ከሰሞኑ የየመን ታጣቂ የሆነው የሃውቲ ቡድን በማዕከላዊ እስራኤል ላይ ያነጣጠረ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽሟል፤ አማጺ ቡድኑ የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ የሚያደርገውን ጦርነት እስኪያቆም በሀገሪቱ ላይ ወታደራዊ ዘመቻውን እንደሚቀጥል ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል።
የሃውቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በቴሌቭዥን ቀርበው እንደተናገሩት ዘመቻው የተካሄደው “ፍልስጤም 2” በተባለ ሃይፐርሶኒክ ባሊስቲክ ሚሳኤል ነው።
እንደሚታወቀው እ.አ.አ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሃማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ትገኛለች፡፡ በዚህ ምክንያትም በየመን የሚገኙ የሃውቲ ተዋጊዎች በእስራኤል፣ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚንቀሳቀሱ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ዒላማ በማድረግ ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ አማጺ ቡድኑ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት እስኪቆም ድረስ ጥቃቱን እንደሚቀጥል ነው የዛተው፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ባለፈው ዓመት ብቻ የሃውቲ ታጣቂዎች በእስራል ላይ 200 ሚሳኤል እና 170 የድሮን ጥቃቶችን ሰንዝረዋል፡፡ ከሰሞኑም በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝሯል፡፡
የሰሞኑን ጥቃት ተከትሎ ታዲያ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በሃዉቲዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወስዱ ነው የተናገሩት፡፡ የሃውቲ ታጣቂዎች ትልቅ ስህተት ሠርተዋል ሲሉ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር መናገራቸውንም ታይም ኦፍ እስራኤል ዘግቧል፡፡
ቀይ ባሕር በሰሜናዊው ጫፍ የስዊዝ ካናል እና በደቡባዊው ባብ ኤል -ማንደብ ስትሬት ጫፍ ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ይደርሳል። ከእስያ እና ከአውሮፓ ዕቃዎችን ለማምጣት የስዊዝ ቦይን የሚያቋርጡ መርከቦች የሚጓጓዙበት የተጨናነቀ የውኃ መንገድ ነው።
40 በመቶ የሚሆነው የእስያ – አውሮፓ የንግድ ልውውጥ በአካባቢው ያልፋል፡፡ ከሰባት እስከ 10 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን የነዳጅ ዘይት በዚህ ቀጣናው ይተላለፋል፡፡ ፓልም ዘይት እና የተለያዩ ዕቃዎች እና የምግብ ምርቶች ያልፉበታል፡፡ በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ዘይት በየቀኑ በስዊዝ ካናል በኩል ያልፋል፡፡
በኢራን የሚደገፉት የየመን አማፂያን ሃውቲዎች እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ አብዛኛውን ሰሜናዊ የመንን፣አንዳንድ ምዕራባዊ የሀገሪቱን ክፍል ፣ ለሳዑዲ አረቢያ ቅርብ የሆኑ አካባቢዎችን እና የሀገሪቱን ዋና ከተማ ሰንዓን ተቆጣጥረው ይገኛሉ።
ሃውቲዎች ራሳቸውን አንሳር አላህ (የፈጣሪ ደጋፊዎች) በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። ሃውቲዎች በ1990ዎቹ ብቅ በማለት እ.አ.አ በ2014 ቡድኑ በየመን መንግሥት ላይ በማመጽ ከሥልጣን እንዲወርድ በማድረግ ከባድ የሆነ ሰብኣዊ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል።
ሃውቲዎች በክልሉ በሚጓዙ መርከቦች ላይ አልፎ አልፎ ዒላማ በማድረግ ጥቃት ሲፈጽሙም ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን እ.አ.አ ጥቅምት 7 ቀን 2023 የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ጥቃቶቹ ጨምረዋል። መርከቦቹን ለማጥቃት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ፀረ – መርከብ ሚሳኤሎችን ተጠቅመዋል፤ ሄሊኮፕተርን በመጠቀምም የእስራኤል ንብረት የሆነውን መርከብ በቁጥጥር ሥር እስከማዋል ደርሰዋል።
እ.አ.አ በጥቅምት 2023 በጋዛ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ሃውቲዎች ከ90 በላይ የንግድ መርከቦችን በሚሳኤል እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች ዒላማ አድርገዋል። በጥቃቱ አንድ መርከብ ሲያግቱ ሁለቱን አስምጠዋል፡፡
በአማጺ ቡድኑ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎ እስራኤል፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ በምላሹ በየመን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ሰንዝረዋል። ውጤት ባያስገኝም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሃውቲዎች የቀይ ባሕር የመርከብ ጥቃቶችን እንዲያቆሙም በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር።
ሃውቲዎች የሚያደርሱት ጥቃት በቀጣናው ምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን አድርሷል፡፡ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት መስመሮች ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖም ቀጥሏል፡፡ ለአብነትም በሳምንት ውስጥ በቀይ ባሕር የሚያልፉ የንግድ መርከቦች ብዛት በግማሽ ያህል ቀንሷል። በርካታ ትላልቅ የምዕራባውያን የመርከብ መስመሮች መርከቦቻቸውን በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ዙሪያ ለማዞርም ተገደዋል፤ በዚህም የባሕር ላይ የቆይታ ጊዜያቸው (እስከ 17 ሰዓታት) ጨምሯል፡፡ ይህ ሁኔታ ጉዳቱ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም በቀይ ባሕር ዙሪያ ላሉ ሀገሮች ያለው ተፅዕኖ ደግሞ የበለጠ ጉልህ ሆኗል።
ሃውቲዎች በቀይ ባሕር ማጓጓዣ ላይ የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች በጂኦ -ኢኮኖሚያዊ ግጭት ውስጥ አዲስ ክስተትንም አምጥቷል፡፡ በእስያ እና በአውሮፓ መካከል ያለው ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ እንዲዛባ አድርጓል፡፡
እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት የተቃወሙ ሀገራት መርከቦቻቸው ከሃውቲ ጥቃቶች ነፃ በመሆናቸው ቀደም ሲል ሲያገኙት የነበረው ጥቅም ባለበት የቀጠለ ሲሆን በአንፃሩ እስራኤልን በሚደግፉ ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ የመርከብ ኩባንያዎች ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል። እ.አ.አ በ1973 በነበረው የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት ጊዜ በእስራኤል ደጋፊዎች ላይ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ለማድረስ ከተጣለው የአረብ ዘይት እገዳ ጋር ተመሳሳይ ተጽዕኖ እንዳለው ነው አረብ ሴንተር ዲሲ ኦርግ ላይ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው።
በተመሳሳይ የግብፅ ባለስልጣናት በሃውቲ ጥቃቶች ከባድ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ነው የሚናገሩት፡፡ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደል አቲ በቀይ ባሕር በኩል ባለው ውጥረት ምክንያት ባለፈው ዓመት ብቻ የግብፅን ኢኮኖሚ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንዳሳጣው መናገራቸውን ማሪታይም ኤክስክዩቲቭ ዘግቧል። በተጨማሪም የቀይ ባሕር እገዳ የእስራኤልን ምጣኔ ሀብት ጎድቶታል። በዋነኛነት መኪናዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እና የፖታሲየም ማዳበሪያን ወደ እስያ ፓስፊክ ክልል የሚልከው የኢላት ወደብ ብቻ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ቀጥተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ደርሶበታል።
ከ14 በመቶ በላይ የዓለማችን ንግድ በቀይ ባሕር በኩል የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም