ዋናው ጤና ነው እንዲል የሃገሬ ሰው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ንጋት ላይ በየቦታው በቡድን እና በግል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችን ማየት የተለመደ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ከአካል ብቃት መጎልበት ባለፈ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጡንቻዎች በአግባቡ እንዲሰሩ ከማድረግ ጀምሮ የተከማቸ ስብና ካሎሪን በማቃጠል ሰውነት አስፈላጊውን ቁመና እንዲይዝ ያግዛል። ሩጫ፣ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ዋና፣ ክብደት ማንሳትን እና የመሳሰሉትን የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ በኋለኛው የእድሜ ዘመን በጤና ለመኖር ያግዛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን በከተሞች አካባቢ የውፍረት መጨመር እየተበራከተ መጥቷል። በተለይ ሴቶች ከወሊድ በኋላ በጭንቀት እና በአመጋገብ የሚመጣ የክብደት መጨመር ይስተዋልባቸዋል።
ከሴቶች በተጫማሪ ከመጠን በላይ ለውፍረት የተጋለጡ ህጻናትንም ማየት እንግዳ አይደለም። ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 17 ዓመት የሚሆኑ የዓለማችን ታዳጊዎችም በቂ እንቅስቃሴ እንደማያደርጉ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። እናም የሕፃናት አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤና እየተቃወሰ፤ አልፎም ማሕበራዊ አኗኗራቸው ቅጥ ያጣ እየሆነ መምጣቱን መረጃው ያስነብባል።
ድርጅቱ ይህ ችግር የደላቸው የዓለም ሃገራት ብቻ ሳይሆን እንድ ኢትዮጵያ ‘ድሃ’ በሚባሉ የዓለም ሃገራትም በሰፊው የሚንፀባረቅ ነው ብሏል።
ጥናቱ በተካሄደባቸው 146 የዓለም ሃገራት ታዳጊ ወንዶች ከሴቶች በተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ተደርሶበታል። አብዛኞቹ ሴቶች ከወለዱ በኋላ እንቅስቃሴ ስለማያደርጉ የሚመገቡት ምግብ ለውፍረት እንደሚዳርጋቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በተለይ ሴቶች ከወሊድ በኋላ ከ20 እስከ 30 ኪሎ ግራም ክብደት እንደሚጨምሩ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረገው የአካል ብቃት እና የስነ ምግብ ባለሙያው ሄኖክ ኪዳነ ማርያም ተናግሯል።
ሰዎች በሥራ ቦታ ስለማይንቀሳቀሱ የዚህ ችግር ተጠቂ መሆናቸውን ባለሙያው ያስረዳል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባህል እየሆነ መጥቷል። በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሰው መጨመሩን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ማህበራዊ ሚዲያ በተለይ የቲክ ታክ መምጣትን ተከትሎ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚያዘወትሩ ግለሰቦች ለውጦቻቸውን ማጋራታቸው ሌሎችም እንዲነቃቁ አግዟል። በተለይ ሴቶች ከወለድን በኋላ ሰውነታችን አይስተካከልም በሚል የሚያራምዱት አመለካከት እንዲሰበር ማድረጉ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አስችሏል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እየዳኑ መምጣታቸው ማህበረሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የህይወት ዘይቤው እንዲያደርግ ማገዙ ነው የተገለጸው። ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲጀምሩ የሚያጋጥማቸው መስናልክ ተስፋ እንዳያስቆርጣቸው እቅድ ማስቀመጥ አለባቸው።
ያካል ብቃት እንቅስቃሴ የማደርገው ውፍረት ለመቀነስ፣ ለጤና፣ ለክህሎት ወይስ ለቅርጽ ነው የሚለውን ማወቅ ይኖርባቸዋል። የስነ ልቦና ዝግጅትም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ከመጀመራቸው በፊት የአካል ብቃት ደረጃቸው የቱ ጋ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ምን ያህል ስዓት መሥራት እንደሚያስፈልጋቸውም በባለሙያ በመታገዝ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመራቸው በፊት ዓላማ እና ግብ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል። በቡድን ነው ወይስ በግል ቢሠሩ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ የሚለውንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ነው የተባለው።
በቡድን መሥራት ድካማቸውን እንዲረሱ እና መሥራት ያለባቸውን እንቅስቃሴ እንዲሠሩ ያደርጋል። ነገር ግን በቡድ የሚሠሩ ሰዎች የጤና ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ የተመጠነ እና ገደብ ያለው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመከራል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የህይወት ዘመን ዘይቤ መሆን እንዳለበት ባለሙያው ያስረዳል። “አካላችን ባልተንቀሳቀሰ ቁጥር ጡንቻችን እየሞተ ይሄዳል፤ ኦክሲጅን የማስገባት እና የማሰወጣት መጠኑ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የስብ ክምችት እየጨመረ ይሄዳል። የስብ ክምችት ደግሞ ለኮሊስትሮል፣ ለደም ግፊት፣ ለስኳር እና ለካንሰር በሽታ ያጋልጣል” ሲል ባለሙያው ሄኖክ ኪዳነ ማርያም ተናግሯል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብቻ ማደርግ መፍትሄ እንደማይሆን ግን ባለሙያው ይናገራል። ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ አመጋገብንም ማስተካከል ይጠይቃል። ለመኖር ነው የምንበላው፤ ለመብላት አይደለም የምኖረው፡፡ ስለዚህ ረዥም ዓመት በጤና ለመኖር አመጋገባችንን ማስተካከል ለነገ የማይተው ተግባር መሆኑን የአካል ብቃት እና የስን ምግብ ባለሙያው ይናገራል፡፡
ውፍረት ለመቀነስ የሚለበስ፣ የሚጠጣም ሆነ በታብሌት መልክ የሚወሰድ ማንኛውም ሰው ሰራሽ ነግሮች መወሰድ የለባቸውም። ሌላው አመጋገብ በጾታ፣ በሰውነታችን መጠን፣ በእድሜ ደረጃ የተለያየ መሆን ይኖርበታል፤ ወደ ሰውነታችን የምናስገባው ከምናስወጣው ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት” ባይ ነው ባለሙያው።
ሰዎች እንደየ እድሜያቸው እና የጤና ሁኔታቸው ክብደት ለመቀነስ የጥንካሬ እና የብርታት ሥራዎችን መሥራት ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው የብርታት እና የጥንካሬ ሥራዎች በሳምንት አምስት ቀን ከ60 እስከ 90 ደቂቃ መሥራት እንደሚጠበቅበት የአካል ብቃት እና የስነ ምግብ ባለሙያው ሄኖክ ኪዳነ ማርያም ያስረዳል።
አሁን ላይ በከተሞች አካባቢ በማለዳ በቡድን እና በግል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችን ማየት እንግዳ አይደለም። ሁሌም መሮጥ ብቻ ሳይሆን እግር ኳስ መጫወት፣ መዋኘት፤ ጠረጴዛ እና ቅርጫት ኳስ መጫወት ሰውነታችን ከእንቅስቃሴ እንዳይወጣ ያግዛል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመጀመሪያዎቹ 30 ቀናት ለአሰልጣኞች እና ለሰልጣኞች ፈታኝ ነው። ስውነታችን ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ ስለሚቆይ እና አመጋገባችን ያልተገደበ በመሆኑ እነዚህን ቀናት አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል። ከዚያ በኋላ ግን ሰዎች ለውጣቸውን እያዩ ስለሚሄዱ እየለመዱት እንደሚመጡ ባለሙያው ተናግሯል።
ጀማሪዎች ማተኮር የሚኖርባቸው በእንቅስቃሴው መጠን ላይ ሳይሆን በእንቅስቃሴው መዘውተር ላይ መሆን ይገባዋል። እንደ ግቡ ቢለያይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብቻውን ለውጥ አያመጣም። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ከ30 እስከ 40 በመቶ ብቻ ነው ለውጥ የሚያመጣው። ታዲያ ድካማችንን ውጤታማ ለማድረግ አመጋገባችንንም ማስተካከል እንደሚኖረብን ባለሙያው ይመክራል። ።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም