ባህል ሠሪዎቹ እና አጥፊዎቹ

0
175

ንግድ እና ቴክኖሎጂ ዓለምን በአንድ ቦታ ያሉ ይመስል አስተሳስረዋቸዋል። ጆንትራ  የሚባል የጸጉር አቆራረጥ ዓይነት ነበር። በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ የዝነኛው ከያኒ ጆን ትራቮልትን ፀጉር አቆራረጥ ዘዴ ተከትሎ የመጣ ነበር። የብዙነሽ በቀለ፣ ሒሩት በቀለ እና በኋላም ሐመልማል አባተ እና ሌሎች ዝነኞች የጸጉር አሰራር ከዝነኞቹ የውጪ ሀገር ሴቶች የተወሰደ ነበር። ናኒ፣ ኔማር የሚባሉ የጸጉር አቆራረጥ ዓይነቶችም ነበሩ፤ ከዓመታት በፊት። የሰዎች ዝና ሲቀንስ ስታይሎችም/የሚጠቀሟቸው ለየት ያሉ ዘዴዎች/ አብረው ይጠፋሉ። አንዳንዱ ፋሽን ረድኤት የለውም፣ ቶሎ ተሟሙቆ ቶሎ ይጠፋል። የኢትዮጵያዊያን ወንዶች ጸጉር ስታይል/አቆራረጥ ስልት/ ምንድን ነው? የሴቶችስ?

ብቻውን የቆመ ባህል የለም። ቀድሞ የነበረንን አለባበስ፣ አመጋገብ፣ አዘፋፈን፣ አነጋገር እና አኗኗር እየተውን ዘመናዊዉ ዓለም የሚያበጅልንን እየተከተልን ቀጥለናል። በኢትዮጵያ እጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጥ ከዘመናዊነት ጋር የገባ ባህል ሆኗል። የቀድሞው ኢትዮጵያዊ አብዛኛው አንገቱን ጎንበስ አድርጎ ጤና ይስጥልኝ ነበር የሚለው። ከዓመታት በኋላ ደግሞ እጅ ለእጅ መጨባበጥን ተሻግረን ጉንጭ መሳሳምን ባህል አደረግነው። ኮሮና ደግሞ ሌላው የሰላምታ ልምዳችንን የቀየረ አዲስ ገጠመኝ ሆኖ በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ አለፈ።

አዲስ አበባ ውስጥ ሆነን ሩስያ፣ እስራኤል አሜሪካ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ፣  አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ሌሎችም ሀገራት እንዳለን ይሰማናል። ምግብ ቤቶች፣ ሕንጻዎች፣ መጠጥ እና ምግቦች የሰዎች አኗኗር ተቀራራቢነት ባለው የባህል ገመድ ተሳስረው እንመለከታለን። ቢቢሲ አምስት ሀገራት የዓለምን ባህል ሰርተውታል ሲል ሰፊ ንባብ ይዞ ወጥቷል። ከወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይልቅ ባህል ዓለምን በአንድ በማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና መጫዎቱን በመጥቀስ ቢቢሲ ይቀጥላል። ለዚህም ፋሽን፣ አመጋገብ እና መዝናኛዎችን እንደመሳሪያ በመጠቀም ባህል የተራራቁትን ሕዝቦች በአንድ በማሰባሰብ ጉልህ ሚና መጫዎቱን ይጠቅሳል።

የዓለምን ሀገራት መልክ የሰሩለት ያለማችን አምስት ሀገራት ባህል ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ድረስ ተስፋፍቶ ተወዳጅ እና ለማዳ እንዲሆን አድርገዋል። ባህሉን የተቀበሉት አዳዲስ ሀገራት ከሌላ የተዋሱት መሆኑን እስኪረሱት ድረስ ተዋህዷቸዋል።

ሀገራቱ በባህል ጫናቸው ተወዳጅ ሆነው ለመላው ዓለም እንዴት መልክ ሰሩለት ሲባል ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ቋንቋ፣ ትምህርት፣ ስራ፣ ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም፣ መዝናኛ፣ ምግብ፣ ልብስ እና ሌሎች መሰል መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ።

ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ስፔን እና እንግሊዝ በባህል ዘርፍ የዓለምን መልክ በመስራት በኩል ጉልህ ተጽዕኖ ያላቸው ሀገራት ናቸው ይላል  ቢቢሲ። እስኪ እንዴት እንደሰሩን እንመልከታቸው።

ጣሊያን

ጣሊያን ቫለንቲኖ፣ አርማኒ፣ ቬርሳስ፣ ጉቺ እና ሌሎችንም ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸውን ምርቶችን በመስራት በፋሽን ዘርፉ ተወዳጅ ሀገር ናት። ጣሊያኖች ቄንጠኞች (ስታይሊስቶች)፣ ፋሽን ተከታዮች እና ከምግብ እስከ የቤት እና የቢሮ እቃዎች አምራቾች እና አስተዋዋቂዎች በመሆን ቀድመው ይጠቀሳሉ።

ጣሊያኖች በአመጋገብ በኩል የዓለምን ስርዓት መልክ ያስያዙት በፓስታ እና ማካሮኒ ምግቦቻቸው ነው። ጣሊያናዊያን በካፌ እና ምግብ ቤቶች (ሬስቶራንቶች) መዝናናት እና መብላትን ያዘወትራሉ። ቢቢሲ ሮም ውስጥ የሚገኘውን ፖርቶ ሬስቶራንትን በማሳያነት ይጠቅሰዋል። ፓስታ፣ አይብ እና የባህር ውስጥ ምግቦችን አጣፍጦ በመብላት ጣሊያኖች ጎልተው ይጠቀሳሉ። ሀገራቱ ይህንን የምግብ ተጽዕኖ እንደየ ልማድ እና እምነታቸው ወስደውታል። ሀገራችን ኢትዮጵያ  ከጣሊያን ፓስታ እና ማካሮኒ የተባሉ ምግቦችን ወስዳለች። የጣሊያኗ ሚላን ከተማ ግዙፍ የንግድ እና የፋሽን ማዕከል ናት። በርካታ ቁጥር ያላቸው ምግብ ቤቶች በዚህች ከተማ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ከቤት ውጪ መብላት ባልተለመደበት ዘመን ጣይቱ ሆቴል ሲከፈት ምግብ እንዴት ይሸጣል? የሚል ግርታን ፈጥሮ ነበር። በጣሊያን ግን ምግብን በሬስቶራንቶች መብላት ቀደምት ታሪክ አለው።

ዴስል፣ ቬርሳስ፣ ጉቺ፣ አርማኒ፣ ፊላ፣ ካፓ፣ፑማ፣ ዲ ኤንድ ጂ በቲሸርት እና ሌሎች ፋሽን አልባሳት በኩል ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳላት ያሳየናል። በሀገራችን እነዚህን የአልባሳት ምርቶች በሰዎች ትክሻ ላይ ማየት በጣም ቀላል ነው።

ፈረንሳይ

ፈረንሳይ ቅንጡ፣ ዘመናዊ እና አዳዲስ (ፋሽን) ምርቶችን በማምረት ትታወቃለች። የዓለም ሀገራት ፈረንሳዮች የሆኑትን እና ያደረጉትን ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያሉ ብሏል፤ ቢቢሲ። የፓሪስ ከተማ ፕሬዝደንት ሮቢንስ ፊልስ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና እስያ ሀገራት ከመጓዙ በፊት የፈረንሳይ ተጽዕኖ ምን ይመስል እንደነበር አላወቀም ነበር። “የሩቅ ሀገር ሰዎች ሁሉ የፈረንሳይን ምግብ፣ ጥበብ እና ፋሽን መውደዳቸው አስደንቆኛል። በኢራን ሞሌርን በጣም የሚወዱ ሰዎች እንዳሉ ሲነግሩን ደነገጥሁ። ኢራን ውስጥ ሞሌር ይታወቃል “ ሲል ተናግሯል። ሞሌር ፈረንሳያዊ ቴያትር፣ ተውኔት እና ግጥም ጽሐፊ ነው። በሀገራችንም ስራዎቹ መድረክ ላይ ቀርበውለታል። የፈረንሳይ ዋና ከተማን ፓሪስን  ጨምሮ ልዮን እና ቶሉስ ከተሞች ተወዳጁን የፈረንሳይ ምግብ እና ቦርዶክስ ወይን ለማጣጣም አይነተኛ ምርጫዎች ናቸው። ቦርዶክስ ፈረንሳይ ውስጥ በወይን ምርት የታወቀች ከተማ ናት። የቦርዶክስ  ወይንም በዓለም ታዋቂ በመሆኑ ፈረንሳዮች በጣም ኩራት ይሰማቸዋል። ፈረንሳይ በቋንቋዋ በኩልም ዓለምን ለመስራት ትሞክራለች። ለምሳሌ ፈረንሳይ ውስጥ እንግሊዘኛ አይናገሩም፤ ፍላጎትም የላቸውም። ይህን የሚያደርጉትን ቋንቋቸውን ሰው እንዲለምድላቸው ከመፈለግ ነው ሲል ቢቢሲ ጽፏል። የሚፈልጋቸው ሰው ቋንቋቸውን እንዲለምድ ያደርጉታል።

አሜሪካ

የዘመናዊነት ምልክት፣ የመዝናኛ አማራጭ በመሆን የአሜሪካ ተጽዕኖዋ ጎልቶ ይታያል። የአሜሪካ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች፣ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በዓለም ሕዝብ ዘንድ ተፈላጊ ናቸው። አንድን የመዝናኛ ፕሮግራም እንግሊዝ ጀምራው ሊሆን ይችላል፤ አሜሪካ የነካችው ጊዜ ግን ዓለም አቀፍ እውቅና እና ዝናን ያገኛል። አሜሪካ የወደደችው ይቀደሳል፣ የጠላችው ይረክሳል። አሜሪካ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ብዙ ተጉዛለች። የማህበራዊ ሚዲያ መዝናኛዎች ፌስቡክ፣ ኤክስ፣ ጎግል፣ አማዞን፣ ዩቱዩብ መሰል አማራጮች ቢቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በማስተሳሰር ዝነኛ እና ተወዳጅ አድርገዋታል።

አሜሪካ ሆሊውድ የሚባል የፊልም ኢንዱስትሪ አላት። ይህ ኢንዱስትሪ የዓለምን ዕይታ ለመለወጥ በርካታ ፊልሞችን ያመርታል። ፊልሞች በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች ምን መልበስ እንዳለብን፣ እንዴት መናገር እንዳለብን፣  ምን ማየት እንደሚገባን፣ እናም ማን እንደ ሆንን ሊነግሩን ይሞክራሉ።

ስፔን

ስፔኖች በታሪክ ከፍተኛ የግዛት አስፋፊዎች እና ወራሪዎች ሆነው ይወሳሉ። ከደቡብ አሜሪካ እስከ ምሥራቅ ሕንድ ድረስ ጉልህ የግዛት  አሻራ የነበራት ሀገር ናት። ከቻይንኛ ቀጥሎ ስፓኒሽ ቋንቋ በአፍ መፍቻ ቋንቋነት ሲነገር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እና ሙዚቃዎች ስፔንን ስሟ እና ዝናዋ ከፍ እንዲል አድርገዋታል።

ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ የባህል ክብረ በዓላቸው (ፌስቲቫላቸው)፣ እና ሌሎችም ገጽታዎች የብዙዎችን ጎብኚዎች ቀልብ መሳብ እናም የራሳቸው ሀገር እና ማንነት እንደሆነ እንዲሰማቸው አድርጓል። የስፔን ሰዎች ተግባቢዎች ናቸው፤ ሕይወትን ቀለል አድርገው መኖር የሚወዱ እና በጋራ መብላትን ባህላቸው ያደረጉ ናቸው ሲል ቢቢሲ ጽፏል። አመጋገብ የአኗኗር ዘይቤያችን ነው፤ የምንሰራው ለመኖር ነው ብለው ያምናሉ።

እንግሊዝ

በቢቢሲ መረጃ መሰረት እንግሊዝ በጠንካራ የሥራ ባህል፤ ፈጠራ እና ለለውጥ ዝግጁነት ዓለም አቀፍ አሻራ አላት። በዓለም ደረጃ የታወቁ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት አሏት። የስራ ፈጠራ ማእከላትም በብዛት የሚገኙባት ሀገር ናት። የማሽን ኮድ፣ ኮምፒዩተር እና ወርልድ ዋይድ ዌብን (WWW) የፈጠረችውም እንግሊዝ ናት። የእንግሊዝኛ ቋንቋ መስፋፋት መላው ዓለም እንግሊዝ ውስጥ መኖርን እንዲመርጥ እና በቋንቋው እንዲናገር አስችሎታል። ከስምንት ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ያህሉ እንግሊዝ ያበረከተችውን እንግሊዝኛ ቋንቋ ይናገራል። እንግሊዝኛን  የሚናገር እንግሊዝ ውስጥ የተገኘ ማንኛውም ሰው በቅጽበት እንግሊዛዊነት እንዲሰማው  ይሆናል። የንግድ እና ስራ ማእከሏ ለንደን ከተማ የስራ ፈላጊዎች ምርጥ መዳረሻ ናት።

ከቢቢሲ መረጃ ተነስተን ስንመለከተው በአንድ በኩል ዓለም አቀፋዊነት እውቀት እና መረጃ ለብዙኀኑ እንዲዳረስ በማድረግ ለባህል ልውውጥ እንዲኖር ያግዛል። በባህል ቱሪዝም በኩል መልካም የኢኮኖሚ  እድሎችን ይዞም ይመጣል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም አቀፋዊነት መስፋፋቱ ሀገር በቀል ባህሎች እና ነባር ቋንቋዎች እንዲጠፉም የማድረግ እድል አለው። የታዳጊ ሀገራት ባህሎች እና ማንነቶች ተዳክመው በውጪ ጠንካራ ሀገራት የመዋጥ ስጋት አለባቸው። አንደ ሸቀጥ ሁሉ ባህልም በሀብታም ሀገራት መመራቱ አይቀሬ ይሆናል። የአፍሪካን ምርት አውሮፓ መሸጥ ቢፈለግ በጥራት አይወዳደርም እንደሚባለው ሁሉ፤ በባህልም ዘርፍ ኋላ ቀር ተብሎ መውደቅ ሊመጣ ይችላል። በልዩነት ውስጥ የነበረ ውበት ጠፍቶ አንድ ዓይነትነት የዓለም እጣ መሆኑ አይቀርም። ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ሀገራት እንዴት ዓለምን እንደሰሩ አይተናል። በሒደት አንድ መምሰል መሰላቸትን ሊፈጥር ይችል ይሆናል።

ይህ ዓለም አሸናፊዎች የሚኖሩበት እንደመሆኑ ያልጠነከረ ከሕልውና ተገፍቶ ሲወድቅ እያየን ነው። ዓለም አቀፋዊነት በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ነው። ለሚጠቀምበት አልሚ እድል ነው። ለሚተኙ ሰዎች እና ሀገራት ደግሞ አጥፊ ነው።

የባህል ትምህርትን ማስፋፋት፤ ተቋማትን እና ግለሰቦችን በመጠቀም ማስተማር ጃፓን፣ ቻይና እና የአረብ ሀገራት ራሳቸውን ጠብቀው ለመቀጠል የተጠቀሙበት ዘዴ ነው።

ቴክኖሎጂን መጠቀም ሌላው ባህልን ከዓለም አቀፍ ሰለባነት መጠበቂያ ዘዴ ነው። ቨርቹዋል ሪያሊቲ (ምናባዊ እውነታ)ን በመጠቀም ቅርሶችን፣ ታሪኮችን፣ የመስሕብ ስፍራዎችን እና ጥንታዊ ባህሎችን ማሳየት ይቻላል። በዚህም መጠበቅ፣ ማስተዋወቅ እና ማስቀጠል ይቻላል።

የባህል ቅርሶችን ለመጠበቅ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋራ ሊሰሩ የሚችሉባቸውን የፖሊሲ ማእቀፎች ሊያወጡ ይችላሉ። ዩኔስኮ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። በዓለም የሚገኙ ቅርሶችን እና ባህሎችን በመመዝገብ፣ በማጥናት ለመጪው ትውልድ እንዲሸጋገሩ እየሰራ ነው።

ቱሪዝምን ማስፋፋት ብዙ ጎብኚዎች ነባር ባህላችን እንዲጎበኙ እድል ይሰጣል። ጎብኚዎች ነባር  የባህል ክዋኔ፣ ልምምድ፣ ድርጊቶች፣ አኗኗርን መመልከታቸው ሀገር በቀል ባህሎች የሚጠበቁበትን ገቢ በማምጣት በሕልውና እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል።

ከሁሉም በላይ ግን የኢኮኖሚ አቅም መኖር አለመኖር ባህልን ንጉሥ ወይም ሎሌ ያደርገዋል። የምዕራባውያን ባህሎች በየትኛውም ዓለም ንጉሥ ናቸው። የአፍሪካዊያን ምርጥ ባህሎች ግን በሌላው ዓለም እንኳን ሊነግሡ በስም አይጠሩም፤ አይታወቁም። የኢኮኖሚ አቅም የፈጠሩ ሀገራት በሁሉም ዘርፍ ጠንካራ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ አይተናል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቱርክ ፊልሞችን የሚያሰራጩ በመብዛታቸው፣ የቱርክ ሱፍ፣ የቱርክ ሸሚዝ ፣የቱርክ ሌሎች አልባሳት እና መዋቢያዎች በብዛት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እየተስፋፉ ነው። ኧረ እንዲያውም ሰው ሱፍ ለብሶ ሲያምርበትም “ቱርክ መስለሃል” መባባል ለምዶብናል።

ባህሎችን መርጦ መውሰድ ይቻላል፤ ለመምረጥ ግን ቅድሚያ በኢኮኖሚ መጠንከር ግድ ይላል። የኢትዮጵያ ፊልም ጠንካራ ቢሆን ኖሮ የአሜሪካ፣ ሕንድ እና ቱርክ  ፊልሞች በዚህ ስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ ባልተስፋፉ ነበር።  ቱርክ በፊልሞቿ ቤታችን ውስጥ ገብታለች። አነጋገር፣ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ አስተሳሰብ እና ቋንቋችንን ተጽእኖ ውስጥ አስገብታለች። ያልጠነከረ ሰው የመምረጥ መብቱን ይነጠቃል፤ እየሆነ ያለው ይህ ነው። ጠንካራ ሀገራት ደካማ ሀገራትን ከባህላቸው ነቅለው እንደሚጥሏቸው ማወቅ ግድ ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here