እያገረሸ ነው

0
110

የዓለም ጤና ድርጅት “እ.አ.አ በ2030 ከኤች አይ ቪ ኤድስ ነጻ ዓለም እፈጥራለሁ!“ የሚል መሪ ዕቅድ ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቆ  ነበር:: በአንዳንድ ሀገራት ያለው የቫይረሱ  ስርጭት ግን የታሰበውን ለማሳካት ፈተና ሆኖበታል ይላሉ በዘርፉ በስፋት እየሠሩ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት።  ሜዲካል ኤክስፕረስ በ2023 ባወጣው መረጃ በዓለም ላይ ከ39  ሚሊዮን በላይ  ወገኖች  የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው  እንደተገኘባቸው  አመላክቷል።  ከዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ ነጥብ ሦስት  ሚሊዮኑ በየዓመቱ በአዲስ መያዛቸውን  እንዲሁም  በዚያው ዓመት ብቻ 630 ሺህ ሰዎች ውድ ሕይወታቸውን መነጠቃቸውን ዘገባው ጠቁሟል::።

በአፍሪካ ደግሞ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እንዳለባቸው ይነገራል። ይህም የዓለምን 65 በመቶ ገደማ ድርሻ ይይዛል:: ከአውሮፓዊያኑ 2001 እስከ 2023 ባሉት  ጊዚያት የአፍሪካ ሀገራት ለዘርፉ በሰጡት ትኩረት የቫይረሱን የስርጭት መጠን መቀነስ ቢችሉም አሁንም ኤች አይ ቪ  ትልቅ የጤና ስጋት በመሆኑ ወጥነት ያለው ሥራ እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት(WHO) አሳስቧል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በየቀኑ እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት ያሉ 570 ሴቶች በኤች አይ ቪ ቫይረስ ይያዛሉ። ይህም ከወንዶች  በሦስት እጥፍ ይበልጣል።

በኢትዮጵያም የኤች አይ ቪ  ስርጭት አሁን ላይ እየተስፋፋ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ከሰሞኑ የህብረተሰብ ጤና ከፍተኛ አማካሪ  ዶ/ር አምሀ ኀይሌ  ለመገናኛ  ብዙኃን  በሰጡት መረጃ በኢትዮጵያ 605 ሺህ 238 ወገኖች ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው  ተገኝቷል።

በየዓመቱ ደግሞ ሰባት  ሺህ ወገኖች  በአዲስ በቫይረሱ እንደሚያዙ ነው በዘንድሮው የዓለም ኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን አከባበር ላይ የጤና ሚንስቴር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ያስረዱት። እንደ ሀገር የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ ዜሮ ነጥብ ስምንት በመቶ ሲሆን በየዓመቱ 10 ሺህ ወገኖች ሕይወታቸውን ያጣሉ::

ከሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ  የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ታዲያ በአንዳንድ ክልሎች  የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ ከሀገራዊ  በላይ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚያሻው ነው።   በሀገሪቱ ከተመዘገበው የኤች አይ ቪ  የስርጭት ምጣኔ አንጻር አዲስ አበባ 3 ነጥብ 25 በመቶ፣ ጋምቤላ በ3 ነጥብ 24፣ ሀረሪ በ2 ነጥብ 76፣ ድሬዳዋ በ2ነጥብ 35 በመቶ ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአማራ ክልል ያለው የስርጭት ምጣኔ ደግሞ ከሀገሪቱ አማካይ በላይ መሆኑ ታውቋል። በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመ ለአሚኮ በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ከተለዩት 173 ሺህ 463 ይበልጥ የኤች አይ ቪ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 157 ሺህ 972 ሰዎች  ተመርምረው ራሳቸውን አውቀዋል:: 156 ሺህ 91 የሚሆኑት ደግሞ ሕክምና እየተከታታሉ መሆናቸው ተገልጿል:: በአዲስ ከሚያዙት ውስጥ 67 በመቶ ከ30 ዓመት  በታች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::

ቫይረሱ በፍጥነት እየተሰራጨ ካለባቸው አካባቢዎች መካከል ደሴ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙም አረጋግጠዋል።  በክልሉ ከቫይረሱ ተጠቂዎች  መካከልም 61 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን አቶ ውድነህ ተናግረዋል::

በክልሉ ካሉት አካባቢዎች ደግሞ ትኩረታችንን ደብረብርሃን ከተማ ላይ አድርገናል። በከተማዋ ለኤች አይ ቪ ኤይድስ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ተከትሎ በበሽታው የመያዝ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ገልጿል። ባለፈው በጀት ዓመት ምርመራ ከተደረገላቸው 24 ሺህ 359 ይበልጥ ተጋላጭ የማሕበረሰብ ክፍሎች መካከል 321 ሰዎች በአዲስ የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጠቂ መሆናቸውን መምሪያው አስታውቋል። አሁን ላይ በማሕበረሰቡ ዘንድ በሽታው የሌለ እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ተከትሎ  በከተማዋ የስርጭት ምጣኔው  አንድ  ነጥብ ሦስት  በመቶ ደርሷል።

ከዛሬ  25 ዓመታት በፊት ጀምሮ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸው ወይዘሮ ሰናይት አክሊሉ የበሽታውን አስከፊነት አስመልክቶ ምስክርታነቸውን ሰጥተውናል። በወቅቱ ለዘላቂ የሕይወት ግብና በትምህርታቸው ላይ ትኩረታቸውን  ማድረግ ሲገባቸው ለወጣትነት ፈተናዎች በቀላሉ እጅ መስጠታቸው በኋላ መዘዝ አስከትሎባቸዋል።  እርሳቸው እንደሚሉት ቤተሰብ ያቀረበውን ተደጋጋሚ ምክር በመዘንጋት  ትምህርቱም እስከወዲያኛው ቀርቶ በራስና በፍቅር አጋር ውሳኔ ትዳር ተመስርቶ በዚያው ፍጥነት  ልጅ ተወለደ።

ትዳር የመሰረቱት ያለምንም የጤና ምርመራ እንደነበር ባለታሪካችን ያስታውሳሉ::  ውጤቱም ጎጇቸው ሳይሞቅ አራስ  ቤት እያሉ ባለቤታቸውን ተነጠቁ፤  በኤች አይ ቪ ኤድስ ምክንያት የመሞታቸውን  እውነታ ያወቁትም በዚያው  ጊዜ ነበር።

በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት የደረሰባቸውንና ዛሬ ላይ እንደ እግር እሳት እየፈጃቸው ያለውን ችግር ተከትሎም ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ መገለል እና መድሎ ደርሶባቸዋል። 25 የመከራ ዓመታትን ከብዙ ውጣ ውረዶች ጋር ተጋፍጠው ያሳለፉት ወይዘሮ ሰናይት በማህበረሰቡ ዘንድ አድሎና መገለል ዛሬም ድረስ መዝለቁን ተናግረዋል::

ወይዘሮ ሰናይት የሚመሩት የሄዋን ሴቶች የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማን ማህበር ስለበሽታው አስከፊነት ትውልዱን እያስተማረ ይገኛል። ይሁን እንጂ ለዚህ በሽታ የተሰጠው ትኩረት ማነስና የትውልዱ መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮባቸዋል። “አሁን ላይ በሽታው የሌለ እስኪመስል ድረስ እየታዬ ያለው መዘናጋት የከፋ ዋጋ ሳያስከትል ይብቃ! ማለት ይገባል፤ ጉዳዩ የማይመለከተው የለምና ሁሉም አካል የድርሻውን ይወጣ::  በተለይ ወጣቱ ከኔ ይማር! ተገቢውን ጥንቃቄም ያድርግ!“ በማለት መክረዋል።

ኤች አይ ቪ ኤድስ በዓለም ላይ አድማሱን እያሰፋ ያለ በሽታ መሆኑ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ አስከትሏል። ይህ እውነታ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መገለጫ አለው።

አቶ ኤልያስ ጌታቸው በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ቡድን መሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ቀደም ባሉት ጊዜያት የኤች አይ ቪ ኤድስን ስርጭት ለመግታትና በበሽታው ምክንያት የሚከሰትን ችግር  ለማስቀረት  መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ማሕበረሰቡ በልዩ ሁኔታ ርብርብ አድርገዋል። በዚህም አመርቂ ውጤት ተገኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል።  ይሁን እንጂ እንደ ሀገር የተገኘውን አመርቂ ውጤት ተከትሎ በማኅበረሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንዲፈጠር ሆኗል። ይህም አሁን ላይ የበሽታው የስርጭት ምጣኔ ዳግም አሳሳቢ እንዳደረገው አቶ ኤልያስ ጠቁመዋል።

በደብረብርሐን ከተማ አስተዳደር የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማእከል ያደረገ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ቡድን መሪው ተናግረዋል። ሴትኛ አዳሪዎች፣ የሕግ ታራሚዎች እና የሱስ ታካሚዎች  (injectable drug users) ይበልጥ ተጋላጭ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተብለው ከተለዩት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ትዳራቸውን የፈቱ፣ እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያለ ሴቶች፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ተንቀሳቃሽ ሠራተኞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ እንዲሁም በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ  ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችም ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ከሚባሉት መካከል ተጠቃሽ  ናቸው። በተለይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸው ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻሉ ለተጨማሪና ውስብስብ ለሆኑ የጤና ችግሮች የሚጋለጡበት አጋጣሚ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2030 ከኤች አይቪ ኤድስ ነጻ ትውልድ ማፍራት የሚለውን መሪ እቅድ ለማሳካት ከዚህ በፊት ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት አሁንም መድገም እንደሚያስፈልግ  ቡድን መሪው አስገንዝበዋል::

ኢትዮጵያን ጨምሮ የኤድስ ቀን በልዩ ልዩ ሁነቶች በተከበረበት ወቅት  በመላው ዓለም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሀገራት እንደ አዲስ መነቃቃት እንዳለባቸው ተመላክቷል። መተላለፊያ መንገዶችን አውቆ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ከሁሉ እንደሚጠበቅም መልእክት ተላልፏል።

(ደጀኔ በቀለ)

በኲር የታኅሳስ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here