ፈጣኑ ሮቦት

0
108

በደቡብ ኮሪያ በውሻ አምሳያ የተሰራው ሮቦት አንድ ጊዜ በተሞላ ባትሪ ማራቶንን በአራት ሰዓት ከአስራዘጠኝ ደቂቃ በማጠናቀቅ የመጀመሪያው ሆኖ መመዝገቡን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

“ራይቦ2” የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ሮቦት በደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም የተመረተ ሲሆን “ሳንግጁ” 22ኛው የማራቶን ውድድርን በተሻለ ሰዓት በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችሏል:: ሮቦቱ 47 ኪሎግራም ነው የሚመዝነው:: ለክብደቱ መጨመር በአንድ ጊዜ ርቀቱን ማጠናቀቅ የሚያስችለው ባትሪ የተገጠመለት መሆኑ ነው በምክንያትነት የተጠቆመው::

ሮቦቱ የሚሮጥበት ቀጣና አቀበት ቁልቁለት ያለው  ነው፤  ሮቦቱ ቁልቁለት ሲሮጥም የሚመነጨውን ኃይል በማከማቸት አቀበት ላይ እንዲያውለው ተጠበውበታል- ባለሙያዎቹ:: የኃይል አጠቃቀሙ በሰውሰራሽ ክሂሎት (AI) የማመጣጠን ተግባር እንዲከወንም ተደርጓል:: በሮበቱ ላይ የተገጠሙት  ዳሳሾች ወይም (sensor) ከፊት ለፊት በተገጠሙ ሁለት የምስል ማንሻ ካሜራዎች  ነው የሚደገፉት::

ሮቦቱን በማምረት ሂደት የተሣተፉት ባለሙያዎች በሩጫው ወቅት ከሌሎች ጋር እንዳይጋጭ ርቀቱን ጠብቆ እንዲጓዝ፣ ኃይል እንዲቆጣጠር የተቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውም ነው የተገለፀው::

ቀደም ባለው ጊዜ በተመሣሣይ ተመርቶ ለሩጫ ውድድር የተሳተፈ ሮቦት 32 ኪሎ ሜትር ላይ ማጠናቀቁን ያስነበበው ድረ ገጹ የነበሩ ህፀፆች ተገምግመው በመታረማቸው “ራይቦ2” የተፈለገውን ውጤት ማምጣቱን ነው ያሰመሩበት ተመራማሪዎቹ::

አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ከአንድ መቶ ዘጠና አምስት ሜትር ርቀትን በአራት ሰዓት ከሃያ ደቂቃ አንድ ጊዜ ብቻ በተሞላ ባትሪ ያጠናቀቀው “ራይቦ2” ሮቦት በባለሙያዎች የተደረገለት የማሻሻያ ስራ እስከ 67 ኪሎሜትር ርቀት መሮጥ እንደሚያስችለውም ነው እማኝነታቸውን የሰጡት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here