የአእምሮ መካኖች እንዳንሆን…

0
164

ሀገራችን ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ ባለቤት መሆኗ በብዙ ድርሳናት  ተሰንዶ ሲነገር እንዲሁም ሲነበብ ኖሯል። አዎ! ይህም ሀገራችንን  የሥልጣኔ መነሻ ከሆኑ  ሀገራት ተርታ ያስመድባታል።

የሰለጠነ ማህበረሰብ ይኖር ዘንድ የቀለም  ትምህርት እና ጽሑፍ ግድ ነው።  ጸሐፍት ካሉ ድግሞ አንባቢያን ይኖራሉ። ለዚህም ነው እንግዲህ ንባብን በሀገራችን ካሉ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ነጥሎ ማየት የሚከብደው።

ንባብ በግለሰብም ሆነ በማሕበረሰብ  ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖረዉ የሚገባ መሰረታዊ ክህሎት ነዉ። የሰዉ ልጅ ሰብዕናዉን  የሚቀርጽበት እና  የማንነቱ እንዲሁም የምንነቱ መገለጫ  የሆኑት ባህላዊ፣  ታረካዊ  ሥነ ጥበባዊ… ቅርሶቹ እና ርስቶቹ እንዳይጠፉ ለቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ የሚያቆይበት፤ የሚያስተላልፍበት ዓይነተኛ መሳሪያም  ነው።

ማንብብ የማይችል ግለሰብም ሆነ ማህብረሰብ  አካባቢውን የማወቅ እና  የመግለጽ ብቃቱ በመስማት እንዲሁም በማየት ላይ ብቻ የተመሠረተ በመሆኑ፤  ለማንኛዉም የፈጠራም ሆነ የእውነታ ጽሑፍ ዕውቆቶች እንግዳ ወይም ባይተዋር ይሆናል። ስለ ሕይወት፣ ተፈጥሮ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም  አቀፍ ኩነቶች ያለዉ ግንዛቤ ውስን እንዲሁም  የተዛባ ይሆናል።

የንባብ ባህላችን  እንደ ሀገራዊ እሴት መቆጠር የሚገባው እና ልናዳብረው ግድ የሚለን ነገር ነው። የሰለጠነ ሀገር ይኖር ዘንድ የሰለጠነ ማህበረሰብ መኖር አለበት፤ ለዚህም የማንበብ ልምድን ማዳበር ተገቢ ነው።

ቀደምት የንባብ ልምድ ከነበራቸው  ጥቂት ሀገራት መካከል የጥንቷ ሮም፣ ጥንታዊቷ ፔርሺያ ወይም  የአሁኗ ኢራን፣ የታላቁ እስክንድር ሀገር  ግሪክ፣ የጥንቷ መስኮብ፣ ሲቀጥል ሶቪዬት ህብረት ወይም የአሁኗ ሩስያ፣ ጃፓን፣ ህንድ፣ ቻይና እና  እስራኤል የመሳሰሉት የቆየ የንባብ ልምዳቸውን  አስቀጥለዋል። በንባብ  ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ተሳክቶላቸዋል ከሚባሉት ሀገራት መካከልም ተጠቃሽ ናቸዉ።

ሀገራችን ቀደምት የንባብ እና የጽሕፈት ታሪክ መነሻ መሆኗ  ሲወሳ አንዱ ማሳያ አያሌ የዓለም ሃገራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ሀገራችን በመምጣት በርካታ የብራና ጽሑፎችን እና ነዋየ ቅዱሳትን መዝብረው በመውሰድ፤ የራሳችንን እውቀት መልሰው ሲያሳውቁን  የመኖራቸው  ጉዳይ ነው።

እዚህ ላይ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሀገራችን የመጣውን  አሳሹን ጀምስ ብሩስን ማንሳት ተገቢ ነው። በታሪክ መማሪያ መጽሐፎቻችን ሳይቀር የዓባይን ወንዝ መነሻ እና መድረሻ ያጠና በሚል ስለ እሱ ተምረናል:: ሆኖም ባምስት ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው የፈጸመው ጥፋት አልተገለጸም::  ጀምስ ብሩስ አምስት ዓመት ኢትዮጵያ ቆይቶ ግዕዝ ቋንቋን  በሚገባ  አጥንቶ መጽሐፈ ሄኖክን ይዞ የሄደ ቢሆንም ስለዚህ ጉዳይ  እንዲት መስመር የተባለ ነገር የለም። እንዴት እና ለምን የሚለውን ለጊዜው ዝርዝሩን እናቆየው፤ ይህን ያነሳነው የሀገራችንን የጽሕፈት እና የንባብ ታሪክ ቀደምትነት ለማውሳት ያህል ነውና።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የዳበረ የንባብ ልምድ ያላቸዉ ግለሰቦች߹  የንባብ ልምድ ከሌላቸዉ ግለሰቦች ይልቅ በሦስት እጥፍ የተፈጥሮ እንክብካቤ ከማድረጋ ቸውም በላይ የበጎ አድራጎት (ሰብዓዊ) ድርጅቶች በሚያደርጓቸዉ እንቅስ ቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸዉ። ይህ ዓይነቱ ንቁ ተሳትፎ አንባቢያንን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከማድረጉም በላይ ለግለሰቦችም ሆነ  ማህበረሰቦች ደህንነት በእጅጉ ተቆርቋሪ እና ኃላፊነት የሚሰማቸዉ ዜጎች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

ስልጣኔ እና ባህልን ነጣጥሎ ማየት ይከብዳል፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውና። የትኛውም ስልጣኔ፣ ራስን መናቅን እና ሌሎችን እንደ ጭራ ከኋላ መከተልን ካስከተለ ስልጣኔ መሆኑ ቀርቶ ዘመናዊ ባርነት ይሆናል። በሌላ መልኩ ለስልጣኔ በሩን ከርችሞ  ባህል ላይ ብቻ  እንደመዥገር  ተጣብቆ የሙጥኝ የሚል  ማህበረሰብ ደግሞ እንደ ሃገር ለመቀጠል  የሚደረገውን የለውጥ ጎዳና አዝጋሚ  ያደርገዋል።  እንግዲህ  ሁለቱን አስታርቆ ለመሄድ  ጤናማ ያልሆነ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቀማችንንና  አካታችነት የጎደለው የትምህርት ፖሊሲያችንን ደጋግሞ በመፈተሽ ማረም ይገባል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየተዳከመ የመጣው የሀገራችን የንባብ ባህል በትውልድ ላይ ያስከተለው  የመንፈስ  እርዛት እንደ ስጋዊ ረሀብ ፈጥጦ ፊት ለፊት አለመታየቱ በጀ እንጂ በሀገራችን  ከ1977ቱ ያላነሰ ድርቅ  መከሰቱን ጠቋሚ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በርካታ የሀገር ውስጥ  ጥናቶች እንደሚያሳዩን እና እኛም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያችን እንደምንታዘበው ኢትዮጵያ የማያነቡ ዜጎች ካሉባቸው ሀገራት ተርታ በቀዳሚነት ትገኛለች።

ለሀገራችን የንባብ ባህል መቀጨጭ  እንደምክንያት በርካታ ነጥቦችን ማንሳት  ይቻላል::  ከጥቂት ዓመታት በፊት  በሀገራችን የብሔራዊ የብዙኃን መገናኛዎች ከሚተላለፉ የውጭ ትርጉም ፊልሞች አንዱ ከወጣት እስከ አዛውንት የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ በመሳብ ማህበራዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮቻቸውን ትተው የእሱን ጭብጦች የዕለት ተዕለት ርዕሳቸው በማድረግ  ለዘብተኞች  እንዲሆኑ እያደረገ ነው ብላችሁ ስሙን ባልጠቅሰም መቼም ምንነቱን የምትረዱልኝ ይመስለኛል። ምክንያቱም ፊልሙ ያልገባበት ቤት የለም ማለት ይቻላልና::

ንባብ ከፊልም እና ከቴሌቪዥን ከምናገኛቸዉ መረጃዎች ይልቅ የአስተሳሰባችንን አድማስ የማስፋት እና ምናባዊ ዕይታችንን የማሳደግ ብቃት እንዳለዉ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ። የሚያሳዝነዉ ግን አስቂኝ ፊልሞች እና የቴሌቪዥን መሰናዶዎች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምረዉ ንባብ በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ እንዲነፈገዉ ምክንያት ሆነዋል። አንድ ሰዉ አዘውትሮ ቴሌቪዥን የሚመለከት እና የማያነብ ከሆነ߹ የማንበብ ችሎታዉ ብቻ ሳይሆን በትክክል የማሰብ እንዲሁም የማመዛዘን  ችሎታዉ ሊቀንስ እንደሚችል በጥናት ተደርሶበታል።

በተጨማሪም በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ሳቢያ  ገደብ ያልተበጀላቸዉ እና ከምዕራቡ ዓለም በብርሃን ፍጥነት እየተሰራጩ ያሉ የአሉታዊ እንዲሁም መጤ ጎጂ ልማዶች  ወረራ፣ እንዲያም ሲል ወላጆች߹ መምህራን እና ት/ቤቶች የንባብን ባህል ከማዳበር አንጻር መጫወት የሚገባቸዉን ሚና በአግባቡ መጫወት አለመቻላቸው ነዉ።

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የራሳችን ያልሆኑ አስተሳሰቦች እና ማንነቶች እየበዙ ነው። በንባብ ያልተሞረደ እውቀት  ያገብዛል። የገበዘ ትውልድ ደግሞ “እኔነት” እንደጋሬጣ እየወጋ ስለሚያስቸግረው ተራማጅ መሆን ሲሳነው ይታያል። ይህም አሁን ላይ እያየለ የመጣውን የመንደርተኝነት  አስተሳሰብን ከማስፋፋቱም በላይ፤ የእዕምሮ ምክነትን ያስከትላል። ይህ ደግሞ እየሄድንበት ያለውን የንባባችንን የቁልቁለት ጉዞ ማፋጠኑ አይቀሬ ነው።

እንግዲህ የሀገራችንን የንባብ የቁልቁለት ጉዞ ለመግታት፣ ብሎም ወደ ቀደመ ደረጃው ለመመለስ ግንባር ቀደሙን ሚና የሚጫወቱ ወላጆች እና መምህራን መሆናቸዉ ይታመናል:: ከዚህ አንጻር በተለይ ወላጆች የልጆች የማንበብ ልምድ እንዲጎለብት ቀዳሚ ሚና አላቸው:: ልጆቻቸውን ስለንባብ ጥቅም እና መሰረታዊ የህይወት መርህ ሰለመሆኑ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ዝም ብሎ በንደፈ ሃሳብ ከመሞገት መጀመሪያ ወላጅ ራሱ አንባቢ መሆን ይጠበቅበታል::

ጋዜጦችን߹  መጽሔቶችን እና መጽሐፍትን ጓደኛው ማድረግ የቻለ ወላጅ    የንባብን ጠቀሜታ ለልጆቹ በተግባር ያስተምራል። የዛኔ ልጆች   የንባብ ባህልን ከቤተሰቦቻቸዉ  ወረሱ ማለት ነዉ።

ይህን የተረዱ ወላጆች ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ  ሁኔታዎችን ለመከታተል߹ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ወይም ለመዝናናት  ከሌሎች ዘዴዎች ይልቅ ንባብን ምርጫቸዉ ያደርጋሉ።  በሌላም በኩል ወላጆች ባካበቱት የንባብ ልምዳቸዉ አማካኝነት ለልጆቻቸዉ አዝናኝ እና አስተማሪ ድርሳናትን በማንበብ በልጆቻቸዉ የንባብ አመላካከት ላይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ይችላሉ።

ከወላጆች ቀጥሎ በተለይ  የህጻናትን እና የወጣቶችን የንባብ ባሕል በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወት የሚችሉት  መምህራን እና ት/ቤቶች  ናቸዉ። ተማሪዎች እንዲያነቡ የሚያበረታቱ መምህራን እና በባለሙያ የሚታገዙ፣ ባግባቡ የተደራጁ ቤተ መጻሕፍት  ያላቸዉ ት/ቤቶቾ ዉስጥ የሚማሩ ወጣቶች  ከሌሎች ይልቅ በእጅጉ የተሻለ የንባብ ልምድ እንደሚኖራቸዉ ይታመናል። ነገር ግን የሀገራችን ትምህርት ቤቶች ይህን ያሟላሉ ወይ? የሀገራችን የትምህርት አሰጣጥስ እንዴት ነው? ይሄን ለመመለስ ይከብዳል… ምናልባትም መቅበጥ ይሆናል…

ይህ ባለመሆኑ  እነሆ  የንባብ ልምዱ በየቀኑ እየሰለለ፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ፍቅሩ በየጊዜው እየጨመረ ቅንጭብጭብ ነገር በመቃረም፣ ግንጥል አውቀት ይዞ የሚሮጥ ትውልድ ላይ ደርሰናል።

ይህን ስል ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ወይም ዘመኑ የወለዳቸው የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች  ፈጽሞ አይረቡም ማለቴ እንዳልሆነ መረዳት ያሻል:: የራሳቸው የሆነ መልካም ነገር ይኖራቸዋል:: ሆኖም እነሱን ብቻ ሙጥኝ ብሎ ከንባብ መፋታት የአእምሮ ምክንነት ምንጭ ይሆናል:: የአእምሮ ምክነት ደግሞ ሀገር በየቀኑ እንድትሞት ከማድረጉም ባለፈ  በዜጎች ላይ  የከፋ ጦስ  ማምጣቱ አይቀሬ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ያነበብኩትን አንድ ስሙን የማላስ ታውሰውን ፈላሰፋ አባባል በማውሳት  ላብቃ።

“ከአብዛኛው የሰው ልጅ መብላትን  እንጂ ማጣጣምን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው፤ እየበላህ ማጣጣም አለመቻል እና ማንበብ እየቻልክ አለማንበብ ሁለቱ አንድ ናቸው:: “

   (ኢዮብ ሰይፉ)

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ተማሪ

በኲር የታህሳስ 21  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here