መደበኛው የግብርና ሥራ በመገባደድ ላይ ነው፤ ይህን ተከትሎ ታዲያ የበጋ መስኖ ሥራ እንቅስቃሴ ተጀምሯል:: በኩኵር በስልክ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን:: የሚጠበቅባቸውን እየሠሩ መሆኑን በማንሳትም ግብዓት በወቅቱ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል::
በመሬት ዝግጅት ረገድ አስፈላጊውን ተግባር እየከወኑ መሆኑን የገለፁልን በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓንጓ ወረዳ ጥሩ ብርሃን ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሙሉቀን ደስታ ናቸው፤ በአካባቢያቸው ባለው የብር ጥምብል በተባለው ወንዝ ያለውን ግድብ በመጠቀም በመስኖ በርበሬ፣ ሽንኩርት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ስንዴ በማምረት ከበፊቱ የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግዋል:: በሌላ በኩል በየዓመቱ የግብዓት ፍላጎታቸው እየጨመረ መሄዱን ያነሱት አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር (በዋናነት ስንዴ) እና የአፈር ማዳበሪያ በበቂ መጠን በወቅቱ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል::
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጓንጓ ወረዳ እንጓይ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አልጋነው አካል ባለፈው ዓመት አርዲ ወንዝን በመጥለፍ ድንች፣ በርበሬ እና ስንዴን በኩታ ገጠም በማምረት ከአንድ ሔክታር መሬት 15 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል:: አርሶ አደሩ እንዳሉት ለበጋ መስኖ የግብርና ሥራ በትኩረት መሥራታቸው ተጠቃሚነታቸውም ጨምሯል:: በዘንድሮው ዓመትም የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ ነው፤ የሚመለከተው ባለ ድርሻ አካል ደግሞ የባለሙያ እገዛን ጨምሮ ግብዓት በወቅቱ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል::
በሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብር እና ዋዩ ወረዳ ወሌ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አሥራት ጌቶ የበጋ መስኖ ሥራን በተመለከተ ሐሳባቸውን ለበኵር በስልክ አጋርተውናል፤ አርሶ አደሩ እንዳሉት በሮቢ ወንዝ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ስንዴን በኩታ ገጠም እያመረቱ ነው:: ለዘንድሮው የመስኖ ሥራም የሚጠበቅባቸውን እየከወኑ ይገኛሉ:: ይሁን እንጂ ወደ አካባቢው የመጣላቸው አምስት የውኃ መሳቢያ ጀኔሬተር ብቻ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ጠይቀዋል:: ችግሩ ከተፈታላቸው ደግሞ ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል::
ከመኸር ሰብል ስብሰባ እና ጥበቃ ጎን ለጎን የበጋ ልማትን በትኩረት እየሠሩ መሆኑን የነገሩን ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ናቸው:: ምክትል ኃላፊው ለበኵር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ በአዲስ እና በነባር 39 ሺህ 552 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 27 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ የሚለማ ነው።
ለመስኖ ልማቱ የወንዝ ጠለፋ፣ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን የመጠገን እና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ዕቅዱን ለማሳካትም የግብዓት እና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማቅብ በትኩረት እየተሠራ ይኛገኛል።
እንደ አቶ አዲሱ ማብራሪያ ለበጋ መስኖ ልማት የሚውል 84 ሺህ 514 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ያስፈልጋል፤ ከዚህ ውስጥ ከአምስት ሺህ ኩንታል የሚበልጠው ተሰራጭቷል። አንድ ሺህ 250 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብም በዕቅድ ተይዟል። ሦስት መቶ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ተሰራጭተዋል።
በተመሳሳይ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ታደሰ ማሙሻ ለበኵር ጋዜጣ እንደገለፁት ዞኑ 43 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ነው። የተሻለ ምርት ለማግኘት ጊዜን እና ጉልበትን እንዲሁም ግብዓት እና የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ መምሪያ ኃላፊው አስገንዝበዋል:: አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት በመሰብሰብ ለመስኖ ልማት ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል::
ከዞኑ ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ለበጋ መስኖ ልማቱ ጥቅም ላይ የሚውል 126 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል። የምርጥ ዘር እጥረት እንዳይከሰት ደግሞ በምርጥ ዘር አባዢ ድርጅቶች ተዘጋጅቷል።
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት 342 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በሦስት ዙር በመስኖ በማልማት ከ47 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከዚህ ውስጥ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ እንደሚሸፈን ተመላክቷል።
የዘንድሮውን የበጋ ስንዴ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግም አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ለመስኖ ልማቱ የሚያገለግል ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብም ታቅዷል።።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም