“ሰላም ለሁላችሁ፤ አጠር እና ግልጽ አድርጌ እነግራችኋለሁ፤ ከቡጢ ስፖርት መገለሌን አሳውቃችኋለሁ። በቡጢ ቀለበት ውስጥ የነበረኝን እያንዳንዷን ደቂቃ እወዳታለሁ” ይህን መልዕክት በኤክስ ገጹ ያስተላለፈው እንግሊዛዊው ቡጢኛ ታይሰን ፉሪ ነው። በእርግጥ የ36 ዓመቱ ቡጢኛ እንደዚህ ዓይነት መልዕክት ሲያስተላልፍ እና ጓንት መስቀሉን ሲናገር የመጀመሪያው አይደለም። ከሁለት ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ2022 ከስፖርቱ መገለሉን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
ይህን ላስታወሱት ለቡጢው ዓለም ሰዎች እና ለደጋፊዎቹ የታይሰን ፉሪ ሰበር ዜና አላስበረገጋቸውም፤ አላስገረማቸውም። ሀሳቡን ይቀይራል የሚል ተስፋ አላቸውና ነው፡፡ ታይሰን ፉሪ ላለፉት 16 ዓመታት በቡጢ ቀለበት ውስጥ ተጋጣሚዎችን በመዘረር በቡጢኞች ዓለም አንቱታን አትርፏል። ቡጢኛው ፉሪ ደፋር እና የማይገመት ባህሪ እንዳለው በቅርበት የሚያውቁት ይናገራሉ።
ቡጢ ቀለበት ውስጥ የተለየ የፍልሚያ ክህሎት እና ብቃት እንዳለውም ያዩት ሁሉ ይመስክሩለታል። የመልሶ ማጥቃት ታክቲክ ይጠቀማል፤ በሁለቱም እጆቹ ተጋጣሚን መፋለም ይችላል። በዚህ የግጥሚያ ታክቲኩ ለ15 ዓመታት ያህል ሳይሸነፍ በስፖርቱ ውስጥ ቆይቷል።
ታይሰን ፉሪ እ.አ.አ በ1988 በእንግሊዝ ማንቸስተር ከተማ ነው የተወለደው። ከተለመደው ውጪ ከሦስት ወራት ቀደም ብሎ በመወለዱ እና ክብደቱ 450 ግራም ብቻ መመዘኑ ቤተሰቦቹ ያድጋል የሚል እምነት አልነበራቸውም። አባቱ ጆን ፉሪ “ዶክተሮች የመኖር እድሉ አነስተኛ እንደሆነ ነገሩኝ፤ እኔም አምኛለሁ፤ ምክንያቱም በተመሳሳይ መንገድ ሁለት ሴት ልጆቼን አጥቻለሁና” በማለት የታይሰን ፉሪን አስቸጋሪ የልጅነት ህይወት ይናገራል። ታዲያ በህይወት መቆየቱን ያረጋገጡት አባት ጆን ፉሪ በወቅቱ የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮና እና በቡጢ ቀለበት ውስጥ የማይደፈር የነበረውን የማይክ ታይሰንን ስም ለልጃቸው ሰጥተውታል።
ታይሰን ፉሪ ከአየርላንድ ጄፕሲዎች ባለው የዘር ግንድ ምክንያት “ጄፕሲ” የሚል ቅጽል ስምም አለው። የታይሰን ፉሪ ቤተሰቦች ከቡጢ ስፖርት ጋር ያላቸው ቁርኝት የተለየ ነው። በተለይ አያቱ፣ አባቱ እና ወንድሙ ቡጢኞች እንደነበሩ የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል። ፉሪም ከቤተሰቦቹ የወረሰውን ስፖርት ማዘወተር የጀመረው የዐስር ዓመት ልጅ እያለ ነው። ያኔ አባቱ ስፖርቱን ያለማምደው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የወጣትነት እድሜውን በተለያዩ የቡጢ መድረኮች በመወዳደር ራሱን ያጎለበተው ታዳጊው ቡጢኛ በ19 ዓመቱ ሀገሩን እንግሊዝ መወከል ችሏል። እ.አ.አ በ2006 ሞሮኮ አጋዲር ላይ በተከናወነው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ለሀገሩ እንግሊዝ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ፖላንድ በተካሄደው የአውሮፓ ህብረት ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል። እንዲሁም በዚሁ መድርክ ሰርቢያ ላይ የብር ሜዳሊያ ለአያቶቹ ሀገር አየርላንድ አበርክቷል። ድንቅ ብቃቱን የተመለከቱ ፕሮፌሽናል አሰልጣኞችን እና ማኔጀሮችም በታዳጊው ላይ ዐይናቸውን ማሳረፍ የጀመሩት በዚህ ወቅት ነው።
በ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ ሀገሩን እንግሊዝን ወክሎ የመሳተፍ ፍላጎት ቢኖረውም ሳይሳካለት ቀርቷል። ምክንያቱ ደግሞ እያንዳንዱ ሀገር በአንድ ክብደት ምድብ፤ በአንድ ቡጢኛ ብቻ የተገደበ ስለነበር ነው። የአየርላንድ ብሄራዊ ቡድን ለመወከል ያደርገው ጥረትም ፉርሽ ሆኖ ኦሎምፒኩ አልፎታል።
ከአንድ ዓመት በኋላም የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል ግጥሚያውን አደረገ። የመጀመሪያ ግጥሚያው ከሀንጋሪያዊው ቡጢኛ ቤላ ጂዩንግዩሲ ጋር በመፋለም ገና በመጀመሪያው ዙር ተሸነፈ። ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ራሱን እያሻሻለ ከዓለማችን ምርጥ ቡጢኞች መካከል ራሱን ማስቀመጥ ቻለ።
የከባድ ሚዛን ቡጢኛው በአጠቃላይ በፕሮፌሽናል የቡጢ ህይወቱ 37 ግጥሚያዎችን በማድረግ 34ቱን አሸንፏል። ከእነዚህ ውስጥ 24ቱን ያሸነፈው ፎጣ በማስጣል ነው። በሁለቱ ብቻ ሲሸነፍ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።ታይሰን ፉሪ ሁለቱንም ግጥሚያዎች የተሸነፈው በሰባት ወራት ልዩነት በዩክሬናዊው ቡጢኛ ኦሌክሳንደር ዩዜክ ነው። ፉሪ ባለፈው ታህሳስ ወር ነው ሁለተኛ ሽንፈቱን የቀመሰው።
በ2015 እ.አ.አ አበረታች ንጥረ ነገር በመጠቀሙ የብሪቲሽ የቦክስ ቁጥጥር ቦርድ ፈቃዱ ታገደ። በውድድር ዘመኑ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው ውጤትም ተሰረዘ፣ ሽልማቱንም ተነጠቀ። ይህ ወቅት ለታይሰን ፉሪ አስቸጋሪ እንደነበር በግል የታሪክ ማህደሩ ላይ ሰፍሯል። “ዝና እና ገንዘብ ቢኖርህም ደስታ ከሌለህ ለመኖር አትጓጓም። እኔም ለመኖር ፍላጎት አልነበረኝም፤ የአዕምሮ መታወክ ገጥሞኝ ነበር” ሲል የገጠመው ችግር አስከፊ እንደነበር ያብራራል።
በ2016 እ.አ.አ እገዳው አብቅቶ ወደ ቡጢ ቀለበት በመመለስ የመጀመሪያ ግጥሚያውን ከአልባኒያዊው ሰፈር ሰፈሪ ጋር በማድረግ አሸንፏል። ከአራት ዓመታት በኋላ አሜሪካዊውን ቡጢኛ ዲዮንታይ ዋይልደርን ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የዓለም ሻምፒዮና ሆኗል።
በ2011 እ.አ.አ በብሪቲሽ ኮመን ዌልዝ ሻምፒዮና አሸንፏል። ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ የዓለም ከባድ ሚዛን ሻምፒዮና ቀበቶን ታጥቋል። የዓለም ቦክስ ካውንስል ውድድርን (እ.አ.አ በ2020፣2024)፣ የዓለም አቀፍ ቦክስ ፌዴሬሽንን (በ2015 እ.አ.አ)፣ የሪንግ ሜጋዚንን (እ.አ.አ በ2015፣ 2018፣ 2020 እና 2022 ) የአውሮፓ ሻሚዮናን (በ2014 እ.አ.አ) ካሸነፋቸው ውድድሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በ2015 እና 2020 እ.አ.አ የዓመቱ ምርጥ ቡጢኛ ተብሎ ተመርጧል። በሪንግ ሜጋዚን ደግሞ (በ2018 እና 2021 እ.አ.አ) የዓመቱ ምርጥ ተፋላሚ በሚል ተሸልሟል። ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ታይሰን ፉሪ ከኦሌክሳንደር ዩዜክ ጋር በሳውዲ አረቢያ ያደረገው ፍልሚያ የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ግጥሚያ ተብሏል።
ታይሰን ፉሪ ከከፍተኛ ተከፋይ ቡጢኞች መካከል አንዱ ነው። የ36 ዓመቱ እንግሊዛዊ 160 ሚሊዬን ዶላር ገንዘብ በስፖርቱ እንዳካበተ ዴይሊ ሚረር አስነብቧል። ፉሪ ከስፖርት ህይወቱ ከተገለለ በኋላ የቡጢ ስፖርት ግጥሚያ ቀጥታ አስተላላፊ (ኮሜንታተር) ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን ከዘ ሰን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የህክምና ዶክተር መሆን እንደሚፈልግ ተናግሯል።
“ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው ውሳኔ ላይ የደረስኩ። ዶክተር ሆኜ ሰዎችን መርዳት እፈልጋለሁ” ሲል ተድምጧል። በተጨማሪም የስነ ልቦና ትምህርት መማር እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም አዕምሮ እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ እፈልጋለሁም ብሏል። ይህን ሁሉ የሚያደርገው ገንዘብ ለመሥራት ሳይሆን የቆየ ህልሙን ለማሳካት እንደሆነ ቡጢኛው ያስረዳል።
አሁን ላይ በቡጢ ስፖርት ከሚሳተፉ ስፖርተኞች የተሻለ ስኬታማ ነኝ የሚለው ፉሪ አንዳቸውም አጠገቡ እንደማይደርሱ በልበ ሙሉነት ይናገራል።በተከታታይ በኦሌክሳንደር ዩዜክ ከተሸነፈ በኋላ ከሌላኛው እንግሊዛዊ አንቶኒዮ ጆሾዋ ጋር የሚያደርገው እና ሚሊዬን ረብጣ ዶላሮችን የሚያፍስበት ግጥሚያ በጉጉት ሲጠበቅ ነው ድንገት ጓንት መስቀሉን ያወጀው። ታዲያ ሀሳቡን ቀይሮ ድጋሚ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ቡጢ ቀለበት ይመለሳል? ወይስ የእውነት ቀለበት ውስጥ መፋለም በቅቶታል? የብዙዎቹ የስፖርቱ አፍቃሪ እና የደጋፊዎቹ ጥያቄ ነው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም