ኢትዮጵያ ከምትከተለው የግብርና መር ፓሊሲ ዋና ዓላማዎች መካከል በምግብ ራስን መቻል፣ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማቅረብ እና የሀገሪቱን የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ይገኙበታል። ይህን ለማሳካትም አዳዲስ አሠራሮችን መከተል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ ከባሕላዊ የአስተራርስ ዘዴ መውጣት፣ የተሻሻለ ምርጥ ዘር መጠቀም እና ሌሎች ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ ምቹ የአየር ንብረት እና ለም መሬት መኖሩ ለሰብል ልማት ተስማሚ አድርጎታል። ለአብነትም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች መካከል የአማራ ክልል በትርፍ አምራችነቱ የሚታወቅ ሲሆን በዋና ዋና ሰብሎች 34 በመቶ ያህሉን ሀገራዊ ምርት ለኢትዮጵያ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በመሆኑም የሰብል ልማት ዘርፉን ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በተደራጀ ሁኔታ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና መጠቀም ይገባል።
የክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ስርጭት እና አጠቃቀም ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም የአርሶ አደሩን ፍላጎት በተሟላ መልኩ ማርካት እንዳልተቻለ የቢሮው መረጃ ያሳያል። ይህን ፍላጎት ለማሟላት በበቂ መሬት ላይ ምርጥ ዘር ማባዛትን (ማምረትን) ይጠይቃል።
የክልሉን የምርጥ ዘር ተደራሽነት ለማሳደግ በተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም በጥራት፣ በመጠን እና በዓይነት በሚፈለገው ልክ ማቅረብ ባለመቻሉ ክልሉ ማግኘት የሚገባውን ምርት ማግኘት እንዳልቻለ ተጠቅሷል።
ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ (የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲሻሻል) ከተመሠረቱ ተቋማት መካከል የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አንዱ ነው። ተቋሙ በዋናነት መነሻ ዘር ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። በ18 ሰብሎች 35 ዝርያዎች ላይ በስፋት እያባዛ ይገኛል። የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ብዜት እና ምርምር ዳይሬክተር ሰማኝ አስረዴ (ዶ/ር) ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት ተቋሙ አራቢ ዘር፣ ቅድመ መሥራች ዘር እና መሥራች ዘር ለዘር አባዢዎች ያቀርባል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ተግባሩም የግብርና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር ለግብርና ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትን እና የውጭ ምንዛሪ አቅምን ማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ፣ ማላመድ፣ መጠበቅ፣ ማስተዋወቅ እና መነሻ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ነው።
ምርጥ ዘር ምርታማነትን በማሳደግ፣ ፈጥኖ በመድረስ እና የተለያዩ በሽታዎችን በመቋቋም ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል። ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት ሌሎች ግብዓቶችን እንዳሉ ሆኖ (የአፈር ማዳበሪያ፣ ቴክኖሎጂ እና አስተራርስ) ምርጥ ዘርን መጠቀም እንደ የብርዕ፣ አገዳ፣ ጥራጥሬ እና የቅባት ሰብሎች እስከ 30 በመቶ እንዲሁም አትክልት እና ፍራፍሬ ደግሞ እስከ 50 በመቶ የምርት ጭማሪ እንደሚያስገኝ አመላክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ባለፈው ዓመት (2016 ዓ.ም) ሦስት ሺህ 900 ኩንታል የሚሆን ምርጥ ዘር ለተጠቃሚው ተሰራጭቷል። በዚህ ዓመት ደግሞ አምስት ሺህ 700 ኩንታል ምርጥ ዘር ለመሰብሰብ በዕቅድ ይዞ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሦስት ሺህ 700 ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰብስቧል።
የምርምር ተቋሙ ድርቅን እና አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ ለአብነትም “ሰከላ” የተባለ አሲዳማ አፈርን የሚቋቋም የስንዴ ዝርያን እንዲሁም በአጭር ጊዜ መድረስ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን እያባዛ ይገኛል። ከዚህ ባሻገር ለበጋ መስኖ ስንዴ የሚሆኑ ቀድመው የሚደርሱ ምርጥ ዘር በማባዛት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ጠቅሰዋል። የመስኖ ስንዴ ምርታማነትን የሚያሳድጉ “ህብስት” እና “ቀቀባ” የሚባሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ቴክኖሎጂን በማመንጨት፣ ዘር በማባዛት እና በማስተዋወቅ ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርስ እየሠራ ይገኛል፡፡ የዝናብ እጥረት ወይም ድርቅ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውን አካባቢዎች በመለየት ችግሮችን ለመቀነስ ድርቅን መቋቋም የሚችል እና ንጥረ ነገሩ የተሻለ የሰብል ዝርያዎችን እንደ ብርቱካናማ የስኳር ድንች፣ ዕንቁ ዳጉሳ፣ መልካም የማሽላ ዝርያ፣ አይዶርቄ ጎመን እና ሌሎችን ዝርያዎችን በማባዛት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የዘር ብዜት ሥራዎች የሚከናወኑት አካባቢዎቹ ምቹ መሆናቸው በተረጋገጠ፣ የአየር ንብረቱ ተጠንቶ፣ የአፈር ለምነቱ ተለይቶ እና የሰብል በሽታ የማይከሰትባቸው ቦታዎች ተመርጠው እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ ያለው የምርምር ማሳ አነስተኛ ነው። አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር የመጠቀም ፍላጎቱ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በቂ የዘር ማባዣ መሬት ባለመኖሩ፣ በክልሉ ያለው ግጭት እና መሰል ችግሮች መነሻ ዘር ለማምረት እንቅፋት ሆነዋል። በዚህ ምክንያትም አሁንም ድረስ አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ምርጥ ዘር ለማቅረብ ውስንነቶች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዘር ብዜት ባለሙያው ጥላዬ ሞገሴ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት ዘር ለማምረት የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የክልሉን የዘር ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም። በክልሉ የምርጥ ዘር ፍላጎት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን በማንሳት ይህን ፍላጎት ለማሳካት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በምርጥ ዘር የሚሸፈነው ማሳ 10 በመቶ ሲሆን አብዛኛው ዘር የሚሸፈነው ደግሞ በኢ – መደበኛ ሥርዓት እንደሆነ አመላክተዋል። ይሁን እንጂ እየተከናወኑ ባሉ የምርጥ ዘር ብዜት ተግባራት አርሶ አደሩን ማርካት እንዳልተቻለ አስገንዝበዋል። በተለይም ባለፈው ዓመት አርሶ አደሩ ይፈልገው የነበረውን “ሊሙ” የተባለ የበቆሎ ምርጥ ዘር ዝርያ በበቂ መጠን አለመቅረቡን ለአብነት አንስተዋል። ይህን ዘር ለማካካስ ታዲያ ሌሎች ዝርያዎችን መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት (2017 ዓ.ም) በዘር ከተሸፈነው 14 ሺህ 26 ሄክታር መሬት (የምርጥ ዘር ማሳ) ላይ 387 ሺህ 509 ኩንታል ንፁህ እና ጤናማ ዘር በወቅቱ እና በጥራት ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዟል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጥር 02 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 89 ሺህ 539 ኩንታል ምርጥ ዘር እንደተሰበሰበ አመላክተዋል። ወቅቱ የዘር እና የሰብል ምርት መሰብሰቢያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ጥራት ያለው እና ደረጃውን የጠበቀ ዘር እንዲያገኝ እና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰብል በሚሰበሰብበት ወቅት ጥራት እንዳይጓደል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ጥላዬ አክለውም በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በዘር አሰባስቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልፀዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ ዘር አባዢ ድርጅቶች ዘር በማምረት ላይ ይገኛሉ። በአጠቃላይ በክልሉ 42 የሚሆኑ የዘር አባዢ ድርጅቶች እንዳሉ ተናግረዋል። ለአብነትም የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ የኢትዮጲያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የውጪ ድርጅቶች፣ ዩኒየኖች እና ማሕበራት ይገኙበታል። እነዚህም ምርጥ ዘርን በጥራት፣ በወቅቱ፣ በዓይነት እና በመጠን ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል። የተባዙ የሰብል ዝርያዎች በወቅቱ እና በአግባቡ እንዲሰበሰቡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም