“ኮሜንታተሯ” እናት

0
145

እ.አ.አ በ2018 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በአንፊልድ ሮድ ሊቨርፑል ናፖሊን አስተናግዶ አንድ ለባዶ ማሸነፉ በታሪክ ተመዝግቧል። ግቧንም ሙሀመድ ሳለህ ማስቆጠሩን መረጃዎች አመልክተዋል። ይህን ልብን የሚያሞቀውን የአንፊልድ የፌሽታ እና የደስታ ድባብ ከቀዮች የልብ ደጋፊ ከማይክ ኬርኒ በስተቀር ሁሉም ስቴዲየም ያለ ተመልካች ተመልክቶታል።

ወጣቱ ማይክ ኬርኒ ግን ዐይነ ስውር ነውና የአንፊልድን ድባብ በጆሮው ሰማው እንጂ በዐይኑ አልተመለከተውም። ታዲያ ግብጻዊው ኮከብ ሙሀመድ ሳላህ ግቧን ባስቆጠረበት ቅጽበት ጓደኛው እና የአክስቱ ልጅ የሆነው ስቴፈን ግቧን ሳላህ እንዳስቆጠራት ወደ ጆሮው ጠጋ ብሎ ሲነግረው በካሜራ ዕይታ ውስጥ ገባ።

በማግስቱም ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ የኤክስ (X) ማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ይህንን አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል በማዘዋወር አድናቆታቸውን አሳይተውታል። ዐይነ ስውሩ ማይክ “እኔ እንደማንኛውም የእግር ኳስ ደጋፊ ነኝ በግልጽ ማየት አልችልም፤ ይህን ደግሞ በፀጋ እቀበላለሁ፡፡ ግን  ማየት ብችል ደስተኛ ነኝ” ሲል ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል። ሳላህ ግቧን ማስቆጠሩን የአክስቴ ልጅ ባይነግረኝ ኖሮ በጫጫታ መሀል ግቧን ማን እንዳስቆጠረ መለየት ይከብደኝ ነበር ሲልም ተደምጧል።

ማይክ ሁሌም ትንታኔዎችን ከመስማት ይልቅ ስቴዲየም ገብቶ ጨዋታዎችን በቀጥታ መከታተልን ይመርጣል። ጓደኛው እና የአክስቱ ልጅ ከሆነው ስቴፈን በተጨማሪ ሌሎች አምስቱ ጓደኞቹም እገዛ እንደሚያደርጉለት ይናገራል። ከእርሱ ጎን በመቀመጥ ስለጨዋታው እንቅስቃሴ እና ድባብ መረጃ እንደሚሰጡትም ቢቢሲ አስነበቧል።

ዓለም በማይክ ኬርኒ አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል ተገርሞ ሳያበቃ የእግር ኳስ ምድር ተብላ ከምትጠራው  ብራዚል  አዲስ የእግር ኳስ ሁነት ታይቷል፤ተሰምቷል። እግር ኳስ ለሁሉም ነው። ብራዚላዊት እናት ሲልቪያ ግሪኮም ይህንን በሚገባ ተረድታለች። ወይዘሮ ሲልቪያ የአንድ ልጅ እናት ነች። ልጇም ኒኮላስ ይባላል። የተወለደው አምስት ወራት እንኳ ሳይሞላው ነው። ታዲያ ሲወለድ በተፈጠረበት ችግር ሁለቱም ዐይኖቹ ማየት አይችሉም፤ መጠነኛ የእድገት ውስንነትም አለበት።

እናት ሲልቪያ ለእግር ኳስ ጥልቅ ፍቅር አላት። አሁን ላይ ግን እግር ኳስን ስቴዲየም ገብታ የምትመለከተው ለራሷ ሳይሆን ለልጇ ደስታ መሆኑን የኢንሳይድ ፊፋ መረጃ ያመለክታል። ይህም ልጇ ኒኮላስ ደስታን እንዲያገኝ የምትሄድበት አንዱ መንገድ ነው። ሲልቪያ ስቴዲየም የምትገባበት ጉዳይ ከአምስት ዓመታት በፊት በአንድ አጋጣሚ ተገለጠ። ነገሩ ወዲህ ነው።

ሲልቪያ የምትወደውን ክለብ የፓልሜራስን ጨዋታ ለማየት ወደ ስቴዲየም ስትገባ ኒኮላስን ይዛ መሄድ ጀመረች። ታዲያ በዚህ ጊዜ ኒኮላስ የራዲዮ ማዳመጫውን በማውጣት የደጋፊዎችን ዝማሬ እና ጩኽት ማዳመጥ ጀመረ። ከዚህ በኋላ ነበር ነገሮች የተቀየሩት። እናት ሲልቪያም ስለጨዋታው እንቅስቃሴ እና በስቴዲየሙ ስለሚፈጠሩ አጠቃላይ ሁነቶች ለልጇ ኒኮላስ ለመተረክ ወሰነች።

ከዚያም ሜዳ ላይ የሚፈጠሩ ትዕይንቶችን በጥሩ መንገድ እንደተሰናሰለ የመድረክ ተውኔት ለታዳጊው ኒኮላስ መተረክ ጀመረች። ኒኮላስም በእናቱ አማካኝነት በሚሰጠው ገለጻ እና ትንታኔ በተለይ ስለሚወደው ፓልሜራስ ክለብ ብዙ መረጃዎችን ሰበሰበ፤ እውቀትም አዳበረ። ስለእግር ኳስም ያለው ግንዛቤ ከፍ አለ። ይህም የህይወታቸው አንድ አካል ሆነ፤ ለዓለምም ተገለጠ፡፡

በብራዚል ፓልሜራስ ከኮረንቲያስ በሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ አንድ የፓልሜራስ ደጋፊ የሆነች እናት ከታዳጊ ልጇ ጋር ስትነጋገር በካሜራ ዕይታ ውስጥ ትገባለች። ይህ ትዕይንትም የዓለምን ቀልብ በመሳብ መነጋገሪያ ሆነ። ወይዘሮ ሲልቪያ ግሪኮ ነበረች ለ12 ዓመት ታዳጊ ልጇ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በቀጥታ  እያስተላለፈች፣ እየተረከች ሳለ በካሜራ ዕይታ ውስጥ የገባቸው።

የእርሷ እና የልጇ ተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርጾ መያዙን ልብ ያላለችው እናት ጨዋታው ተጠናቆ ስቴዲየሙን ለቀው ሲወጡ እርሷ እና ልጇ መነጋገሪያ አርዕስት መሆናቸውን ተረዳች። “ለኒኮላስ ዓይኖቹ እኔ ነኝ፤ ይህ አዲስ አይደለም፤ ለዓመታት በዚህ መንገድ ሳደርገው ነበር፤ ስለማይታይ እንጂ” ስትልም በወቅቱ መናገሯን የብራዚል ጋዜጦች ያስታውሳሉ።

ኒኮላስ የፓልሜራስ የልብ ደጋፊ ነው። እናት ሲልቪያ ግሪኮ ለልጇ ጨዋታዎችን በቀጥታ ከማስተላለፍ ባሻገር ትዘምራለች፤ ተጫዋቾችን ታበረታታለች። “እኔ ብቁ የጨዋታ አስተላላፊ (ኮሜንታተር) አይደለሁም፤ ነገር ግን ለልጄ የቻልኩትን እና የተመለከትኩትን ለመንገር እሞክራለሁ ስትል ተደምጣለች። የአየሩን ፀባይ፣ የእያንዳንዱን ተጫዋች ባህሪ፣ የፀጉራቸውን ቁርጥ እና ቀለም እና ምን ዓይነት መለያ እንደለበሱ ጨምሬ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ለልጄ እተርክለታለሁ ስትል መናገሯን መረጃዎች አመልክተዋል።

ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ደግሞ የጨዋታውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በመተረክ ለኒኮላስ አሳውቃለሁ ስትል ተናግራለች። ከልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስ እወዳለሁ። በህይወቴ ውስጥ ያለው እግር ኳስ በልጄ ህይወት ውስጥም ቀስ በቀስ ለውጥ እያመጣ ነው። በጊዜ ሂደት ደግሞ ኒኮላስ ሌላ ልጅ እየሆነ መምጣቱን እናቱ ታስረዳለች። ኒኮላስ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር አድጓል፤ አሁን ህይወቱ ተቀይሯል፤ ደስተኛ ልጅም ሆኗል ብላለች።

እያደረገች ያለችው በጎ ተግባር የኒኮላስን ህይወት ብቻ አይደለም ያሻሻለው፤ ተገፍተው ጥግ ላይ ለሚቀመጡ አካል ጉዳተኞች ከማህበረሰቡ ጋር እንዲገናኙ በር ከፍቷል። አሁን ላይ ኒኮላስ በመላው ዓለም ይታወቃል። እናም ስፖርት የአካል ጉዳተኞችን ህይወት በበጎ የመቀየር አቅም እንዳለውም ትናገራለች።  “ለእኔ እናት በመሆኔ በዓለም ላይ ትልቁ ምርጥ ነገር ነው። ልብ፣ነፍስ ነው፣ህይወት ነው፣በቃ ሁሉም ነገር ነው”  ስትል ትናገራለች።

ምንም እንኳ “ፕሮፌሽናል ኮሜንታተር” ባልሆነም ፓልሜራስ ግብ ሲያስቆጥር ግን ቃላትን የማወጣበት መንገድ የተለየ ነው። አስደሳች ሁነትም ያ ነው ስትል ትናገራለች። ለዚህ በጎ ሥራዋ በ2019 እ.አ.አ ፊፋ የምርጥ ደጋፊዎች ሽልማትን አበርክቶላታል። የሲልቪያ እና የኒኮላስ ታሪክ በፊፋ ዶት ኮም በተከታታይ ስድስት ክፍል (The beautiful Game) በሚል ርዕስ ፍቅር በሚያዋህዱ አነቃቂ ታሪኮች ደምቆ ቀርቧል።

እግር ኳስ በሰዎች ውስጥ ደስታ እና ሁለንተናዊ ስሜትን የሚፈጥር ስፖርት ነው። ለዚህም ነው ይላል የኢንሳይድ ፊፋ መረጃ  ማይክ ኬርኒም ሆነ ኒኮላስ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው እየታገዙ በቀጥታ የጨዋታ ግጥሚያዎችን ለመታደም ስቴዲየም የሚገቡ።።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታኅሳስ 21  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here