እንዴት እንዘጋጅ?

0
165

ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አሁንም ድረስ የዘለቀው በትጥቅ የታገዘ ግጭት በተማሪዎች ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥረዋል፡፡ ለአብነት በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው ከርመዋል፡፡ ክልል አቀፍ ፈተና ያልሰጡ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት ማሳያ ነው፡፡

ክልሉ ያለው የሰላም እጦት ሳይበግረው አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ሁሉ አሁን ድረስ የተማሪ ምዝገባ እና መማር ማስተማር እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ዓመት ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም ተመዝግበው በትምህርት ላይ የሚገኙት ከሁለት ነጥብ ስድስት አይበልጡም፡፡ በእርግጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ በዓመቱ የዕቅዱን 70 በመቶ ለማሳካት የተለየ የትምህርት የጊዜ ሰሌዳ /ካላንደር/ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቱን የቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ በዓመቱ በመደበኛ እና በግል 750 ሺህ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለመሆኑ ተማሪዎች በችግር ውስጥ ሆነው ያቀዱትን ውጤት ለማስመዝገብ ምን ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ በፋሲሎ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ዐይናዲስ ጋሻው በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡ ተማሪዋ ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርቷን የቀጠለችው ጎን ለጎን የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን እያከናዎነች በምታገኘው ገቢ ነው፡፡

“እስካሁን የመጣሁበትን የድካም መንገድ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ዳር ለማድረስ ጥረት እያደረግሁ ነው፤ ሜዲካል ሳይንስ ማጥናት ደግሞ ትልቁ ህልሜ ነው፤ የተጨናነቀ ጊዜዬ ማስመዝገብ በምፈልገው ውጤት ላይ ጫና እንዳያሳድርብኝ ጥንቃቄ እያደረግሁ ነው” ብላለች፡፡ ዐይናዲስ ሁሌም ጸጥ ያለ ጊዜ እና ቦታን ለጥናት ትመርጣለች፡፡ የጥናት ጊዜዋን የምትጀምረው ሁሌም ከምሽቱ 2፡00 ጀምሮ ሲሆን እስከ ስምንት ሰዓት እንደምትቆይ ተናግራለች፡፡

ከመምህራን የሚሰጡ የመልመጃ ጥያቄዎችን በአብዛኛው ከትምህርት ቤት ከመውጣቷ በፊት የማጠናቀቅ ልምድ ስላላት ወጥ የሆነ የጥናት ጊዜ እንዲኖራት ማድረጉንም ተናግራለች፡፡ የተማረችበትን ደብተር የመያዝ ልምድ ያላት መሆኑን የምትናገረው ዐይናዲስ፣ ይህም ለዝግጅት እንዳትቸገር እንደሚያደርጋት ገልጻለች፡፡ አጋዥ መጻሕፍትንም ትጠቀማለች፡፡

የክልል እና ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች ዓመቱን በድል እንዲያጠናቅቁ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ለማንቃት፣ ዓመቱንም በድል ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ የአጠናን ስልቶች ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ አድርገው የሚሠሩ የበይነ መረብ ሚዲያዎች ጠቁመዋል፡፡ በትምህርት ውጤታማ ሆኖ ለመቀጠል ቀዳሚው መንገድ ተማሪ ዐይናዲስ የምትከተለው ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ዘዴ ነው፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜ አሟጦ ለጥናት ለማዋል ልክ እንደ ዐይናዲስ ሁሉ በመምህራን የሚሰጡ የቤት ሥራዎችን ፈጥኖ መሥራት ይገባል፡፡ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ግን ጊዜን መከፋፈል ይገባል፡፡ ይህም የጊዜ ሰሌዳ ለጥናት፣ ለክለሳ፣ መልመጃዎችን ለመሥራት፣ ቤተሰብን ለማገዝ እና ሌሎችንም ሊያካትት ይገባል፡፡

ትኩረቱን ተማሪዎችን ማብቃት ላይ አድርጎ የሚሠራው ‘ስቱደንት ዶት ኮም’ (www.student.com) በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ጊዜ የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ጊዜን በአግባቡ ተጠቅሞ ብቁነትን እና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የጥናት ክፍለ ጊዜ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ የጥናት ዕቅድ ክፍለ ጊዜው በዋናነት የትምህርት አይነቶችን በይዘታቸው ክብደት እና ቅለት ልክ የተመሰረተ ሰዓት መመደብ ለውጤት ያበቃል፡፡ በቀኑ የተማሩትን ለመከለስ የሚሆን ጊዜ መመደብም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ተማሪዎችም ሆኑ በሌሎች የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሰዎች የፈለጉበት ቦታ ለመድረስ በመኝታ ሰዓት በቂ እንቅልፍ ሊያገኙ ይገባቸዋል፡፡ አንድ ሰው በአማካኝ በቀን እስከ ስምንት ሰዓት መተኛት እንዳለበት መረጃው ጠቁሟል፡፡

በቂ እንቅልፍ አለማግኘት የተማሪዎች ማስታወስ ችሎታ እንዲቀንስ እና ውሏቸውም የተዛባ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህም አዘውትረው ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እና ትምህርታቸውንም በንቃት እንዳይከታተሉ በማድረግ ብቁነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡   ተማሪዎች የትምህርት አቀባበላቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ የዓመቱን ትምህርትም በድል ለማጠናቀቅ ለበቂ እንቅልፍ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ መረጃው አስታውቋል፡፡

ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብን የመዳረሻ ግባቸው ዋና መንገድ አድርገው ሲያስቀምጡ ዋናውን የጥናታቸውን ጊዜ በአነጋግ ሰዓት ሊያደርጉ እንደሚገባ ድረ ገጹ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ይጠቁማል፡፡ ይህ ሰዓት አዕምሮ እረፍት አድርጎ በአዲስ መንፈስ ሁሉንም ነገር የሚጀምርበት መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ቅኝት ቀዳሚው የጥናት ስልት ሊሆን እንደሚገባ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው ጽሑፍ ይገልጻል፡፡ ይህ የጥናት ስልት አንድን የትምህርት ይዘት ምዕራፍ ለማንበብ ከመጀመር በፊት አጠቃላይ ይዘቱን እና  ርእሶቹን መቃኘትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይህም ራስን በራስ ለመጠየቅ የሚገፋፋ እና የማወቅ ጉጉትን በእጅጉ የሚጨምር መሆኑ ተመራጭ እንዳደረገው መረጃው አመላክቷል፡፡

በጥናት ወቅት የይዘቶቹን አንኳር ጭብጦች በማስታወሻ ደብተር ማስፈር፣ አዳዲስ ቃላቶችን መዞ ማውጣት እና ትርጉማቸውን ማፈላለግ  ይዘቶችን በቀላሉ ለማስታወስ  እና አይረሴነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡  ክለሳ ማድረግም ሌላው በትኩረት ሊተገበር የሚገባ የአጠናን ስልት ነው፡፡ የማስታወስ ችሎታን ለማዳበር እና በራስ የመተማመን ክህሎትን ለማሳደግ ራስን በራስ መፈተን እንዲሁም  ከሌሎች ተማሪዎች ጋር የመጠያየቅ ልምድን ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡

ፀጥ ያለ ቦታን መምረጥ፣ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ነጻ መሆን፣ ጥናትን ይዘቱ ከባድ ነው ከሚባለው የትምህርት አይነት መጀመር፣ ያለፉ ፈተናዎችን እና መልመጃዎችን መሥራት ዓመቱን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ አጋዥ ጉዳዮች ሆነው ተመላክተዋል፡፡

ለረፍት የሚሆን በቂ ጊዜ መመደብም ተገቢ ነው፡፡ ይህም አዕምሮን ዘና በማድረግ የተሻለ የጥናት አቀባበል እንዲኖር ያግዛል፡፡ በዚህ ጊዜ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ የተለያዩ አካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን መሥራት፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ አጫጭር ፊልሞችን እና ድራማዎችን ማየትም ይመከራል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here