ማዕከሉ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ ነው

0
110

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምግብነት የሚደርሱ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

በምርምር ማዕከሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ተመራማሪ አቶ አስናቀው ታከለ ለኢዜአ  እንዳሉት ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በምርምር የተገኙ አዳዲስ የአቮካዶ፣ የማንጎ እና የፓፓያ ዝርያዎችን እያስተዋወቀ ነው። የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች ለአካባቢው ሥነ ምሕዳር ተስማሚ የሆኑና በሽታን እና ተባይን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፍራፍሬ ዝርያዎቹ በምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑና ከነባሮቹ ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት የሚችሉ እንዲሁም በገበያም ተፈላጊ መሆናቸውን አክለዋል። በተለይ የአቮካዶ እና የማንጎ ዝርያዎቹ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ ናቸው። ነባሮቹ ዝርያዎች ምርት ለመስጠት አስከ ሰባት ዓመት ጊዜ እንደሚወስዱ አቶ አስናቀው አስታውሰዋል።

ዝርያዎቹ በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተመረጡ አርሶ አደሮች ማሳና በሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ለሙከራ በማልማት ውጤታማነታቸው መረጋገጡንም አስታውቀዋል።

ማዕከሉ በጎንደር ከተማ በፍራፍሬ ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች እና ማሕበራት ዝርያዎቹን በማስተዋወቅ የፍራፍሬ ልማት ሥራውን ለማስፋት ስልጠና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ አደባ በበኩላቸው  የማንጎ እና የአቮካዶ ዝርያዎችን በሁለት የፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያዎች በማፍላት ለልማቱ ተሳታፊዎች እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙ የማንጎ እና የአቮካዶ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ለማመቻቸት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

በፍራፍሬ ልማት የተሰማራው የሙሉዓለም አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሕብረት ሥራ ማሕበር ሊቀ መንበር አቶ ዘመነ መወሻ በበኩላቸው ማሕበሩ በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የፍራፍሬ ልማት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ማሕበሩ ባሉት ዐሥር አባላት ማንጎ፣ አቮካዶ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማልማት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች መምጣት የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

በኲር የታኅሳስ 28  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here