ዓለም በፈረንጆቹ 2024 ምን ገጠማት?

0
132

በቅርቡ የሸኘነው የፈረንጆቹ 2024 አዳዲስ ግጭቶች የተፈጠሩበት፣ ነባር ቀውሶች ያገረሹበት እና በአየር ንብረት ላይ ያተኮሩ አደጋዎች የተበራከቱበት የትርምስ ዓመት ነበር። በዚህም ምክንያት በግጭት እና በስደት ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎች ቁጥር በሰኔ ወር መጨረሻ 2024 እ.አ.አ 123 ሚሊዮን የሚጠጋ ሆኗል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሱዳን፣ በዩክሬን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚሰደዱትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ ይህ ቁጥር የበለጠ ጨምሯል።

በርካታ ክስተቶች የተከናወኑበት የተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2024  የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለሩሲያ እየተዋጉ መሆኑ፣ የእንግሊዝ እና የአሜሪካ ሚሳኤሎች ወደ ዩክሬን ተልከው ወደ ሩሲያ መተኮሳቸው፣ የኢራን ሚሳኤሎች ወደ ሩሲያ መላካቸው ዋና ዋና ክስተቶች ናቸው። እስራኤል ከሃማስ ባሻገር በሊባኖስ ከሂዝቦላህ ጋር፣ ከኢራን ጋር፣ ከየመኑ የሀውቲ ታጣቂ ቡድን ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷ ግጭት የተበራከተበት ዓመት ያደርገዋል።

የ2024 ዐበይት ክስተት ሆኖ የቀጠለው በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የሚደረገው ጦርነት እንዲቆም በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም ፍሬ ያፈሩ አልነበሩም። ጦርነቱ ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ሕይወታቸው ቀጥፏል። 15 ወራትን የተሻገረው ጦርነቱ አብዛኛውን ጋዛ ወደ ፍርስራሽነት ቀይሮታል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በብዙ መልኩ ጋዛ በቀጣናው (መካከለኛው ምሥራቅ) ላገረሹት ሌሎች ግጭቶች ምንጭ ሆናለች፤ ይህም በእስራኤል እና በተለየ መልኩ በሊባኖስ፣ በየመን፣ በኢራን እና በሶሪያ መካከል የተኩስ ልውውጦች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

ኢራን እና እስራኤል በግላጭ ግጭት ውስጥ የገቡት በተጠናቀቀው 2024  ነው። ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የሚገኙ በርካታ አጋር ወይም “ተኪ” ሚሊሻዎችን ገንዘብ፣ መሣሪያ እና ስልጠና በመስጠት ትደግፋለች።  በሌላ በኩል እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከ10 ሺህ እስከ 12 ሺህ የሚገመቱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለሩሲያ መሰለፋቸው  ለዩክሬን አዲስ ፈተና ፈጥሯል። ይህም የተጠናቀቀው 2024 ዐበይት ክስተት ነበር።

እንደ አሲልደ ዳታ (https://acleddata.com) መረጃ የ2024 አደገኛ እና ግጭት ውስጥ የገቡ ሀገሮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ፍልስጤም፣ ማይናማር እና ሶሪያ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በተለይም በጋዛ 87 በመቶ የፍልስጤም ሕዝብ ለግጭት የተጋለጠ መሆኑ ነው መረጃው ያመላከተው። ማይናማር ደግሞ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች የሚፈነጩባት ሀገር ሆናለች።

እንደ መረጃው ከሆነ እ.አ.አ ከሐምሌ 2024 ጀምሮ ከ165 ሺህ 273 በላይ የፖለቲካ ሁከት ክስተቶች በዓለም ዙሪያ ተመዝግበዋል። ይህም ካለፉት 12 ወራት ማለትም ከሐምሌ 2023 እስከ ሰኔ 2024 ባለው ጊዜ የ15 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህም በዓለም ዙሪያ ከሰባት ሰዎች አንዱ ከሐምሌ 2023 እስከ ሰኔ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ለግጭት ተጋልጧል ተብሎ ይገመታል።

ከሐምሌ 2024 ጀምሮ ያለው ግጭት ከ2023 እና ከዚያ በፊት ካሉት አምስት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የግጭት መጠኑ እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል። በሱዳን ያለው ጦርነት እና ደም መፋሰስ ሊታሰብ የማይችል ስቃይ አስከትሏል። ዜጎችን ለከፋ መከራ ያጋለጠ ስደትንም አስከትሏል።

በሱዳን በሚያዚያ እ.አ.አ 2023 ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። ይህ ከሦስት ሚሊዮን በላይ  ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሰዎችን እና ስምንት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ያጠቃልላል። ግጭቱ በምግብ ዋስትና ላይ አስከፊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአሁኑ ወቅት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጧል። የሱዳን የሕዝብ ቁጥር ከ51 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ልብ ይሏል። በጦርነቱ ምክንያት ብሔራዊ የጤና፣ የትምህርት እና የማሕበራዊ አገልግሎቶች ጫና ውስጥ እየገቡ  ነው።

እ.አ.አ በ2025 የሰላም ጥረቶች ካልተሳኩ እና ጦርነቱ ከተቀጣጠለ ለመሰደድ የሚገደዱ ሰዎች ቁጥር ከ16 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ይገመታል። ይህ ቁጥር በጣም መሠረታዊ የሆኑትን የሰብዓዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተን ነው።

ከጦርነት ወጣ ስንል ፒው ሪሰርች ኦርግ የሚባል በይነ መረብ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ባለፈው የአውሮፓዊያን ዓመት ከ60 በላይ ሀገራት ምርጫ አካሂደዋል። በስልጣን ላይ ላሉት መሪዎች እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስቸጋሪ ዓመትም ነበር። የዋጋ ንረትም ለዓለማችን ሕዝብ ፈተና ሆኖ የቀጠለበት እና ችግሩንም ለአዲሱ 2025 ያሸጋገረበት ሆኖ አልፏል።

በዓመቱ በከፍተኛ ፉክክር ምርጫ ከተካሄደባቸው እና የዓለም ሕዝብ በትኩረት ሲከታተለው የነበረው የሩሲያ እና የአሜሪካ ምርጫዎችን ነው። ሩሲያ በመጋቢት ወር 2024 ባደረገችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቪላድሚር ፑቲንን ለድጋሚ ድል አብቅቷል።

በአሜሪካ በሕዳር ወር የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም በርካታ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነበር። የባይደን ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው እና የተቀናቃኛቸው ትራምፕ የተደረገባቸው ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ እና በምርጫው አሸናፊ መሆን የዓለምን ሕዝብ ትኩረት የሳቡ ክስተቶች ነበሩ።

በዩናይትድ ኪንግደም (እንግሊዝ) የሌበር ፓርቲ ለ14 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየውን የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አገዛዝን በማሸነፍ አብላጫውን የፓርላማ ድምጽ አግኝቷል። ከ60 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈው የቦትስዋና ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሽንፈትም ሌላው አስገራሚ የነበረ ክስተት ነበር።

በብዙ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የዋጋ ንረት በተለይ በ2024 ለተካሄዱ ምርጫዎች በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነበር።

የኢኮኖሚ አለመመጣጠን እነዚህ ሁሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራትን ስሜት ፈጥረው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ኢኮኖሚው የመራጮች ቅሬታ እንዲፈጠር ያደረገ ብቸኛው ነገር አልነበረም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፒው ሪሰርች ባደረገው  ዓለም አቀፍ ዳሰሳዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ አተገባበር ላይ ያለውን ጉድለት አጉልተው የሚያሳዩ ሆነዋል።

እ.አ.አ በ2024 በተደረገው ጥናት ከ31 ሀገራት መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች በሀገራቸው ዴሞክራሲ በሚሠራበት መንገድ ደስተኛ አልነበሩም። በበርካታ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ላለፉት ሦስት ዓመታት እርካታ ማጣት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

መረጃው እንዳመላከተው በብዙ ሀገራት ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የተመረጡ ባለስልጣናት እንደነሱ  ስለማያስቡ ግድ እንደማይሰጣቸው ያምናሉ። ብዙዎች ሃሳባቸውን በሚገባ የሚወክል የፖለቲካ ድርጅት የለም ብለው ነው የሚያምኑት።

የደቡብ ኮሪያ መራጮች ድምጻቸውን ለተቃዋሚው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰጥተዋል። ጋና፣ ፓናማ፣ ፖርቹጋል እና ኡራጓይን ጨምሮ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራት በተደረጉ ምርጫዎች አሸንፈዋል።

በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ የአፓርታይድ ስርዓት ካበቃ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አብላጫውን የብሄራዊ ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት አልቻለም።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ሀገሪቱን ያስተዳደረው የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ  እና ጥምር አጋር የሆነው ኮሜይቶ የፓርላማውን አብላጫ ድምፅ አጥቷል።

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የሱባራቲያ ጃናታ ፓርቲ ለሦስተኛ ጊዜ ተከታታይ ድል ቢቀዳጁም ጥምር መንግሥት ውስጥ እንዲገቡ ተገደዋል። በፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበጋ ወቅት ፈጣን ምርጫን ለማካሄድ የወሰዱት ውሳኔ ውድቅ የሆነበት ዓመትም ነበር።

ከምርጫ መለስ ስንል የተጠናቀቀው የአውሮፓዊያኑ 2024 ዓለማችን በአየር ንብረት  ለውጥ የተናጠችበት ሲሆን በተከሰቱ  አደጋዎችም ሁለት ሺህ  ሰዎች ሕይዎታቸውን አጥተዋል። 229 ቢሊዮን ዶላር ጉዳትም ደርሷል። ዘጋርዲያን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ ይህ ጉዳት እስካሁን ድረስ ዓለማችን ካስተናገደቻቸው ውድ 10 የአየር ንብረት የኢንሹራንስ ክፍያዎች ውስጥ እንዲመደብ አድርጎታል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here