አሜሪካውያኑ ጥንዶች በ1951 እ.አ.አ ተጋብተው አራት ልጆች ወልደው በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት በ1975 ፍቺ ቢፈፅሙም ከሀምሳ ዓመታት በኋላ እንደገና መጋባታቸውን አሶሼትድ ኘሬስ ከሳምንት በፊት አስነብቧል::
ፋያ ጋብል እና ወይዘሪት ሮበርት ዊንሪች የመጀመሪያ እለት ትውውቃቸው ታላላቅ ወንድሞቻቸው ጓደኛሞች ስለነበሩ ከእነሱ ጋር በአንድ ላይ በተገናኙበት ወቅት ነበር:: ያኔ ፋይጋ ብል ወይዘሪት ሮበርት ዊንሪችን ሊያገባት እንደሚፈልግ እንደነገራቸው ከወንድሞችዋ ተረድታለች::
ቀኑ ደርሶ ሁኔታው ፈቅዶላቸው በወርሃ ህዳር 1951 እ.አ.አ ጋብቻቸውን ፈፀሙ:: በትዳር ባሳለፉባቸው 24 ዓመታት አራት ልጆች አፍርተው መወያየት መነጋገር መተማመን ባለመቻላቸው በተፈጠረ ጊዜያዊ ግጭት በ1975 እ.አ.አ ፍቺ መፈፀማቸውን አውስተዋል::
የተለያዩት ፋይ ጋብል እና ወይዘሮ ዊንሪች ሁለቱም አጣማጅ ቢጢያቸውን አፈላልገው ትዳር መስርተው የአቶ ፋይጋብል ሚስትም ሆኑ የወይዘሮ ሮበርት ዊንሪች ባል በሞት እስከ ተለዩበት ጊዜ ድረስ እንደወንድም እና እህት በየማህበራዊ ግንኙነቶች ሳይራራቁ ቆይተዋል:: ኃላም የነበራቸው መልካም ግንኙነት ሳይላላ መልሰው በትዳር ዳግም ለመጣመድ ይወስናሉ::
ስለ አባት እና እናቷ የሁለቱ በእድሜ ትንሿ ሴት ልጅ የሆነችው ካሮል ስሚዝ “ሁለቱም ልክ በፍቅር ህይወት ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች ነው የሚመስሉት፤ ይተሳሰባሉ” ስትል ነበር የግንኙነታቸውን ጥብቅነት የገለፀችው:: አዛውንቱ ፋይጋብልም “በህይወቴ የፍቅር መጀመሪያዬ እሷ ነች፤ እንደገና እንገናኛለን እንጋባለን ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፤ አሁን ግን ሁሉንም ነገር ተመቻችቷል ጊዜ አላባክንም”:: በማለት መወሰናቸውን አስረድተዋል::
ዳግም ለመጋባት ሲወስኑ እድሜያቸው አዛውንቱ አቶ ፋይጋብል 94 የቀድሞዋ ሚስታቸው የነበሩት የነገዋ ሙሽራ ሮበርት ዊንሪች ደግሞ 89 ላይ ናቸው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም