አሚኮ በቴክኖሎጂ ልህቀት

0
155

የሰው ልጅ አዕምሮውን የሚጠቀምበት መንገድ (የእሳቤ ልቀት) ከሌሎች እንስሳት በእጅጉ ይለየዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰውን ልጅ ከመፍጠር በቀር ያላሳካው ፈጠራ የለም። ለአብነትም በምድር ላይ ከሚያደርገው መራቀቅ ባሻገር ጨረቃም ደርሶ ተመልክተናል። ጨረቃ ላይ ለመድረስ ካስቻለው ፈጠራ ባሻገር ደግሞ ጨረቃ ላይ ስለመድረሱ መሬት ላይ ያለው ሰው ለዕይታው እንዲበቃ ያስቻለው ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ በቴክኖሎጂ መራቀቅ የሚያረጋግጥ አብነት ነው። ምክንያቱም ጨረቃ ላይ የተጓዙትን የሰው ልጅ ከቤቱ ቁጭ ብሎ መመልከት ችሏልና ነው። ይህን ያስቻለው የቴክኖሎጂ ውጤትም ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ (OB VAN – Outside Broadcasting) ይሰኛል።

የዛሬ 30 ዓመት በበኩር ጋዜጣ የምሥረታ ጊዜውን አድርጎ በአሁኑ ወቅት የሁሉም የብዙኃን መገናኛ አማራጮች (Mediums) ባለቤት የሆነው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ታዲያ የዚህ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆኗል።

ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ ላይ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ማንኛውንም ክስተት ከቦታው በመሆን በመላው ዓለም ለሚገኙ ታዳሚያን ያስመለክታል፡፡ ክስተቱን ለማድረስ ደግሞ ሁሉንም ነገር በውስጡ የያዘ በመሆኑ የስርጭት መቆራረጥርን ከማስቀረቱም በላይ በተለመደው መንገድ የቀጥታ ስርጭትን ለመከወን የሚወጣን ከፍተኛ ሃብት ያስቀራል። የዚህን ቴክኖሎጂ አበርክቶ በማንሳትም “በመገናኛ ብዙኃን ሥራ ፈር ቀዳጅ” ሲል ነው የገለጸው።

ድረ ገጹ እንዳስነበበው የመጀመሪያው ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ተግባራዊ የተደረገው በእንግሊዙ ግዙፍ የሚዲያ ተቋም በቢቢሲ ነው፤ ዘመኑ ደግሞ እ.አ.አ  በኅዳር ወር 1936 ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ30 ዓመታት በፊት በጣት በሚቆጠሩ ሠራተኞች ሥራውን የጀመረው አሚኮ በአሁኑ ወቅት በኲር እና የብሔረሰብ ጋዜጦችን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች ዝግጅቶቹን እያዳረሰ ይገኛል። በዘመን ሂደትም አብሮ እየዘመነ በአሁኑ ወቅት በብዙኃን መገናኛ ታሪክ ዓለም የደረሰበትን የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ ታጥቋል። ይህንን በማስመልከት ታዲያ ከሰሞኑ የምርቃት ዝግጅት ተካሂዶ ነበር።

በዝግጅቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ “የአሚኮ ተንቀሳቀሳቃሽ ስቱዲዮ በሁሉም አካባቢዎች ጥራት ያለው መረጃ ለማድረስ ዋነኛ አቅም ሆኖ ያገለግላል” ብለዋል።  አሚኮ ከ30 ዓመታት በፊት በበኲር ጋዜጣ ሥራውን እንደጀመረ ያስታወሱት አቶ ሙሉቀን “በየጊዜው ማደግን ባሕሉ በማድረግ አሁን ላይ በ12 ቋንቋዎች የሚሠራ ብዝኀ ልሳን ሆኗል” ብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት  በሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎች ተደራሽ ሲሆን ተጨማሪ ጣቢያዎች እንዲኖሩ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ አሚኮ አብሮነትን እንደ ሀገር እየሰበከ የሚገኝ የሕዝብ ሚዲያ፣ የሕዝብ ድምጽ ነው። የአማራ ሕዝብ  ወረራ ሲፈጸምበት ቀድሞ በመድረስ በየግንባሮቹ ዘገባዎችን እንዳደረሰም አስታውሰዋል።

አሚኮ ሥራ ያስጀመረው ዘመናዊ ተንቀሳቀሳቃሽ ስቱዲዮ በሁሉም የሀገራችን አከባባቢዎች በሁሉም ቋንቋዎች ለሚሰጠው የቀጥታ ስርጭት ሥራ ብዙ ምዕራፎችን የሚያሻግር፣ ከነበርንበትም ብዙ እጥፍ ያደገ ጥራት ያለው መረጃ ለማድረስ ዋነኛ አቅም ሆኖ የሚያገለግል እንደሆነ አቶ ሙሉቀን አብራርተዋል። “ባለቤቱ የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ  ይሁን እንጂ የሚያገለግለው መላ ኢትየጵያዊያንን ነው፡፡ ከአራቱም ማዕዘን መረጃዎችን እንሰበስባለን፣ አደራጅተን ለሕዝባችን እናደርሳለን” ብለዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም አሚኮ በቀጥታ ስርጭት  ሥራ በጉልህ ከሚነሱ እና ብቃቱም ልምዱም ካላቸው ውስን የሚደያ ተቋማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“አሚኮ የበለጠ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ይተጋ ዘንድ፣ ይህ ቴክኖሎጅ ይገባዋል” ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) ናቸው።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በችግሮች ውስጥም ሆኖ በርካታ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጠቃሚ ተግባራትን ሲሠራ የቆዬ መሆኑን በማንሳት አሁን ላይ አድማሱን ለማስፋትም ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ እየታጠቀ ይገኛል ነው ያሉት። አሁን የተመረቀው ቴክኖሎጂም ከዓለም አቀፍ ቴክኖሎጅ ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀጣይም “አሚኮ የሕዝቦችንን አንድነት እና ወንድማማችነት ለማስተሳሰር ለሚያደርገው ጥረት ይህ ቴግኖሎጂ አጋዥ ነው” ብለዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ለሕዝብ ተጠቃሚነት እየሠሩት ለሚገኘው ሥራም ምስጋና አቅርበዋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የርእሰ መስተዳድሩ የሕዝብ ግንኘነት አማካሪ እና የአሚኮ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ ሲሳይ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን “ብዝኃ ልሳን፣ ታማኝ እና ተቀባይነት ያለው፣ ለሀገር ዕድገት እና ሰላም አበክሮ የሚሠራ፣ ለምንገነባው የወል ትርክትም ፊት ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ” ሲሉ ነው የገለጹት።

አሚኮን ከዚህ በላይ ለማጠናከር መንግሥት ድጋፉን እንደሚቀጥል ያነሱት አቶ ይርጋ “በፈተና እና በችግር ውስጥ ሆኖ ለሚሠራው፣ ከገጠመን ችግርም ለማሻገር እየታተረ ለሚገኘው አሚኮ የምንሰስተው ነገር የለም” ብለዋል።

በተመሳሳይ “አሚኮ አዲስና ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ማሰራጫ ስቱዲዮ መጠቀሙ የሚዲያውን የላቀ ከፍታ ለማሳየት ዕድል ይፈጥርለታል” ሲል የአማራ ክልል ምክር ቤት ጠቁሟል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ከፍያለው ማለፉ ሚዲያ በተለይም ለማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች ተደራሽነት ጉልህ አስተዋፅኦ  እንዳለው ገልጸዋል።

“ከዚህ አኳያ  በተለያዩ  አካባቢዎች የሚካሄዱ ሁነቶችን፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዘቶችን በመዘገብ እና በወቅቱ ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ አሚኮ የተጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም” ብለዋል፡፡ አሚኮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ፣ ብዝኀነትን እየተላበሰ፣ የሁሉንም አካባቢ ቋንቋ፣ ባሕል እና እሴቶችን እያጎለበተ ትክክለኛ የሕዝብ ሚዲያ መሆኑን እያረጋገጠ በመጓዝ ላይ የሚገኝ ተቋም ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here