የሎውስቶን ብሔራዊ ፓርክ በአሜሪካ የሚገኝ መጋቢት 1/1872 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የተመሰረተ የመጀመሪያው ፓርክ ነው:: አጠቃላይ ስፋቱ 8991 ኪሎ ሜትር ስኩዌር፤ መገኛ ከፍታው ደግሞ 2470 ሜትር ተለክቷል::
ለፓርኩ መመስረት የዱር አራዊት፣ ፍልውኃ፣ ወንዞች፣ ኃይቆች፣ ሸለቆ እና ደን የለበሱ ሰንሰለታማ ተራራዎች መገኛነቱ ዋነኛ ምክንያቶች ሆነው ተጠቅሰዋል::
የሎውስቶን የሚለው የፓርኩ መጠሪያ በቀጣናው በሸለቆዎች መካከል የሚያልፈው ወንዝ መውረጃው ንጣፍ ቢጫ ቀለም ያለው አለት ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው በድረ ገፆች የሰፈረው::
የፓርኩ ሰፊ ክልል የዋዮሚንግ ግዛትን ቢሸፍንም ወደ አጐራባች ሞንታና እና ኢዳሆ ቀጣናዎችም ይዘልቃል::
በፓርኩ 67 አጥቢ እንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ፣ ከነዚህ መካከል ተኩላ፣ ጎሽ፣ ድብ፣ አጋዘን፣ጥንቸል ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው::
በፓርኩ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ የእፅዋት ዝርያዎች እንደሚገኙም ተመዝግቧል:: ከነዚሁ መካከል አብዛኛዎቹ በዛው በአሜሪካ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው የተጠቀሰው፤ ሰፊው ቀጣና ግን ጫፋቸው ሽቅብ በሾጠጡ የጥድ ዝርያ የተሸፈነ ነው::
በአበዛኛው ተፈጥሯዊ ደን በሚበዛባቸው ጥብቅ ቀጣናዎች የሰደድ እሳት መከሰት ተጠባቂ ሁነት ነው:: በመሆኑም በየሎውስ ቶን ፓርክም በአብዛኛው መብረቅ መነሻ መንስኤአቸው የሆኑ የሰደደ እሳት ቃጠሎዎች ከ20 እስከ 25 ዓመታት በሚደርስ ልዩነት ተከስቷል::
በፓርኩ ከፍተኛ ቦታዎች ቀዝቃዛ ዝቅተኛዎቹ ደግሞ ሞቃት ዓየር ንብረት አላቸው:: ከፍተኛው ሙቀት 37 ዲግሪ ሴንት ግሬድ በ2002 ቀዝቃዛው ደግሞ ከዜሮ በታች 54 ዳግሪ ሴንትግሬድ ወይም በ1933 እ.አ.አ ተመዝግቧል::
የፓርኩ ክልል የዝናብ መጠኑ ከ380 ሚሊ ሜትር እስከ 2000 ሚሊ ሜትር ተመዝግቧል:: በአብዛኛዎቹ ቅዝቃዜ ባለባቸው ወራት በረዶ እንደሚነጥፉባቸውም ነው ድረ ገፆች ያመላከቱት::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት – የሎውስቶን ናሽናል ፓርክ፣ ኤንፒ ኤስ፣ የሎውስቶን ናሽናል ፓርክ ሎጂ እና ዊኪፒያን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም