የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር የመጀመሪያው ዙር ተጠናቋል። ምድብ አንድ በአዲስ አበባ የተከናወነ ሲሆን ምድብ ሁለት ደግሞ በሀዋሳ ስቴዲየም ነበር የተደረገው። በዚህ መድረክ በአጠቃላይ 24 ክለቦች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
ምድብ አንድን ሸገር ከተማ ከተከታዩ ቤንችማጂ ቡና በስድስት ነጥብ ርቆ እየመራ የመጀመሪያውን ዙር ጨርሷል። ሸገር ከተማ መሰብሰብ ከነበረበት 33 ነጥብ 29ኙን አሳክቷል፤ እስካሁን አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈ ብቸኛው ክለብም ነው ። ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች ውስጥ ዘጠኙን አሸንፏል። በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል።
በከፍተኛ ሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር ካላቸው ክለቦች ውስጥ በቀዳሚት ይቀመጣል። ክለቡ ከምድቡ ጠንካራ የኋላ ክፍል ካላቸው ክለቦች መካከልም አንዱ ነው። ከዚህ ምድብ በ23 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የመጀመሪያውን ዙር የጨረሰው ቤንችማጂ ቡና ነው። ስሎዳ ዐድዋ ደግሞ በ18 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው።
አማራ ክልልን ወክለው እየተሳተፉ የሚገኙት ደብረ ብርሃን ከተማ እና እንጅባራ ከተማም በምድብ አንድ ነው ያሉት። ባሳለፍነው ዓመት በሊጉ ተፎካካሪ የነበረው ደብረ ብርሃን ከተማ ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ደካማ አቋም አሳይቷል። በ14 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ነው የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው። ክለቡ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች መካከል አራቱን ብቻ ነው ያሸነፈው። በአምስት ጨዋታዎች ሲሸነፍ በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል።
የኋላ ክፍሉ እና የፊት መስመሩ ጠንካራ አለመሆኑ በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪዎች ይልቅ ለወራጅ ቀጠናው እንዲቀርብ አድርጎታል። አሁን ላይ ከወራጅ ቀጣናው በሁለት ነጥብ ብቻ ይርቃል። ደብረ ብርሃን ከተማ በሊጉ ለመቆየት በሁለተኛው ዙር ጠንካራ ሆኖ መቅረብ ይጠበቅበታል። አሊያ ግን በቀጣይ ዓመት በሊጉ ከማናያቸው ክለቦች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በመጀመሪያው ዙር የነበሩባቸውን ክፍተቶች ማረም ከፊት የሚጠብቀው ትልቁ የቤት ሥራ ነው።
በዚህ ምድብ የሚገኘው ሌላኛው የአማራ ክልል ክለብ እንጅባራ ከተማ ነው። በዚህ ዓመት መጥፎ አጀማመር ያደረገው እንጅባራ ከተማ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 12 ነጥብ በመሰብሰብም ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። እንጅባራ ከተማ ከምድቡ በርካታ ጨዋታዎችን ከተሸነፉ ክለቦች ውስጥ አንዱ ነው። አምስት መርሀ ግብሮችን ሲሸነፍ ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ያሸነፈው። በተመሳሳይ በሦስቱ መርሀ ግብር ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ቡድኑ ከምድቡ አነስተኛ ግቦችን ያስቆጠረ ክለብ ጭምር ነው። የኋላ ክፍሉም በቀላሉ የሚረበሽ፣ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን ከምድቡ ደካማ የተከላካይ ክፍል የያዘ ክለብ አድርጎታል። እንጅባራ ከተማ በሊጉ ለመቆየት በዚህ በጥር የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት በመሳተፍ እና ለሁለተኛው ዙር መዘጋጀት ለነገ የማይተው ተግባሩ ነው። ከምድብ አንድ ከእንጅባራ በተጨማሪ ጋሞ ጨንቻ፣ ዱራሜ ከተማ እና አምቦ ከተማ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
ሀዋሳ ከተማ ላይ እየተከናወነ ያለውን የምድብ ሁለት የወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድርን ደሴ ከተማ ነው እየመራ ያለው። ደሴ ከተማ ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ ጠንካራ ፉክክር እያደረገ ይገኛል። 23 ነጥብ በመሰብሰብ ነው የመጀመሪያውን ዙር በበላይነት ያጠናቀቀው። ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ሰባቱን በማሸነፍ የምድቡ ቀዳሚ ክለብ ነው። ደሴ ከተማ ከምድቡ አነስተኛ ጨዋታዎችን የተሸነፈ ክለብ ጭምር ነው። እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው የተሸነፈው። በተመሳሳይ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 15 ግቦችን በተጋጣሚው መረብ ላይ ሲያሳርፍ አምስት ግቦች ብቻ ደግሞ ተቆጥረውበታል። ይህም ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ አነስተኛ ግቦች የተቆጠሩበት ክለብ አድርጎታል።
በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ በሁለተኛው ዙርም ይሄንን ምርጥ አቋሙን መድገም ይኖርበታል። ከዚሁ ከምድብ ሁለት ነገሌ አርሲ ሀላባ ከተማን በግብ ልዩነት በልጦ በ22 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የካ ክፍለ ከተማ፣ ኦሜድላ፣ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና አክሱም ከተማ ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
የወልቂጤ ከተማው ጌትነት ተስፋዬ እና የቤንችማጂ ቡናው ናትናኤል ዳንኤል በዘጠኝ ግቦች ኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመሩት ነው። የነገሌ አርሲው ገብረ መስቀል ዱባለ በሰባት ግቦች ይከተላቸዋል። የንብ ክለብ አጥቂው አዲሱ አቱላ፣ የሱሉልታው አብዱልመጂድ ሁሴን እና የሸገር ከተማው ያሬድ መኮንን እኩል ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
የዘንድሮው የወንዶች ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር። በሁለቱም ምድብ የሚገኙ ክለቦች ተቀራራቢ ነጥቦችን በመያዝ ነው በደረጃ ሰንጠረዡ የተቀመጡት። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ከሚደረገው ትንቅንቅ ባለፈ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክርም አጓጊ ነበር። ዘንድሮ ወደ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሁለት ክለቦች ብቻ እንደሚያድጉ ቀደም ብሎ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል። ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የሚወርዱ ክለቦችም ከወትሮው በተለየ ቁጥራቸው ከፍ ብሎ አምስት ሆኗል። የትኞቹ ያድጋሉ? የትኞቹስ ይወርዳሉ? በውድድር ዓመቱ መጨረሻ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም