ቅንጅታዊ አሠራር – ሙስናን ለመከላከል!

0
219

ሙስና በኢትዮጵያ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት እና ሥልጣንን ለግል ጥቅም በማዋል ወገኖቻቸው የዕለት ጉርስ አጥተው እየተቸገሩ በእርዳታ የተገኘን እህል ሳይቀር የሚቀራመቱ ሙሰኞች ተፈጥረዋል። በመንገድ፣ በመሬት እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጸመው ምዝበራም የጎላ እንደሆነ በስፋት ይሰማል።

ከእነዚህ ዘርፎች በተጨማሪም  አገልግሎትን በፍጥነት እና በጥራት ያለመስጠት ልማድ ተንሰራፍቷል። አገልግሎትን በተፋጠነ እና በቀጥታ ለጠያቂዉ መስጠት እና ሕዝብን ማገልገል እየተቻለ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተዉ አገልግሎት ፈላጊዎችን በቀጠሮ በማጉላላት ዜጎች ሳይፈልጉ የእጅ መንሻ እንዲሰጡ  የሚያደርግ  አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ የተነሳ አሁን አሁን ያለ እጅ መንሻ አገልግሎት ማግኘት ተረት እየሆነ መጥቷል።

ለሙስና በዚህ ደረጃ መስፋፋት የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ አንዱ እና ዋናው ደግሞ ሙስናን ለመቆጣጠር እና ለመታገል በሚሠሩ ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራር አለመስፈኑ ነው፡፡ የተቋማት በጋራ አለመሥራት ሙሰኞች ያሠራር ሥርዓቶችን፣ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ አሠራሮችን እና መርሆዎችን በመጣስ እንዲሁም መረጃዎችን በማጥፋት፣ በማበላሸት እና አምባገነናዊ አሠራርን በመከተል የሕዝብን እንዲሁም የሀገርን ሀብት ለግል ጥቅም እንዲያውሉ በር ከፍቶላቸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት የተከሠቱ ጦርነቶች እና ግጭቶችም ለሙስና መስፋፋት ዕድል እንደከፈቱ ይታመናል፡፡ በዚህም በዚያም የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከጀርባቸው ሙስና እንደሚኖር ማሣያዎች ናቸው። በክልላችን የተከሠተውን ወቅታዊ  የፀጥታ ችግር እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ  የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሐብት ምዝበራ እና የአገልግሎት አሠጣጥ ችግሮች ተከስተዋል።

“ጥረህ ግረህ  ብላ”፣ “ያልሠራ አይብላ “ የሚባሉትን ብሂሎች ወደ ጎን በመተው እና በተቃራኒው ያለውን  “ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን አፍራሽ ብሂል  እንደ ጥሩ ብሂል በመያዝ ከሕዝብ እና ከመንግሥት የተሠጣቸውን ኃላፊነት እና እምነት ወደ ጎን በመተው ከሕዝብ የሚሰበሰበውን እና ለተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውለውን ውስን ሐብት ለግላቸው ብሎም ለቤተሰቦቻቸው የሚያውሉ ወገኖችም ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ሂዷል።

የሙስና ውጤት ሕዝብን በማጉላላት፣ ሀብት እና ንብረትን በመዝረፍ ብቻ ሳይገታ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን  ያስከትላል። የተረጋጋ ማሕበረሰብ እና የፖለቲካ አስተዳደር እንዳይኖር በማድረግ የሚያደርሰው ጉዳትም ከፍተኛ ነው።

ከዚህ እውነታ በመነሳት ሙስናን ለመከላከል ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ከሰሞኑ ተቀናጅተው ለመሥራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት  አድርገዋል። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መልካም ጅምር ነው፡፡

ሙስናን ለመከላከል መሠራት ካለባቸው ተግባራት መካከል በቅድሚያ በማሕበረሰቡ ዘንድ እየተስፋፋ የመጣውን የሰብዕና መጓደል በማረም፣ ዘረፋ እና ቅሚያን የሚያበረታቱ አመለካከቶችን በማውገዝ በየደረጃው ያሉ መሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች እና ሁላችንም ራሣችንን ከድርጊቱ ነፃ በማድረግ ሙስናን በጋራ የመከላከል ሥራ መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበን  ለተግባራዊነቱ መፍጠን አለብን።

መንግሥትም ሙስናን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል እየተሠራ ያለውን ሥራ  በቅርበት በመከታተል እንዲሁም ተገቢ የሆነ እርምት በማድረግ፣ ለሕዝብ ግልፅ መረጃ በመስጠት መሥራቱ ለነገ የማይባል ተግባር መሆን ይገባዋል። ቅንጅታዊ አሠራርን ማስፈንም ሙስናን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ዐውቆ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ያስፈልጋል።

በኲር የታኅሳስ  28  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here