የአፍሪካው ቼ ጉቬራ

0
190

… ካለፈው የቀጠለ

በመጀመሪያው ክፍል ፅሑፍ ስለ ቶማስ ሳንካራ የልጅነት ህይወት፣ የትምህርት ሁኔታ፣  ስለወታደራዊ ህይወቱ እና የሃገር መሪነት አጀማመሩ አስነብበናል። ቀጣዩ እና የመጨረሻው ክፍልም እንደሚከተለው ተዘጋጅቶ ቀርቧል።

መልካም ንባብ!

ነሐሴ 4 ቀን 1983 ዓ.ም ስልጣን የጨበጠው ሻምበል ቶማስ ሳንካራ ወታደራዊ መንግሥት ‹‹አብዮታዊ›› ስርዓት አወጀ፡፡ አብዮቱን የመምራት ኃላፊነት ተረከበ። በ33 ዓመት ዕድሜው ግዙፉን ስልጣን የተሸከመው ሻምበል ቶማስ ሳንካራ በጊዜው በአፍሪካ በዕድሜ ወጣቱ መሪ ሁኖ ተመዝግቧል፡፡ በሕዝባዊ ድጋፍ የፕሬዝዳትነት ኃላፊነቱን ከተቆናጠጠ በኋላ በፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል በሀገሪቱ ዕድገት ለማምጣት ቃል ገባ፡፡ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ እና ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገር ለመፍጠር ልዩ የሆነ የባህል አብዮት ለማካሄድ ቆርጦ ተነሳ፡፡

ጥቅምት 2 ቀን 1983 ዓ.ም በሳንካራ የትግል ጓዱ የተዘጋጀ የአዲሱን አብዮት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሚያስተዋውቅ መግለጫ በብሔራዊው የራዲዮ ስርጭት ተላለፈ፡፡ ይህ የአምስት ዓመቱ የልማት እቅድ እያንዳንዱ ዜጋ የተሻለን ነገ ለመፍጠር ዛሬን በድፍረት በልማት ዘመቻ መትጋት  እንደሚገባው ገለጸ፡፡

ሻምበል ቶማስ ሳንካራ ሀገሩን ማስተዳደር ሲጀምር የወሰደው ቀዳሚው እርምጃ ከፊደል ካስትሮ፣ ቼጉቬራ፣ ከጋናው ወታደራዊ መሪ ጄሪ ሮውሊንግ፣ ከሊቢያው ሶሽያሊስት መሪ ሙአማር ጋዳፊ እና መሠል ኢምፔሪያሊዝምን ለአርነታቸው ለመፋለም ከተነሳሱ አብዮታዊ የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም ከሚከተሉ መንግሥታት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናከረ፡፡ በተመሳሳይም ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነት መሰረተ፡፡ ሳንካራ በአመራር ዘመኑ ኮሙኒስት ቻይናን እና የቀድሞዋን ሶቭየት ኅብረትን ጨምሮ በርካታ አብዮታዊ አስተሳሰብ አራማጅ ሀገሮችን ትኩረት ሰጥቶ ጎብኝቷል፡፡

ሳንካራ የውጭ እርዳታ ህዝቡን ከማስነፍ ባለፈ በእርዳታ እና በብድር ስም ወደ እጅ አዙር ቅኝ ግዛት ስለሚወስድ፣ ከነጮች የእርዳታ ፍርፋሪ እና መመሪያ መቀበል በማቆም የሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮችን ማሳደግ ላይ ትኩረት አደረገ፡፡ ከእርሱ የቀደሙት መንግሥታት የወሰዱት ብድር የስርዓቱ እንጂ የአፐር ቮልታ ብድር አለመሆኑን በይፋ አወጀ፡፡

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሻሻል በግብርና፣ በአስተዳደር፣ በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ከፋፍሎ የሕዝቡን ሕይወት ለማሻሻል ወገቡን ታጥቆ ወደ ትግል ገባ፡፡ ይህንን ለማስፈጸም ደግሞ በአብዮታዊ ፖሊሲው ላይ ግንዛቤ ማሳደግ፣ ደን ልማትን ጨምሮ አካባቢን ማሻሻል እና ጾታና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያሉትን መዋቅሮች ትኩረት ሰጠ፡፡ ምሁራን እና የስነ ዜጋ ትምህርትን ደግሞ ህብረተሰቡን በዘመቻ ወደ ልማት እንዲሰማራ ንቅናቄ እና ግንዛቤ ለመፍጠር ይጠቀምባቸው ነበር፡፡

ሻምበል ሳንካራ ሥራውን የየጀመረው “አፐር ቮልታ” የሚለውን ቅኝ ገዥዎች ያወጡትን የሀገሪቱን መጠሪያ በመቀየር ነበር። ለሀገሩ ታሪኳን የሚመጥን እና አፍሪካዊነትን የሚያንጸባርቅ  የክብር ስም “ቡርኪናፋሶ” ሲል ደረበላት፤ “የቀና ሕዝብ መኖሪያ ምድር” እንደማለት ነው፡፡ ስያሜው ሕዝቡ ሀገሩን ወዳድ እና በሥነ-ምግባር የታነጸ ትክክለኛ፣ እውነተኛ ማህበረሰብ መሆኑን ለመግለጽ የታሰበ ነበር፡፡ ዜጎቿም ቦርኪናቤ ተብለው እንዲጠሩ አደረገ፡፡ “ቀና ሰዎች” እንደማለት ነው፡፡

ሀገርን እና ሕዝብን ለመለወጥ የሚንቀለቀል ውስጣዊ ጉጉት ሰንቆ የተነሳው ወታደሩ ሳንካራ በሚወደው ጊታር ታግዞ ጣፋጭ ብሔራዊ መዝሙር እና ሰንደቅ ዓላማ አዘጋጅቶ አበርክቷል፡፡ ምናልባትም በዓለማችን የብሔራዊ መዝሙር እና ሰንደቅ ዓላማ በማዘጋጀት የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሳይሆን አይቀርም ይሉለታል፡፡

ከ23 ዓመታት በፊት ቡርኪናፋሶ ከፈረንሳይ ነፃነቷን ብትቀዳጅም ቅሉ ከነፃነት በኋላ እንኳ ቅኝ ገዥዋ ከጀርባ ሀገሪቷን ትዘውር ነበር፡፡ ቶማስ ሳንካራም ሀገሩን በመሪነት በተረከባት ወቅት በፈረንሳይ የምትበዘበዝ፣ ሙስና እና ማህይምነት የተንሰራፋባት፣ በድህነት ከሚማቅቁ የዓለማችን ሀገራት ቀዳሚ ነበረች፡፡ በወቅቱ ማንበብ እና መጻፍ የሚችለው የሀገሪቱ ሕዝብ አስር በመቶው ብቻ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ቦርኪናፋሶ በምዕራብ አፍሪካ ከፍተኛ የሕጻናት ሞት መታወቂያዋ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር ሳንካራ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘውን ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ ከጨለማው መጋረጃ ለማውጣት ወጣ ባሉ ዕቅዶች የባህል አብዮት ለማካሄድ ቆርጦ የተነሳው፡፡ በ1984 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት ባደረገው ንግግር ‹‹የሀገሬ ሰባት ሚሊዮን ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት ከአሁን በኋላ በድንቁርና፣ በረሃብም ሆነ በዉሃ ጥም አይሞቱም! አመራራቸው በሚያካሂደው የሞት ሽረት ትግል የቡርኪናቤዎችን ሕይወት ይታደጋል፤ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃም ያሻግራል!›› በማለት ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል፡፡

ሳንካራ በአብዮታዊ ትግሉ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት፣ ያረጀ እና ያፈጀ ሥርዓትን ለማፍረስ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጀ፡፡ በኢኮኖሚ የደቀቀች ሀገሩን በሶሽያሊስት ርዕዮተ-ዓለም መሪነት በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ልማት ለማየት ጓጓ፡፡

በመሆኑም ድሃው ሕዝብ በምግብ ራሱን እንዲችል፣ የአስተራረስ ዘዴው እንዲሻሻል በማስተማር በመስኖ እና በዝናብ መሬቱን እንዲያለማ ጥብቅ ትዕዛዝ አሰተላለፈ፡፡ አርሶ አደሩ በሚያካሂደው የልማት ዘመቻ ባለስልጣናት፣ ወታደሩ እና የከተማው ነዋሪ ድጋፍ እንዲያደርግ በጥብቅ አውጇል፡፡ ሳንካራ ለአንድ ፕሬዝዳንት የሚገባውን ክብር እና ምቾት አሽቀንጥሮ በመጣል ዶማ እንዲሁም አካፋ ይዞ በመውጣት በመስኖ ልማት፣ በውኃ ጠለፋ እና በእርሻ፣ በሌሎች በዘመቻ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ላይ ራሱ በተግባር በመሳተፍ ለሚኒስትሮቹ አርአያ ሆኖ ይታይ ጀመር፡፡

በቦርኪናቤዎቹ ድህነት የቅንጦት አኗኗርን በማውገዝ ከአለባበስ ጀምሮ ቀላል የሕይዎት ዘይቤን ለሕዝቡ እንዲሁም ለባለስልጣናቱ ራሱን በተግባር አስቀድሞ በማሳየትም ጀመረ። ምስኪኑ የቦርኪናቤ ገበሬ ባመረተው ጥጥ ቦርኪናቤው ሸማኔ የሰራውን የባህል ልብስ እንዲጠቀሙ አዘዘ፡፡ ዓላማው ሕዝቡ የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀም በማበረታታት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መገደብን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ራሱም ሳንካራ በሀገር ውስጥ ልብስ አሸብርቆ በመታየት በራስ ምርት መኩራት እንደሚቻል አሳይቷል፡፡

ሙስና እና ሌብነትን የሚጠየፈው ሳንካራ ባለስልጣናትም ቢሆኑ የላባቸውን ብቻ ማግኘት እንዳለባቸው ሰበከ፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በተቃራኒ የራሱን ወርሃዊ ደሞዝ ወደ 450 ዶላር ዝቅ ካደረገ በኋላ የሌሎችን የመንግሥት ባለስልጣናት ደሞዝ እና ሌሎች የገቢ ምንጮችን በመቀነስ በጀቱን ለሕዝብ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ አዋለ፡፡

ከእርሱ በፊት የነበረው መንግሥት ይጠቀምባቸው የነበሩ ውድ እና ቅንጡ ተሽከርካሪዎች ከየመስሪያ ቤቱ ተሰብስበው እንዲሸጡ  በማድረግ በተራ ተሽከርካሪዎች ተክቷቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሲፈልግ በርካሽ በተገዛች አነስተኛ አሮጌ መኪናው፤ ሲያሻው ደግሞ ብስክሌቱን እየጋለበ ከቤቱ ወደ ስራ ቦታው ይመላለስ ነበር፡፡

ቶማስ ሳንካራ የራሱ የቤተሰብ አባላት እንኳ የተለየ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አይፈልግም ነበር። ቤተሰቡን በመሰብሰብ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ቤተሰብ አይነት የተለየ ጥቅም እንዳይጠብቁ አስቀድሞ አስጠንቅቋቸውም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ሁለት ልጆቹ ቀደም ሲል ከሚማሩበት የመንግሥት ትምህርት ቤት የቀጠሉ ሲሆን ቀዳማዊቷ እመቤትም በፊት ከነበራት የስራ ኃላፊነት ምንም የጨመረችው ደረጃ አልነበረም፡፡ ወላጆቹም ድሮ ከሚኖሩበት ሕይዎት ለውጥ አልነበራቸውም፡፡

መሬትን ከውጭ ኩባንያዎች እና ከመሬት ከበርቴው እጅ ፈልቅቆ በማውጣት ለአርሶ አደሩ አከፋፍሏል፡፡ አርሶ አደሩም የአስተራረስ ዘዴውን እንዲያሻሽል ድጋፍ ስለተደረገለት በሦስት ዓመት ውስጥ የሀገሪቱ የስንዴ ምርት በሄክታር ከነበረበት 1 ሺህ 700 ኪሎ ግራም ወደ 3 ሺህ 800 ኪሎ ግራም ከፍ ብሏል፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡርኪናፋሶ በምግብ ራሷን እንድትችል አስችሏታል፡፡ ከ1983 እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት ብቻ ሕዝቡ ባካሄደው “የግብርና ስራ ዘመቻ” የተገኘው ምርት ቀደም ሲል ከነበረው የምርት ምጣኔ 75 በመቶ ብልጫ ነበረው፡፡ በጊዜው ሕዝቡ የምዕራባውያንን እጅ ሳያይ፣ በሀገሩ ለምግብ ፍላጎት ከሚያስ ፈልገው መጠን በላይ የምግብ ሰብሎች አትረፍርፎ እንዲያመርት አስችሎታል፡፡

ሁሉም የቦርኪናፋሶ ሕዝብ እንደ ዜጋ ነፃ የትምህርት እና የጤና ሽፋን እንዲያገኝ በደነገገው አዋጁ የሚታወቀው ሳንካራ ማህበረሰቡ በአካባቢው ተደራጅቶ በራሱ ጉልበት ከ350 በላይ የትምህርት ተቋማት እንዲገነቡ አነሳስቷል፡፡ በመሆኑም 35 ሺህ ቦርኪናቤዎችን በሦስት ወራት ውስጥ ማንበብ እና መጻፍ እንዲችሉ አድርጓል፡፡ ትምህርትን በማስፋፋት 13 በመቶ የነበረውን የትምህርት ሽፋን በ1986 ዓ.ም ወደ 73 በመቶ አሳድጓል፡፡ ይህም የሳንካራ አስተዳደር በሀገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ ሕዝቡን ከመሃይምነት ለማላቀቅ ያደረገውን ውጤታማ ትግል ያሳየ ነው፡፡

ወጣቱ የሀገር መሪ ቶማስ ሳንካራ በጤናውም ዘርፍ በኅዳር 25 ቀን 1984 ዓ.ም የቦርኪናቤ ታዳጊዎች እና ሕፃናት የክትባት ዘመቻን አሳክቷል፡፡ በየመንደሮቹ የጤና ጥበቃ ማዕከላትን በማቋቋም በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የማጅራት ገትር፣ የወባ እና የኩፍኝ ክትባት እንዲወስዱ በማድረግ የጤና ሽፋኑን ወደ 60 በመቶ ያስመነደገ ተምሳሌታዊ ስራ አከናውኗል፡፡ ሳንካራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግዙፍ ብሔራዊ የክትባት ዘመቻ በማካሄድ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን ይዞ ነበር።

ወታደሩ፣ የኮማንዶ አዛዡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፕሬዝዳንቱ ቶማስ ሳንካራ በፀረ ቅኝ አገዛዝ እና በፓን አፍሪካኒስት አመለካከቱ በአመራር ዘመኑ ‹‹የሚመግባችሁ ይቆጣጠራችኋል›› እና ‹‹ለማኝ ለማንም መመኪያ አይሆንም›› በሚለው አመለካከቱ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት አስቁሟል፡፡

በሐምሌ ወር 1987 ዓ.ም ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት›› በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ ባካሄደው ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ባደረገው ንግግር “አፍሪካውያን ከምዕራቡ የተበደሩት ዕዳ አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ወቅት በአህጉሪቱ ለፈጸሙት የተፈጥሮ ሃብት ዝርፊያ እና የጉልበት ብዝበዛ ማካካሻ ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና ከሌሎች አበዳሪ ተቋማት ጋር ኢፍትሃዊ የብድር ስምምነቶችን በማድረግ ቀጣዩን ትውልድ በዕዳ ዘፍቀን የትውልድ ተወቃሽ መሆን አይገባም! ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በአፍሪካ ላይ ያላቸው የኢኮኖሚ ቁጥጥር የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ‹‹ኒዮኮሎኒያዝም›› አካል በመሆናቸው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት እና ከምዕራባውያን ሀገራት ያለብንን እዳ መክፈል አይገባንም፡፡

“ምክንያቱም አፍሪካውያን ዕዳቸውን ባይከፍሉ ምዕራባውያን አይሞቱም፣ አፍሪካውያን ዕዳቸውን ቢከፍሉ ግን ይሞታሉ፡፡ ስለዚህ መክፈል እንደማይገባ እያንዳንዳችን ድምፃችንን በጋራ ልናሰማ ይገባል፡፡  ብድር የሚሰጡን ከዚህ ቀደም በቅኝ ግዛት ስር አውለው ሲበዘብዙን የኖሩት ሀገራት ናቸው፡፡ ቅኝ ተገዝተን ተበዝብዘናል፤ ሀብታችንን ተዘርፈናል፡፡ ዛሬም ለደስታችን ብለን ያልተዋዋልነውን ዕዳ እንድንከፍል ይፈልጋሉ፡፡ ብድር ለሁለተኛ ዙር የየሀገራችንን የተፈጥሮ ሃብት ዘረፋ እንደ ሽፋን ነው” በማለት በስብሰባው የታደሙ መሪዎችን አስደምሟል፡፡

በአጭር ጊዜያት ውስጥ ራስን በምግብ የመቻል ስኬቱ እና የምዕራባውያንን ጉልበት ፊት ለፊት ታግሎ ድልን በመቀናጀቱ በአፍሪካ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ “ጀግና” የሚለውን ክብር መጎናጸፍ ችሏል፡፡ ሆኖም ይህ የአመራር ዘይቤው ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላት ፈጥሮበት ነበር፡፡

ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ለበርካታ ዓመታት የቡርኪናፋሶን የተፈጥሮ ሃብት እና የሕዝቡን ጉልበት ለመበዝበዝ ሕዝቡን በመደብ ልዩነት ከፋፍላ እርስ በእርስ በማጋጨት ስታሴር ቆይታለች፡፡ በኋላም ይህን የሴራ አደረጃጀት በመጠቀም በሚዋደዱት የትግል ጓዶች፣ በሳንካራ እና ኮምፓዎሬ መካከል ጥል በመፍጠር እርስ በርስ የሚገዳደሉበትን ዘዴ አቀነባበረች፡፡ ሳንካራ ሀገሩ ቦርኪናፋሶ ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነቷን እንድታቋርጥ ሲያደርግ ፈረንሳይ በምስጢር ኮምፓዎሬ የሳንካራን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲቃወም ሴራ ታደርግ ነበር፡፡

ሴራው ሊፈጸም ቀናት ሲቀሩት የደህንነት ሚኒስትሩ እና ታማኝ የስራ ባልደረቦቹ ኮምፓዎሬ ሊገድለው እየዶለቱ መሆኑን ሲያሳውቀው እርምጃ እንዲወሰድ ሲያስታውቁት ሳንካራ ግን ሃሳቡን አልወደደላቸውም፡፡ “ራሱ ኮምፓዎሬ ይክዳኝ እንጅ እኔ ግን በፍጹም አልክደውም፡፡ ጓደኛ አይካድም!” በማለት ተቃወማቸው፡፡

ሳንካራ ባሰበው መጠን ነገሮች ሳይሆኑ ቀርተው የተፈራው ነገር ሆነ፣ ከምሽቱ 4፡30 ላይ ሳንካራ ከ13 ሚኒስትሮቹ ጋር በቤተ መንግሥቱ  አዳራሽ ውስጥ  ነበር። በወቅቱ የሀገሪቱ የልማት እና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎች ዙሪያ እየተወያየ ነበር፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 1987 ዓ.ም። ምሽቱ ድንገት በተኩስ እሩምታ ተናጠ፤  ዓላማው ራሱን ሰውቶ ባልደረቦቹን ማትረፍ ነበር፡፡ ሆኖም ቶማስ ሳንካራ ከአዳራሹ መውጪያ በር ላይ እንደ ደረሰ ሁለት እጁን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ እጅ መስጠቱን ከመናገሩ ቅፅበት የጥይት ዶፍ በደረቱ ላይ ያዘነበበት፤  ታላቁ ሰው ወደቀ፡፡

የሀገሪቱን መሪ መግደላቸውን እንዳረጋገጡ ወታደራዊ ልብስ ያጠለቁ እና ክላሽንኮቭ የታጠቁ ታጣቂዎች ወደ አዳራሹ ዘለው በመግባት እሩምታ ተኮሱ፡፡ ያ ሁሉ የጥይት መአት አዳራሹ ውስጥ በነበሩት 13ቱ ሚኒስትሮች ላይ አረፈ፣ አዳራሹ በደም ጎርፍ ተሞላ፡፡ ያ ታላቅ የአፍሪካ ጀግና ከሚኒስትሮቹ ጋር ወደቀ። ሁሉም ነገር በቅጽበት ፀጥ ረጭ አለ። አስደንጋጩ የተረገመ ምሽት የቦርኪናቤዎቹን ብቻ አይደለም የአፍሪካን የተስፋ ጭላንጭል አጠፋው።

ገዳዮቹ አላማቸውን ካሳኩ በኋላ የቶማስ ሳንካራን እና የሌሎች ጓዶቹን አስክሬኖች ምልክት እንዳይገኝ አድርገው በዚያው ሌሊት በምስጢር ወስደው በአንድ ጉድጓድ ቀበሯቸው፡፡ በክስተቱ የተደናገጡት የሳንካራ ባለቤት ማርያም ሳንካራ እና ሁለቱ ልጆቻቸው ሀገር ለቀው ወደ ፈረንሳይ ተሰደዱ፡፡

የቦርኪናቤው ሻምበል፣ ማርክሲስቱ አብዮተኛ፣ የፓን አፍሪካ አቀንቃኙ፣ የአብዮቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቶማስ ሳንካራ ይህችን ዓለም ሲሰናበት ቤቱ ውስጥ የቀረው አንድ መኪና፣ አራት ብስክሌት፣ ሶስት ጊታር እና አንድ ፍሪጅ ብቻ ነበር፡፡

በቦርኪናፋሶ ታይቶ የነበረው ስር ነቀል አብዮታዊ ለውጥ ከሳንካራ ግድያ በኋላ ወዲያዉኑ ተገታ፡፡ እንዲያውም የእርሱ ፖሊሲዎች እና የሳንካራ ስም በሚዲያ፣ በታሪክ እና በመጽሐፍ ውስጥ ሆን ተብሎ እንዲዘነጋ ተደርጎ ቆየ፡፡

ነገር ግን እውነት ከ33 ዓመታት በኋላ ቃተተች። የዚህ ጀግና እና ጓዶቹ አስከሬን ከተቀበረበት ቦታ ወጥቶ ሲመረመር በሰባት ጥይት ደረቱ ተበሳስቶ እንደሞተ ከተረጋገጠ በኋላ በስርዓት ተቀብሯል፡፡ በሀገሪቱ ዋና ከተማ በሚገኝ አደባባይ ላይ 16 ጫማ ርዝማኔ ያለው የነሐስ ሐውልት ቆመለት፡፡ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት እና በአብዮታዊው ባንዲራ ያሸበረቀው መካነ መቃብሩ በሀገሪቱ እና ከውጭ በሚመጡ እንግዶች በየጊዜው ይጎበኛል፡፡

በአጠቃላይ ቶማስ ሳንካራ በስሙ የመታሰቢያ ፓርክ፣ የሲኒማ አዳራሽ፣ ቤተ መጻሐፍት፣ ዩኒቨርሲቲ እና መሰል መታሰቢያዎች የተሰየሙለት ሲሆን እነዚህም የሳንካራን ፍልስፍና ለትውልድ እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡ የቶማስ ሳንካራ ግለ ታሪክ የሚያወሱ መጻሕፍትም በበርካታ ቋንቋዎች ተጽፈው ታትመውለታል፡፡ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይኖራል…!

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here