ዝነኛው ባህላዊ ስፖርት

0
213

በሀገራችን ዝነኛ ከሆኑት የባህል ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው የገና  ጨዋታ መቼ እንደተጀመረ የሚገልጽ ትክክለኛ መረጃ የለም። ይሁን እንጂ ከክርስቶስ ልደት በፊት እረኞቹ በተለይ በበጋው ወቅት ከብት እየጠበቁ ይጫወቱ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

የክርስቶስ ልደትን /የገና በዓልን/ ምክንያት በማድረግ እረኞች የገና ጨዋታን ከታህሣሥ ጀምሮ እስከ ጥር እና ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ይጫወቱት እንደነበር አባቶች ይናገራሉ:: ታዲያ ይህ ጨዋታ አዝናኝ እና ተወዳጅ በመሆኑ ዘር ፣ የሀብት ደረጃ ፣ የሥራ ኃላፊነት፣ እና ሌሎች ልዩነቶች ሳይኖሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በፍትሐዊነት ያሳትፍ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ የገና ስፖርት ጨዋታ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ረቂቅ ደንብ ወጥቶለት ውድድሩ እየተደረገ ይገኛል። በስፖርታዊ ውድድር የተካተተው ዘመናዊው የገና ጨዋታ ከመጫዎቻ ሜዳው ቅርጽ ጀምሮ በዳኞች ብዛት እንዲሁም በሌሎች መስፈርቶች ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋር ተቀራራቢ ነው።

በአጠቃላይም ሰባት ያህል ሕግና ደንቦች ተዘጋጅተውለታል።  በገና ጨዋታ ላይ ተጠባባቂዎቹን ጨምሮ እያንዳንዱ ቡድን አስራ አምስት ተጨዋቾች ሊኖሩት ይገባል፣ ወደ ሜዳ የሚገቡት ግን አስሩ ብቻ ይሆናሉ፣ ቀሪዎቹ አምስቱ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ይቀመጣሉ። ጨዋታውን የሚመራ የመሐል ዳኛ እና ረዳት ዳኞችም ይኖሩታል።

የገና ጨዋታን ለመጫወት “ሩር” እየተባለች የምትጠራ ድቡልቡል መጫዎቻ ኳስ ታስፈልጋለች፣ ክብደቷም እስከ አምስት መቶ ግራም የሚመዝን ሲሆን ከእንጨት፣ ከፕላስቲክ ይዘጋጃል። ሩርን ለመምታት እና ወደ ተቃራኒ ቡድን ለማስገባት ልክ እንደ ማንኪያ ቅርጽ ያለው ከአንድ ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው ዱላም ያስፈልጋል።

የገና ዱላውም ለሁሉም ተሳታፊዎች በእኩል ቁመት የተዘጋጀ ነው። በአጠቃላይም ለስድሳ ደቂቃ ጨዋታው ሲከናወን በመሐል አጋማሽ ላይ ተሳታፊዎቹ ለአስር ደቂቃ እረፍት የሚያደርጉ ይሆናል። ጨዋታው የፍፃሜ ወይም የደረጃ ከሆነ እና ቡድኖቹ ካልተሸናነፉ ተጨማሪ ደቂቃ እና ቅጣት ምት ይሰጣል። ስፖርቱ ልክ እንደ እግር ኳስ ስፖርት በዚህ መልኩ ይከናወናል።

በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ዜጎች በባህላዊ ስፖርት መሳተፍ እንዳለባቸው የተጠቆመ ቢሆንም ዘርፉ ከመንግስት እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ግን በቂ እንዳልሆነ ይነገራል። የገጠሩ ማሕበረሰብ ክፍል የገና ስፖርት ጨዋታ ባለቤት ቢሆንም በስፖርቱ ግን ተጠቃሚ አለመሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው።

የስፖርት ምክር ቤት በየዓመቱ የስፖርት ሀብት ገንዘብ ሲሰበሰብ ከአርሶ አደሩም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚሰበሰብ ከዚህ በፊት በነበሩት የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ሰምተናል። ታዲያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለስፖርቱ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለሚያደርገው የገጠሩ ማህበረሰብ ስልጠና በመስጠት እና ግንዛቤ በመፍጠር በዘርፉ ማሳተፍ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነው የገና ስፖርት በቂ ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑ አያጠያይቅም። በየዓመቱ በሚደረጉ የባህል ስፖርቶች ውድድር ምክንያት የገና ስፖርት ትንሽ መነቃቀት ቢያሳይም በተፈለገው ልክ ግን እያደገ አይደለም። ስፖርቱን በተሻለ ለማሳደግ እና ለማስተዋወቅ በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ብዙ ሥራዎች መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም እና አህጉር አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት የባህል ስፖርቷን ያስተዋወቀችበት እና የተሳተፈችበት ጊዜ እንደ ነበር ታሪክ ያስረዳል። ታዲያ የገና ስፖርትን ለማሳደግም አሁንም ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እና ስፖርት በዓሎችን በማዘጋጀት ስፖርቱን የማስተዋወቅ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል።  በመላው ጨዋታዎች ፣ በትምህርት ቤት ውድድር ተካቶ እንዲካሄድ መደረጉ ስፖርቱን ከማሳደግ አንፃር መልካም ጅምር ቢሆንም አሁንም ግን ብዙ ሥራ ይጠይቃል።

የገና ስፖርት የአንድን አካባቢ ባህል፣ ትውፊት፣ ወደ ሌላው አካባቢ ለማወራረስ እና ያልተበረዘውን የኢትዮጵያውያንን ማንነት ለማንፀባረቅ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል፣ ይህ ደግሞ የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።  ለስፖርቱ መወዳደሪያ የሚሆን የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት የስፖርት ቁሳቁስ እጥረትም ይስተዋላል።

ማሕበረሰቡ እና በየደረጃው የሚገኙ የስፖርት ባለሙያዎች የባህል ስፖርቶችን ልክ እንደ ዘመናዊ ስፖርቶች እኩል ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።  በየአካባቢው የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ  ጥናት እና ምርምር በማድረግ ስፖርቱን ለማሳደግ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

የገና ስፖርት በስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ከታች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ቢሰራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችንን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ብቁ ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል። ይህን ለማደረግ የሚቻለው ግን ስፖርቱን በተሻለ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ብቁ እና የሰለጠኑ  ዳኞች፣ አሰልጣኞች እና ባለሙያዎች ሲኖሩን መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የገና ስፖርት እንደ ሌሎቹ የስፖርት ዓይነቶች የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትን በማቅራረብ የአካባቢውን ባህል እና ወግ በማስተዋወቅ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።

በዘመናዊ ስፖርቶች የሚታየው የሥነ ምግባር እና ሥነ ስርዓት ግድፈት በገና ስፖርት ጨዋታ እንደሌለ መረጃዎች ያመለክታሉ። በጨዋታ ወቅት ተጫዋች ቢጎዳ መክሰስ፣ መካሰስም የተከለከለ ነው፤ ማን እንደጎዳውም ማረጋገጥ አይቻልም፣ ተሸናፊው ቡድንም ውጤቱን በፀጋ ይቀበላል። ይህም ለሌሎቹም ስፖርቶች አስተማሪ መሆኑ በብዙዎቹ ዘንድ ተመስክሮለታል።

የገና ስፖርት ጨዋታ በይበልጥ መዘውተር የጀመረው በተለይ በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ መረጃዎች ያስነብባሉ:: በወቅቱ ብዙ ዓይነት ውድድር ይደረግበት ነበር፤ ለአብነት ቁርቁዝ፣ ሙጭ፣ ቀልቦ መለጋት እና አፍሶ መለጋት የመሳሰሉት ይገኙበታል:: ከገና ጨዋታቸው በኋላ ጐልማሶች በምሽት በየቤቱ በመዟዟር  ይጨፍሩ እንደነበር ተነግሯል:: የገና ጨዋታ ዛሬ በዓለም ዘንድ በጣም ተፈላጊ ከመሆን ደረጃ አልፎ ተርፎ በኦሎምፒክ ከሚደረጉት ውድድሮች አንዱ ለመሆን በቅቷል::

ባህላዊው የገና ጨዋታ ለዘመናዊ ስፖርትም መነሻ እንደ ሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያውያኑን የገና ስፖርት ካናዳውያን በዘመናዊ መንገድ በማሻሻል የበረዶ ሆኪ በሚል ስያሜ እ.አ.አ 1875 ገደማ በሀገራቸው አስተዋውቀውታል። የበረዶ ሆኪ ስፖርት ከገና ስፖርት ጋር ተመሳሳይ ነው።

ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በካናዳ ክለብ ተቋቁሞ የሊግ ጨዋታዎች መደረግ ጀምረዋል። ከዛ በኋላም በእንግሊዝ፣ በአየርላንድ እና በሌሎችም የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ስፖርቱ ሊስፋፋ ችሏል። እ.አ.አ ከ1920 ጀምሮ ስፖርቱ በኦሎምፒክ ተካቶ እየተካሄደ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በፓራለምፒክም ውድድር በመካተቱ ተወዳጅ ስፖርት ለመሆን በቅቷል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here