ችግሩን በዘላቂነት የመፍታት ጥረት አስፈላጊነት

0
142

የአማራ ክልል ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት፣ 177 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዓመታዊ የዝናብ መጠን እና በአምራች ዜጋ የታደለ ስለመሆኑ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ መረጃ ያመላክታል:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን አምራች እጆች ጠባቂ እየሆኑ መጥተዋል:: ለዚህም መፍትሔ ርቋቸው የቀጠሉ ግጭቶች ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ በማድረጋቸው ሕይወት እንዲፈተን፣ መሬት ጾም እንዲያድር አድርገዋል::

የተፈጥሮ ፊቷን ማዞር የዜጎች የምግብ ዋስትና ፈተና እንዲሆን አድርጎታል:: ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ጎርፍ፣ የዝናብ እጥረት ለዚህ ማሳያ ናቸው:: ከምንም በላይ ግን በዝናብ እጥረት ምክንያት ባለፈው ዓመት የተከሰተው ድርቅ ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ አምራች እጆች ለምጽዋት መዘርጋታቸውን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ማስታወቁ አይዘነጋም::

በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች ተከስቶ የነበረው ድርቅ አርሶ አደሩ እንዲራብ ከማድረጉም በተጨማሪ ሕጻናት ከትምህርት እንዲርቁ፣ እንስሳት እንዲሞቱ እና እንዲሰደዱ አድርጓል:: የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ለተጎጂ ወገኖች የዕለት ደራሽ ምግብ በማቅረብ ችግሩ ሊያደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነሱን አስታውቆ ነበር:: ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም በመኸሩ ወቅት ችግሩ ያጋጠማቸው አርሶ አደሮች ወደ ልማት እንዲገቡ የዘር ድጋፍ መደረጉም አይዘነጋም::

የድርቁ ተጽእኖ ግን አሁንም በአሳሳቢነቱ ቀጥሏል:: ችግሩ ከበረታባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜን ወሎ ዞን ይገኝበታል:: የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለሙ ይመር እንደሚሉት በዞኑ ያለው የተረጂ ቁጥር በ80 በመቶ ቢቀንስም አሁንም በከፋ የምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች አሉ:: የጸጥታ ችግሩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በወቅቱ እንዳይደገፉ አድርጎ መቆየቱንም የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅት በቡግና ወረዳ ለሚገኙ 110 ሺህ 563 ዜጎች እርዳታ እየተጓጓዘ እንደሚገኝም አስታውቀዋል::

የቡግና ወረዳ ለአንድ ዓመት ያህል በክልሉ በተከሰተዉ ግጭት ዉስጥ መቆየቱን አስተዳዳሪው አቶ ጌታዬ ካሳው አስታዉሰዉ፣ ይህም ምንም አይነት የግብርና ግብዓት ወደ ወረዳው እንዳይገባ፣ ሰብዓዊ እርዳታውም እንዲስተጓጎል ማድረጉን አስታውቀዋል:: እነዚህ ችግሮች የወረዳው ነዋሪዎች ለረሀብ እና ለበሽታ እንዲጋለጡ እንዳደረጋቸው   ጠቁመዋል:: ባሁኑ ወቅት ግን ሰብዓዊ እርዳታ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል::

የዞኑ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ሀብታሙ አዱኛ በበኩላቸው እንዳስታወቁት ሁለት ሺህ 294 ሕጻናት በአጣዳፊ የምግብ ችግር እንዲሁም 39 ሺህ 156 ሕጻናት በመካከለኛ ደረጃ የምግብ እጥረት ውስጥ ይገኛሉ:: ከእነዚህ ሕጻናት ውስጥ 49 በመቶው በቡግና ወረዳ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል:: በጸጥታ ችግሩ ምክንያት አልሚ ምግቦችን በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሉ የተፈጠረው ክፍተት በሕጻናት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በአሁኑ ወቅት አልሚ ምግብ እና ክትባት ለመስጠት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው::

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽንም ለችግሩ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል:: የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሰርክ አዲስ አታሌ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም  በሰጡት መግለጫ  በቡግና ወረዳ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት 110 ሺህ ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አረጋግጠዋል::

በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የሚያስፈልገው የአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት የታወቀው በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ መሆኑንም  ገልጸዋል:: ችግሩ በነዋሪው ዘንድ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ፈጣን ሰብዓዊ ምላሽ እንዲሰጥ  መሥሪያ ቤታቸው ለፌዴራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማሳወቁን ጠቁመዋል::

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመላክተው  ከኮምቦልቻ መጋዝን አራት ሺህ 146 ኩንታል ስንዴ እና 414 ነጥብ ስድስት ኩንታል አልሚ ምግብ ወደ ወረዳው እያጓጓዘ መሆኑን አስታውቀዋል:: በዓለም የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ በዓለም ምግብ ድርጅት፣ በቀይ መስቀል እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በኩል የቀረበው ድጋፍ ወደ አካባቢው ደርሶ ለተጠቃሚዎች መሰራጨቱን አስታውቀዋል::

በክልሉ ያለው የሰላም እጦት እርዳታ ለማድረስ በርካታ ክፍተቶች መፍጠሩን ምክትል ኮሚሽነሯ  ጠቁመዋል::  በቀጣይም አንጻራዊ ሰላም በሚኖርባቸው አካባቢዎች መሰል ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል:: ኮሚሽኑም በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ለመሥጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል::

ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀንን ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ዓ.ም አክብሮ በዋለበት ወቅት እንደተገለጸው በክልሉ ከ700 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ:: ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያ እና ከማኅበረሰቡ ጋር እንደሚገኙም ተመላክቷል::

የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ማረጋገጥ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋና መውጫ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል አስታውቀዋል:: እያንዳንዱ ወረዳ እና ዞን በምግብ ራስን ለመቻል ብሎም የአደጋ ምላሽ ለመስጠት ማልማት ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ተመላክቷል::

ኮሚሽነሩ እንዳሉት የመረዳዳት ሥነ ልቦናን ማሳደግ፣ ከድህነት የሚያወጡ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ  ማስቀጠል፣ ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል:: የርዳታ ድርጅቶችም ርዳታ ከመስጠት ባሻገር ልማት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ ተጠይቋል::

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለ ማርያም (ዶ/ር) ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ሰብዓዊ ርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል በቂ ክምችት እና የተሟላ ዝግጅት አለ:: ባሁኑ ወቅት በሁሉም አካባቢዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለይቶ ተደራሽ የማድረግ  ሥራ እየተከናወነ ነው:: ለአብነት  በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ  የነበረው የጸጥታ ችግር ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል:: ባሁኑ ወቅት ግን ሰብዓዊ ድጋፉ  ተደራሽ ሆኗል::

በአጠቃላይ እንደ ሀገር ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በዘላቂነት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ታውቋል:: በዚህም ከ2016/17 እስከ 2017/2018 የምርት ዘመን 253 ሺህ ሄክታር መሬት በማረስ 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በማምረት መጠባበቂያ ክምችት ለመያዝ በትጋት እየተሠራ ነው ብለዋል:: እስካሁንም 108 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን አስታውቀዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here