የመጪው ዘመን የአትሌቲክስ ፈርጥ

0
131

ብዙዎች የጥሩነሽ ዲባባ ተተኪ እያሉ ያሞግሷታል፤ የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ ነች፤ የረጅም ርቀት በተለይ የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት ሯጭ ናት፤ የርቀቱ የአለም ከ20 አመት በታች ክብረወሰን ባለቤትም ናት፤ በተደጋጋሚ በጎዳና ላይ ሩጫ ድንቅ አትሌት መሆኗን አስመስክራለች፤ ሀገሯን ወክላ በተለያዩ መድረኮች በመሳተፍ ውጤታማም ሆናለች፤አርአያዬ የምትላት መሰረት ደፋርን ነው- አትሌት መዲና ኢሳ።

መዲና በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ንፋስ መውጫ ከተማ ነው ተወልዳ ያደገችው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም በዚያው በተወለደችበት ከተማ ነው የተከታተለችው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በክምር ድንጋይ ከተማ ተከታትላለች። አትሌቷ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም (ዩንቨርሲቲ) መግባት የሚያስችላትን ውጤት ብታስመዘግብም ትኩረቷን ሩጫ ላይ በማድረግ ሳትገፋበት እንደ ቀረች በአንድ ወቅት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

የአትሌቲክስ ስፖርትን ከመቀላቀሏ በፊት የቮሊቦል ስፖርት ታዘወትር የነበረችው መዲና፤ በሠውነት ማጎልመሻ መምህሯ አማካኝነት ሩጫን በ2008 ዓ.ም በትምህርት ቤት ጀምራለች። ይሁን እንጂ ቤተሰቦቿም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ትኩረቷን ትምህርቷ ላይ እንድታደርግ በማሰብ ለስፖርቱ የምትሰጠውን ጊዜ እንዳልወደዱት ታስታውሳለች። “የሠውነት ማጎልመሻ መምህሬ እና ጓደኞቼ የሩጫውን ዓለም እንድቀላቀል ግፊት ያሳድሩብኝ ነበር፤ እናም ቮሊቦል ስፖርትን ተውኩና የአትሌቲክስ ስፖርትን ተቀላቀላቀልኩ፤ ቤተሰቦቼ እና የአካባቢው ሰዎች ባይወዱልኝም እኔ ግን መሮጤን አላቆምኩም” ስትል አጋጣሚውን ታስታውሳለች።

በ2008 ዓ.ም በከተማው ያለውን የአትሌቲክስ ፕሮጀክት በመቀላቀል ከሌሎች ሰልጣኞች ጋር ስልጠና መውሰድ ጀምራለች። በዚሁ ዓመት ጫጫ ላይ የተከናወነውን የአማራ ክልል አገር አቋራጭ ውድድርም አሸንፋለች።   የመዲናን እምቅ አቅም የተረዱት በወቅቱ የፕሮጀክቱ አሰልጣኝ የነበሩት አቶ ደስታው አረጋ ወደ አውስኮድ የአትሌቲክስ ክለብ ሲያመሩ ይዘዋት ተጉዘዋል።

መዲና ከአውስኮድ ክለብ ጋር ልምምዷን ታከናውን እንጂ የክለቡ አባል ግን አልነበረችም። ከስልጠና በኋላም ራሷ ወደ ተከራየችው ማረፊያ ቤት ነበር የምታመራው። ምንም እንኳ ከክለቡ የላብ መተኪያ፣ ጥቅማጥቅም እና ለሩጫ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ባታገኝም በወቅቱ ከነበሩት የክለቡ አትሌቶች ግን የተሻለች ነበረች።

ተሰጥኦዋን የተመለከተው አውስኮድ የአትሌቲክስ ክለብም በ2009 ዓ.ም በይፋ ክለቡን እንድትቀላቀል አድርጓል። በዚሁ ዓመት በአማራ ክልል በተደረገ አገር አቋራጭ ውድድር ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ይህ ውጤትም በሀገር አቀፉ ደረጃ ጃንሜዳ ለሚደረገው የአገር አቋራጭ ውድድር ክልሉን ወክላ እንድትሳተፍ በር ከፍቶላታል። ይህ ግዙፍ የውድድር መድረክም ለታዳጊዋ ትልቅ ልምድ ሆኗታል። ከዚያ በኋላ በተደረጉ የአገር አቋራጭ ውድድሮችም በተደጋጋሚ ማሸነፍ ችላለች።

ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ2012 ዓ.ም አውስኮድን በመልቀቅ የአማራ ማረሚያ ማረሚያ ቤቶችን ተቀላቅላለች። በወቅቱ በአውስኮድ የሚከፈላቸው የላብ መተኪያ አነስተኛ መሆን እና በቂ የውድድር እድል አለመኖር ክለቡን እንድትለቅ እንዳስገደዳት ተናግራለች። ምንም እንኳ ውድድሩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ባይከናወንም በ2013 ዓ.ም ለአገር አቋራጭ ውድድር ወደ አዲስ አበባ እንዳቀናች በዚያው መኖሪያዋን በዋና ከተማዋ አደረገች።

ብዙም ሳትቆይ ከማኔጄር ቴዎድሮስ ኃይሉ ጋር አብራ በመሥራት ሂንግሎ ላይ በተካሄደው የኦሎምፒክ ማጣሪያ የራሷን ፈጣን ስዓት ጭምር በማሻሻል አሸንፋለች።

በ2014 ዓ.ም ኮሎምቢያ ካሊ ላይ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ሺህ ሜትር ርቀት ለኢትዮጵያ ወርቅ አምጥታለች። በዚህ ውድድር መቶ ሜትር ሲቀር ከአትሌት መልክናት ውዱ ጋር ያደረገችው ፉክክር በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ታሪክ ድንቅ ከሚባሉት ፉክክሮች መካከል ተጠቃሽ ነው።

2015 ዓ.ም የአትሌት መዲና ኢሳ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። በወርሀ ሀምሌ 2015 ዓ.ም ለንደን ላይ በተደረገው አምስት ሺህ ሜትር የዲያመንድ ሊግ ውድድር የራሷን ምርጥ ስዓት በማሻሻል ጭምር አሸንፋለች።  ያስመዘገበችው 14 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ከ54 ማይክሮ ሴኮንድ በዲያመንድ ሊግ ውድድር የቦታው ክብረወሰን ጭምር ነው።

መዲና ለ19 ዓመታት በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በ14 ሴኮንድ ነው ያሻሻለችው። ኢትዮጵያዊቷ ብርቅየ አትሌት ጥሩነሽ 14 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ከ88 ማይክሮ ሴኮንድ መሮጧን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል ።

መዲና በአወስትራሊያ ባትረስት በተደረገው የስድስት ኪሎ ሜትር አገር አቋራጭ ውድድር በግሏ የብር ሜዳሊያ ስታሸንፍ በቡድን ደግሞ የወረቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አምጥታለች፡፡  እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ሚያዚያ ወር አዲዳስ የስፖርት ትጥቅ አምራች  ኩባንያ “አዲ ዜሮ” በሚል ለአራተኛ ጊዜ በጀርመን ባዘጋጀው የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ድንቅ ፉክክር አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያዊቷን ሰንበሬ ተፈሪን ተከትላ በመግባትም የብር ሜዳሊያ አሸንፋለች። የዓለም አትሌቲክስ ምርጥ ተስፈኛ አትሌቶችን ሲመርጥ መዲና በውድድር ዓመቱ ባሳየችው ድንቅ አቋም የመጨረሻ ሦስት እጩዎች ወስጥ አካቷት እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡

ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር በአፍሪካ ጨዋታዎች በተወዳደረችበት የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ የሚታወስ ነው። እንዲሁም አምና ሞሮኮ ላይ በተካሄደው የዲያመንድ ሊግ ውድድር በአምስት ሺህ ሜትር ስታሸንፍ በኳታር ዱሃ በተደረገው ሌላኛው ዙር የዲያመንድ ሊግ መድረክ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክም በአምስት ሺህ ሜትር ርቀት የተሳተፈች ሲሆን ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ነበር የጨረሰችው። ከቀናት በኋላ ደግሞ በፔሩ ሊማ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ርቀቱን በበላይነት በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አምጥታለች። “የመሰረት አሯሯጥ ይማርከኛል” የምትለው አትሌት መዲና ኢሳ እሷም  እንደመሰረት ደፋር እና ጥሩነሽ ዲባባ ሀገሯን በኦሎምፒክ እና ዓለም ሻምፒዮና ለማስጠራት ትልቅ ህልም ይዛ እየሠራች ትገኛለች፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥር 12  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here