የነዳጅ ማስተካከያው የተለያዩ ስሜቶች እየተንጸባረቁበት ነው

0
138

መንግሥት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻ በማድረግ የነዳጅ ችርቻሮን ዋጋን በየሦስት ወሩ እንደሚያስተካክል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል:: በዚህ መሠረትም ከተኃሳስ 29/2017  ጀምሮ የሚተገበር የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ይፋ ተደርጓል፤ ይህም የተለያዩ ስሜቶችን እያስተናገደ ይገኛል:: በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው ባጃጅ በማሽከርከር ራሱን የሚያስተዳድረው አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ግለሰብ በአሁኑ  ጊዜ በከተማዋ ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ይልቅ በከተማዋ ነዳጅ እንደልብ ያለማግኘት ችግር ትልቅ ራስ ምታታ እንደፈጠረበት ይናገራል:: እንደ ግለሰቡ ገለጻ  ቤንዚን ለመቅዳት ማደያ ላይ እስከ ሳምንት ድረስ መሰለፍ ግድ ይላል::

በጥቁር ገበያ ግን  ገንዘብ እስካለ ድረስ እንደልብ እንደሚገኝ ነው የተናገረው:: ግለሰቡ እንዳለው  በጥቁር ገበያ ቤንዚን በሊትር እስከ 240 ብር በመግዛት ሥራውን እየሠራ ይገኛል:: ሆኖም የነዳጁን ዋጋ ለማካካስ  ባጃጅ ተጠቃሚዎች ላይ ጫና እየፈጠረ  መሆኑን ነው የጠቆመው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የደምበኞቹ ቁጥር መቀነሱን ነው የገለጸው::

ሌላዋ ስሟን መጥቀስ ያልፈለገች ያነጋገርናት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ  በበኩሏ በከተማዋ ያለውን የነዳጅ ግብይት እና አቅርቦት ሁኔታ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያሳሰበችው:: እንደ ግለሰቧ ገለጻ ቤንዚን በማደያዎች ባለመኖሩ በጥቁር ገበያ በእጥፍ ነው የገዛነው በሚል ምክንያት ነዋሪው ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባሕር ዳር ከተማ በየማደያዎች ረጅም የተሸከርካሪ ሰልፎችን ለቀናት ማየት እና በየመንገዱ በፕላስቲክ (ሃይላንድ) ዕቃዎች ቤንዚን የሚሸጡ ግለሰቦችን ማየት የተለመደ ሆኗል:: ይህም የጥቁር ገበያ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል::

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒቴር   እንዳስታወቀው በሊትር የ10 ብር ጭማሪ ያሳየው ቤንዚን 91 ብር ከ14 ሳንቲም የነበረው ወደ 101 ብር ከ47 ሳንቲም ከፍ ብሏል:: ኬሮሲን እና ነጭ ናፍጣ ደግሞ የስምንት ብር ጭማሪ አሳይተው በሊትር  98 ብር ከ29 ሳንቲም መሸጫ ዋጋ ወጥቶላቸዋል።

ይህን ተከትሎ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በ35 በመቶ ቅናሽ አለው ብለዋል::

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here