው በ1979 እ.አ.አ ነው::

ከደሴቶቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በከፍታ ቀዳሚው 1707 ሜትር የተለካው በኢዛቤላ ደሴት የሚገኘው ቮልካን ዎልፍ ተራራ ነው:: የኢኳዶር መንግሥት 97 በመቶ የሚሆነውን የደሴቶቹን መገኛ ቀጣና በብሄራዊ ፓርክነት ጥበቃ እንዲደረግላቸውም ደንግጓል::

በደሴቶቹ ኗሪዎች የሚበዙባቸው ኢዛቤላ፣ ባልትራ፣ ሳንክሪስቶቦል እና ሳንታክሩዝ የተሰኙት ሦስት በመቶ የቆዳ ሽፋንን ይዘዋል:: በፓርኩ ከሚገኙ የዱር እንስሳት ግዙፍ ኤሊዎች፤ ከአእዋፍ- “አልባትሮስ”፣ ጭልፊት፣ “ፒንጉዊን” እንዲሁም ዓሣ ነባሪ፣ የባህር አንበሳ ዝርያዎች ተጠቅሰዋል:: ለፓርኩ የጥበቃ አካል ተቋቁሞለታል:: ዓላማው ደግሞ በደሴቶቹ እና በሚገኙበት የውቅያኖስ ክልል የእንስሳት ዝርያዎችን ለመጠበቅ ነው::

የፓርኩ አስተዳደርም ጐብኚዎች በፓርኩ ላይ የሚያደርሱትን ተፅእኖ ለመቀነስ ደንቦችን አዘጋጅቷል:: ከደንቦቹ መካከል በደሴቶቹ በተዘጋጁ ሆቴል ቤቶች ለማረፍ እና ተንቀሳቅሶ ለመጐብኘት ለአዋቂዎች 200 ዶላር ለታዳጊዎች 100 ዶላር እንደሚያስከፍል በማደማደሚያነት ለንባብ በቅቷል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ ዶት ኦርግ፣ ዩኔስክ ዶት ኦርግ፣ ዲስከቨር ጋላፓጐስ ድረገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here