ወርቃማው ቃል!

0
155

ታክሲዋ ከሞላች ቆይታለች:: ቢሆንም ረዳቱ “ቅርብ ወራጆች ካላችሁ ግቡ! ቆጠጢና! መስጊድ! አዲናስ! ሳፋሪ መታጠፊያ!… ቅርብ ወራጅ!..”. እያለ ተሳፋሪውን እያስገባ ባግዳሚው ወንበርም፣ በኩርሲውም፣ በጋቢናው ጀርባም፣ ሦስተኛም … እያስቀመጠ እንደ ሰርዲን እያጨቀው ነው::

እኔ ዓይኖችም ሥራ አልፈቱም፤ ታክሲዋ ውስጥ የተለጣጠፉ ጥቅሶችን ይመለከታሉ:: ጥቅሶቹ ረዳቱ “ትርፍ” ይጭን ዘንድ የሚያበረታቱ፣ ተሳፋሪው ደግሞ “ለምን?” ብሎ እንዳይጠይቅ የሚያስጠነቅቁ፣ ብሎም የሚዘልፉ ናቸው:: “ኑሮ እና ታክሲ ሞልቶ አያውቅም”፤ “ሞላ የሰው ስም ነው ተጠጋጉ”፤ “አምስት ደቂቃ ለማትቀመጠው አምስት ሰዓት አታውራ”፤ “አፍህን ከምትከፍት ሥራና ሱቅ ክፈት…”  ይላሉ፤ ጥቅሶቹ::

ጥቅሶቹ “ከዝንጀሮ ቆንጆ…” ዓይነት ቢሆኑም የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ግን አበሳጩኝ:: ሆኖም እንዳልናገር ፈርቼ ራሴ ከራሴ ጋር፣ ‘ይገርማል! ገንዘብ ከፍሎ መሰደብ! …’ እያልሁ ማውራት ጀመርሁ:: መከባበር በቃ ቀረ ማለት ነው… ሕዝብ እንዲህ ሲዘረጠጥ ዓይቶ የሚገስጽ የሕግ አካል የለም?… ሰሚ እንዲሁም መልስ ሰጪ በሌለበት ከራሴ ጋር እንዲህ ስነጋገር ታክሲዋ ጉዞ ጀመረች::

ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም የቀደመች ይመስል ስትከንፍ ከጋቤናው ጀርባ የተቀመጠች አንዲት ልጅ እግር ተሳፋሪ “ወራጅ!” አለች:: የመጀመሪያዋ ቅርብ ወራጅ መሆኗ ነው:: ረዳቱ ደስ እያለው ወደ ሾፌሩ ዞሮ “ወራጅ!” ሲል ታክሲዋ ቆመች:: በወረደችው ልጅ እግር ተሳፋሪ ምትክ በዕድሜ የገፉ አባት ገቡና ልጅቷ በነበረችበት ቦታ እጥፍጥፍ ብለው ተቀመጡ::

የሰውየውን በዕድሜ መግፋት እንዲሁም እጥፍጥፍ ብሎ መቀመጥ የተመለከተ ወጣት ከተቀመጠበት እየተነሳ “አባባ ይምጡ! እዚህ ይቀመጡ! እኔ ከእሱ ልቀመጥ!” አለ:: አረጋዊው ተሳፋሪ ተነስተው ከልጁ ቦታ ተቀመጡ:: ወጣቱ እጥፍጥፍ ብሎ ተቀመጠ:: በዚህ ቅጽበት ወንበር ከተለቀቀላቸው ተሳፋሪ አንድ ወርቃማ ቃል ጠብቄ ነበር፤ “አመሰግናለሁ!” የሚል ቃል:: ሆኖም እንኳን ሊያመሰግኑት ቀና ብለው ሳያዩት ተደላድለው ተቀምጠው ጉዟቸውን ቀጠሉ::

የወጣቱን ትህትና እንዲሁም ያረጋዊውን ተሳፋሪ የምስጋና ንፍገት ሳስተውል ልጁን ምን እንደተሰማው ባላውቅም የእሱን ንዴት ተናደድሁለት፤ የእሱን ጸጸትም ተጸጸትሁለት፤ ‘ባልተነሳላቸው ኖሮ…’ ስል የማይረባ ሀሳብ አሰብሁ፤ ለመመስገን ሲል የተነሳላቸው ይመስል::

ይህንን እያሰብሁ እያለ ረዳቱ ወደ ሾፌሩ እየተመለከተ “ይቺን መቶ ብር ሀምሳ ሀምሳ አድርግልኝማ!” ሲል ጠየቀው:: ሾፌሩ ግን “የለኝም!” አለው:: መቶ ብር የሰጠው ተሳፋሪ መውረጃው ደርሶ ኖሮ ረዳቱን “መልስ ስጠኝ እንጂ!” እያለ አጣደፈው:: ረዳቱ “መልስ አጥቼ እኮ ነው…”፤ በመጨነቅ ስሜት መለሰለት:: ይሄኔ ‘ሰው እንዲህ ሲቸገር እንዴት ገና ለገና ዝርዝሩ ያስፈልገኛል ብየ ዝም እላለሁ’ ስል አሰብሁና የሚፈልገውን ዝርዝር ሰጠሁት፤ መቶ ብሩን ሰጠኝ፤ ተሳፋሪውም መልሱን ተቀብሎ ወረደ::

ረዳቱ መቶ ብሩን ሲሰጠኝ ዝርዝር አጥቶ ሲቸገር የደረስሁለት ባለውለታው ነኝና ወርቃማው ቃል ካንደበቱ ይወጣ ዘንድ ጠብቄ ነበር፤ ምንም እንኳን ዝርዝሩን የሰጠሁት “አመሰግናለሁ!” እንዲለኝ በመፈለግ ባይሆንም:: መልካም ነገር አድርጌ ላደረግሁት መልካም ነገር “አመሰግናለሁ!” ባለማለቱ ‘ባልሰጠው ኖሮ’ ስል ለሁለተኛ ጊዜ የማይረባ  ሀሳብ አሰብሁ:: በዚህ መሀል ታክሲዋ መንገዷን ጨርሳ ኖሮ ረዳቱ “መጨረሻ!” ሲል ወርጄ ሁለተኛ ታክሲ መያዝ ስለነበረብኝ ወደ ታክሲ መያዣየ ጉዞየን ቀጠልሁ::

ታክሲ መያዣው እንደ ደረስሁ ተሳፈርሁ:: በቦታው ተቆጣጣሪዎች ስለነበሩ ታክሲዋ ያሳፈረችው በወንበር ልክ ነበር:: ሆኖም መንገድ ላይ ያገኘችውን ተሳፋሪ እየለቃቀመች በመሞጀር ጉዞዋን ቀጠለች:: ረዳቱ “ሂሳብ!” እያለ ገንዘብ ሲሰበስብ አንደኛዋ ተሳፋሪ ሁለት መቶ ብር አውጥታ ሰጠችው:: “ዝርዝር ፈልጊ!” አላት:: “የለኝም!” ቆጣ ብላ መለሰችለት:: በዚህ የተጀመረው ምልልስ እየጠነከረ ሄደና ረዳቱ “ዝርዝር የያዘ አለ?!” ሲል ጠየቀ:: እናንተ ቢሰጧችሁም አታመሰግኑም  በሚል ዝም አልሁ::

ረዳቱ ደጋግሞ ዝርዝር ያላችሁ እያለ ሲጠይቅ ግን ራሴን ታዘብሁት፤ ወቀስሁትም፤ ራሴን ታዝቤና ወቅሼም ከራሴ ጋር ‘እነሱ አመሰገኑኝ አላመሰገኑኝ መልካም ነገር ማድረግ ይጠቅመኛል እንጂ አይጎዳኝ’ ስል መከርሁና የፈለገውን ዝርዝር ሰጠሁት:: ዝርዝሩን ተቀብሎ ሁለት መቶ ብሩን ሰጠኝ::

ከብሩ ጋር “አመሰግናለሁ!” የሚለውን ወርቃማ ቃል ብጠብቅም አንደበቱ እንደቀደመው ረዳት ይህን ቃል ማፍለቅ አልፈለገም:: የሁለቱ ረዳቶች ድርጊት ተመሳሳይነት አስገረመኝ:: ሆኖም ለምን ሰጠሁት ብየ አልተጸጸትሁም፤ መልካም ነገር ባደረግሁ ቁጥር ምስጋናን የምጠብቅ ከሆነ አመስጋኝ ካልተገኜ ከመልካም ተግባር እየራቅሁ እንዳልሄድ ከእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ መውጣት እንዳለብኝ ከራሴ ጋር መክሬ ወስኜ ስለነበር በችግሩ ጊዜ ስለደረስሁለት ደስታ እየተሰማኝ ጉዞየን ቀጠልሁ::

ይህን ገጠመኜን ላንድ ጓደኛየ ሳጫውተው አንተ “ዓለመኛ ነህ!” አለኝ:: አባባሉ ግርታን ፈጥሮብኝ “እንዴት?” ስለው “ከእነሱ እንዴት ምስጋና ትጠብቃለህ? ከእነሱ የሚጠበቀው ተሳፋሪን ማንጓጠጥ፣ መዝለፍ እና ማዋረድ እንጂ በማመስገን አይደለም” አለኝ:: ጓደኛየ በታክሲ ረዳቶች ባህርይ እንደተማረረ ተረዳሁ:: ሆኖም ሁሉንም በጅምላ መውቀሱን አልወደድሁለትም:: እናም  “ከረዳቶችም እኮ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው” አሉ በማለት ላሳምነው ሞከርሁ:: እሱም “ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ላደረግነው ነገር ምስጋናን  መጠበቅ ራስን ከጥሩ ነገር ማራቅ ነው ሲል” ሀሳቡን አጠቃለለ:: እዚህ ላይ ጓደኛየ መልካም ነገር ተናግሯል፤ ለምናደርገው መልካም ነገር ሁሉ ምስጋናን መጠበቅ የለብንም::

ጓደኛየ ሰው ለሚደረግለት መልካም ነገር የማመስገን መልካም ልማዱን እየተወ እንደሆነ በመግለጽ “መልካም ነገር ከማድረግ እየራቅህ እንዳትሄድ፣ ለሰዎች መልካም ነገር ባደረግህ ቁጥር  ከሰው ምስጋናን አትጠብቅ” ባለኝ በሦስተኛው ቀን ተመሳሳይ ክስተት አጋጠመኝ:: አንድ ሻይ ክበብ ውስጥ ቡና ጠጥቼ ላስተናጋጇ አንድ መቶ ብር ሰጠኋት::  ያንድ ስኒ ቡና ዋጋ ሀያ ብር ነው:: አስተናጋጇ መልስ ሰጠችኝ::

ሆኖም የመለሰችልኝ ብር ስለበዛብኝ ቆጠርሁት፤ ሰማኒያ ብር መመለስ ሲገባት የመለሰችልኝ ዘጠና ብር ሆኖ አገኜሁት:: በመሆኑም “አሥሩ ብር በስህተት የተጨመረ ነው” ብየ ሰጠኋት:: ብሩን ተቀብላ እንደ ታክሲ ረዳቶቹ “አመሰግናለሁ!” ሳትለኝ  ሄደች:: የሰጠኋት የራሷን ገንዘብ ነው፤ የራሷን ገንዘብ መስጠቴ ደግሞ ግዴታየ ነው:: እናም ለምን ሰጠኋት ብየ አልተጸጸትሁም፤ ለምስጋና ሩቅ በመሆኗ ግን ቅሬታ አልተሰማኝም ብየ ልዋሻችሁ አልፈልግም::

“አመሰግናለሁ!” ከአንደበት ለማውጣት የማይከብድ ቀላል ቃል ነው፤ ለዚያምው አንድ ቃል:: ሆኖም ቃሉ ከፍተኛ ኃይል እንዲሁም ትርጉም አለው፤ ወርቃማ ቃል ያልሁትም ለዚህ ነው:: “አመሰግናለሁ!” ማለት ተመስጋኙንም አመስጋኙንም ከምንገምተው በላይ በእጅጉ የሚጠቅም ወርቃማ ቃል ነው:: ተመስጋኙ ሰው “በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለኝ  ሰው ነኝ” የሚል መልካም ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል፤ አንድ መልካም ነገር አድርጎ ላደረገው መልካም ነገር ምስጋና የሚሰጠው ከሆነ ለመልካም ነገር ሁሌም የሚተጋ ደግ ሰው ይሆናል፤ በተለይም ለሚያመሰግነው ሰው ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግን ልምዱ ያደርጋል::

ተመስጋኙ ሰዎች ለእሱ ስሜት እንዲሁም ክብር እንደሚጠነቀቁ ስለሚረዳም ደኅንነት ይሰማዋል፤ እሱም ላመስጋኞች ስሜት፣ ደኅንነት እንዲሁም ክብር መጠንቀቅን ገንዘቡ ያደርጋል::

ላመስጋኞች ስሜት እንዲሁም ክብር ከተጠነቀቀ ደግሞ ከሰዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነትን ይፈጥራል:: ከሰዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ከፈጠረ ድግሞ በዕለት ከዕለት ሕይዎቱ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ይሆናል::  “አመሰግናለሁ!” ማለት በሰዎች ዘንድ ያለንን ቅቡልነት በመጨመር  ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድንሆንም ይረዳናል:: ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆንን ደግሞ በማኅበራዊ ሕይዎታችን ውስጥ የሰዎችን ጫና ተቋቁመን፣ ልባቸውን አሸንፈን ለምንፈልገው ስኬታችን ከጎናችን ማሰለፍ እንችላለን::

ስለሆነም ለሚደረግልን እያንዳንዱ መልካም ነገር ካንደበታችን “አመሰግናለሁ!” የሚለውን ወርቃማ ቃል ማፍለቅን ልምዳችን ልናደርግ ይገባል::

እርግጥ ነው፤ መልካም ነገር ያደረገ አንዳንድ ሰው “አመሰግናለሁ!” ከሚለው ቃል ይልቅ የተለየ ጥቅምን ይፈልግ ይሆናል:: እንዲህ ያለው ሰው ላደረገላችሁ መልካም ተግባር “አመሰግናለሁ!” ስትሉት “ምስጋና በኪስ አይገባም!” በማለት ወርቃማውን ቃል ዋጋ ሊያሳጣባችሁና ሊያቀልባችሁ   ይሞክር ይሆናል::

አንዳንዱም ስታመሰግኑት እናንተን ደካማ ወይም የበታች፣ ራሱን ጠንካራ ወይም የበላይ አድርጎ ሊቆጥር ይችል ይሆናል:: ሆኖም ማመስገን የትህትና እንጂ የደካማነት ምልክት አይደለም፤ ማመስገን የታላቅነት እንዲሁም የደግነት ምልክት ነው፤   “አመሰግናለሁ!” ማለት ለመናገር የማይከብድ፣ ባንጻሩም ዘርዝረን የማንጨርሰው እልፍ ጠቀሜታ ያለው ወርቃማ ቃል ነው:: ስለዚህ ለሚደረግልን እያንዳንዱ መልካም ነገር ሁሉ “አመሰግናለሁ!” ማለትን መለያችን ልናደርግ ይገባናል::

(ቦረቦር ዘዳር አገር)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here