የጤናማ እናትነትን ወር በማስመልከት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ የእናቶች እና ሕጻናት እንዲሁም የጨቅላ ሕጻናትን ጤና ማስጠበቅ የመንግሥት ትኩረት ነው ብለዋል::
እናቶች ከወሊድ ጋር ተያይዞ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማትን እና አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን ተደራሽ የማድረግና የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እና ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ጤና ኬላዎችን እና ጤና ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫቸው እንዳሉት ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት በሽታዎች መካከል የማህጸን በር ካንሰር አንዱ ነው። በመሆኑም እንደ ሀገር የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል ከጤናማ እናትነት ወር ጋር በማያያዝ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ።
ዶክተር መቅደስ እንዳሉት የጤናማ እናትነት ወርን ምክንያት በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የወሊድ አገልግሎት ለእናቶች ለመስጠት አቅም በሚፈጥሩ መርኃ ግብሮች ወሩ የሚከበር ይሆናል::
የጤናማ እናትነት በየዓመቱ በጥር ወር ሙሉውን ቀናት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ይከበራል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም