በዓላት እና የቱሪዝም መነቃቃት

0
134

ወርልድ ቱሪዝም በድረ ገጹ እንዳስነበበው የሰው ልጅ በሕይዎት ዘመኑ ሊጎበኛቸው እና ሐሴት ሊያገኝባቸው ከሚገባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ ጸጋዎች እንዳሏት በማንሳት በተለይ ደግሞ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን “የሰው ልጅ በሕይዎት ዘመኑ ሳይጎበኛቸው ማለፍ እንደሌለበት  ነው “የግድ መጎብኘት ያለበት” ሲል ያመላከተው።

የበርካታ ጸጋዎች ባለቤቷ ኢትዮጵያ ታዲያ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት ሕንጻዎችን፣ የጣና ገዳማትን እና የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ በርካቶችን በዓለም የቅርሶች መዝገብ በማስመዝገብ ለዓለም አበርክታለች፤ የጉብኝት ማዕከላትም ናቸው።

የተትረፈረፈ የቱሪዝም ጸጋ ባለቤቱ የአማራ ክልል ደግሞ በተለይ በታኅሣሥ እና በጥር  ቱሪዝሙ ይበልጥ የሚነቃቃበት ነው። ለአብነትም ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር እና በምንጃር እንዲሁም ጥርን በባሕር ዳር ልዩ ድምቀት የሚታይባቸው ናቸው።

ይህን ታሳቢ በማድረግ ታዲያ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ነው የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ያስታወቀው። የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃትም  የሆቴል እና ቱሪዝም ጥምረት መመሥረቱ ተነግሯል።

በክልል ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ሃብት  በተገቢው መንገድ በማልማት እና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ  አልሞ ነው የተመሠረተው።

የበዓላት ወቅት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ጎብኚዎች በስፋት ወደ ክልሉ እንዲገቡ እየሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፤ ክልሉ ባለፉት ዓመታት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በጦርነት እና በግጭት ምክንያት የጎብኚዎች ፍሰት ቀንሶ ቆይቷል:: በመሆኑም ፍሰቱ ወደ  ቀድሞ ከፍታው ለመመለስ እንዲቻል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ነው ቢሮው ያስታወቀው።

በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም እንደተናገሩት አማራ ክልል ካለው ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ የመስህብ ሀብቶች ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራት ይገባል። አሁን ክልሉ ካለው አንጻራዊ ሰላም በመነሳት በወረርሽኙም ሆነ በሰላም እጦቱ ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት ጎብኚዎች ወደ ክልሉ እንዲመጡ በስፋት እየተሠራ ነው።

በታኅሣሥ ወር መጨረሻ እስከ የካቲት ወር ድረስ በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሁነቶች እንደሚካሄዱ የገለጹት ዳይሬክተሩ እነዚህን ሁነቶች ተጠቅሞ ቱሪዝሙን ማነቃቃት ያስፈልጋል ብለዋል:: በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ፣ የጥምቀት በዓል በጎንደር እና በምንጃር፣ የአስተርዮ በዓል በመርጡ ለማርያም እና በደብረ ወርቅ፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ ብሔረሰብ፣ የመርቆሪዎስ ዓመታዊ በዓል በደብረ ታቦር፣ የግሽ ዓባይ (ሰከላ) ዓመታዊ በዓል ከተያዘው ወር ጀምሮ አስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ በድምቀት የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት ናቸው፤ በመሆኑም እነዚህን  ታላላቅ ሁነቶች በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ ዳይሬክተሩ እስገንዝበዋል።

እንደ አቶ መልካሙ ማብራሪያ ቢሮው ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመሆን ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፤ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ ገብተው እንዳይጉላሉ በየመዳረሻዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።።

(ጌትሽጌትሽ ኃይሌ )

በኲር የታኅሳስ 21  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here