ወርሀ ጥር በርካቶች ትዳር የሚመሰርቱበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ጥንዶች ቤተሰብ ለማስተዳደር መሰረት የሚጥሉበትን ተቋም የሚገነቡት አንድ ማዕከል ነው። ማእከሉም በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጠር እና በልጅ አማካኝነት የሚያድግ የሰዎች ስብስብ እንደሆነ ከአማራ ሬድዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ የሺአምባው ወርቄ አስረድተዋል።
ቤተሰብ ባል ፣ ሚስት ፣ ልጆች፣ በሥጋ እና በጋብቻ የሚዛመዱ፣ ቤት ውስጥ በሥራ የሚያገለግሉ… በአንድ ቤት ውስጥ ተሰባስበው የሚኖሩበት ተቋም ነው፡፡ እናም ቤተሰብ ማሕበረሰብ ነው ማለት እንደሆነ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
ስለመልካም ትዳር ምስረታ አቶ የሺአምባው ምሳሌ ጠቅሰው እንዳብራሩት ተቋም ጥሩ እና የሚቃኝ መሪ ካለው ወደ ተሻለ ስኬት እንደሚያመራ ሁሉ በትዳር ውስጥም ጤናማ ግንኙነት ሲመሰረት ማህበረሰብን ከማነፅ አንፃር ከፍ ያለ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ትንሽ ተብሎ የሚመሰረተው ቤተሰብ አባት፣ እናት፣ እና ልጅ ብሎ የማህበረሰብ ማሳደጊያ፤ የሰዎች ስብስብ ስለሚሆን ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ከታየ “ትዳር ሕይወት ነው!” ማለት እንደሚቻል ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
ይሁንና በትዳር መካከል አለመስማማት፣ ግጭት እና አለመተማመን ሲኖር ትዳር ሊታመም ይችላል፡፡ ለትዳር መታመም ዋናው ምክንያት የሰዎች ጣልቃ ገብነት መኖር ነው፡፡ ጣልቃ ገብነት በትዳር ጓደኞች መካከከል የባል ፣ የሚስት፣ የቤተሰብ ፣ የጓደኛ… መሃል ገብቶ “መሪ ልሁን” ሲል የሚፈጠር ችግር ነው፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት በሃይማኖትም “እናት እና አባቱን ይተዋል” የሚለው ሃሳብ ከስብዕና ፍላጎት አንፃር ሰው ከሰው የሚለያይ ቢሆንም ትዳር ሲመሰረት ሁለቱ ሰዎች የግል ልዩነታቸውን አንድ አድርገው እና አቻችለው የጋራ ነገሩ ይበልጣል ብለው የሚኖሩበት ተቋም ነው፡፡ ይህንን ተቋም ታዲያ ሌላ ወገን ጣልቃ ገብቶ ሊመራው አይችልም፡፡
አቶ የሺአምባው ጣልቃ ገብነት ምንድን ነው?ለሚለው በምሳሌ ሲያብራሩ መኪናን የሚሾፍረው እንድ ሰው ነው፤ አብሮ በጋራ እንሾፍር ከተባለ መኪናው ገደል እንደሚገባ ሁሉ ትዳርንም “በጋራ ተሰብስበን እንምራ” ማለት የሚደርስበት አደጋ ተመሳሳይ በመሆኑ በጋራ እንምራው የማይባል ተቋም ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሀገር የሚገነባው ተቋም ሊፈርስ ይችላል፡፡
በትዳር ሦስተኛ ወገን ጣልቃ የሚገባው ሰው “አንዱን አካል ተበድለሃል፣ አጥፍተሃል ፣ማድረግ የሚገባህ ይሄ ነው?….” የሚሉ ሃሳቦችን እየሰጠ መራራቅን የሚፈጥር ከሆነ በባለትዳሮች መካከል አለመተማመን ይከሰታል፡፡ ይህን ተከትሎም በሚፈጠር ግጭት የልጆች ስብእና እና ስነ ልቦና ይናጋል፡፡
ሃሳብን በማጋራት በኩል ባል ከሚስቱ፣ ሚስት ከባሏ ብዙ ጊዜ አለመመካከር ፣ አለመወያየት እና ጊዜ አለመሰጣጣት እየጨመረ ሲሄድ “በጋራ ረጅም መንገድ አብሬ እዘልቃለሁ” የሚለው ቁርጠኝነት በተጋቢዎች መካከል ስለሚጠፋ ትዳሩ የመፍረስ አደጋ እንደሚገጥመው አቶ የሺአምባው ይገልፃሉ፤ በእነዚህ ምክንያቶችም ፍች በስፋት ይከሰታል፡፡
ባለሙያው ለአብነት በባሕር ዳር ከተማ በ2015 ዓ.ም 2ሺሕ 117 ግጭቶች ለፍች ሲቀርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ከ16 ሺህ በላይ ፍች መፈፀሙን የወሳኝ ኩነት መረጃን ዋቢ አድርገው አመላክተዋል፡፡ ይሄ ትንሽ ማሳያ የሚያመለክተው በፍርድ ቤት የተጓዙትን ችግሮች ብቻ እንደሆነ የሚያነሱት ባሙያው፤ አስታማሚ የሚፈልጉ በርካታ ትዳሮች በየቦታው ሊኖሩ እንደሚችል መገመት ደግሞ እሙን ነው ይላሉ፡፡
እንደባለሙያው ማብራሪያ በትዳር ውስጥ መቻቻል የሚባለው ነገሮችን መቻል ከሚገባው በላይ መተው እና ይዞ መኖር አይደለም፡፡ “ችሎ ችሎ ባለፈው እንደዚህ አድርጎ/አድርጋ …..” እየተባለ ለሌላ ሦስተኛ ወገን ከተወራ ደግሞ በትዳር መካከል ለሚፈጠር ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታል፡፡
በትዳር ውስጥ መወያየት ፣ጊዜ መሰጣጣት…በደንብ ማጠናከር ይገባል የሚሉት አቶ የሺአምባው፤ ችግርን ሦስተኛ ወገን ሳይገባበት ቤቱ ባለው ነባራዊ ሁኔታ እየተመሩ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩም በምን? እና እንዴት? ተፈጠረ ብሎ ማሰብ ፣የሚመሩትን ትዳር መረዳት፣ እንደ ሀገር እና ማንነት፣ ሃይማኖት… ማሰብ እንደሚገባም አቶ የሺአምባው መክረዋል፡፡ “ካልቻልኩ እተወዋለሁ የምንለው ነገር ስላልሆነ ለትዳሩ በቂ ነኝ ወይ? ብሎ መረዳት እና ማሰብ ይጠይቃል” በማለትም አስገንዝበዋል፡፡
“ትዳር የህይወት ዘመን ፅናት ነው” ተብሎ ከታመነ ለመሸነፍ ዝግጁ የሆነ ስነ ልቦና ሊኖረን አይገባም ያሉት ባለሙያው፤ ሰው የትዳር አጋሩን ማክበር ሲችል ረጅም መንገድ እንደሚጓዝም መክረወዋል፡፡
“በትዳር መካከል ጠብ አይኖርም አይባልም” ያሉት አቶ የሺአምባው፤ ሰው እንኳን ከሌላው ከራሱም ሊጣላ ስለሚችል እንደ አዲስ ነገር ሊወሰድ አይገባም፡፡ ነገር ግን ችግር ተፈጥሮ ለውይይት ሲቀርቡ ራስን እንደተበደለ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ የተቆጣው ባል ከሆነ “እኔ ምን አጉድዬ? ምን ስህተት ሰርቼ ሊሆን ይችላል?” ብላ ሚስት ራሷን መጠየቅ፤ ባሏንም መጠየቅ ይገባል፡፡ ሚስትም ስትቆጣ ባል “ምን በድዬ ይሆን? ምን አጥፍቼ ነው?” ብሎ በመጠየቅ መረዳዳት ያስፈልጋል፡፡ ሰውን በመንቀፍም የሚመጣ ለውጥ የለም እና መነጋገር ሲጀምሩ ከጥሩ ተነስቶ በጥሩ መጨረስ ከተቻለ ችግርን ተቀራርቦ መፍታት ይቻላል፡፡
ሰዎች በተለይ ወደ ትዳር ሲገቡ “ልፋታ እችላለሁ” ብለው ወስነው መጀምር የለባቸውም ያሉት ባለሙያው፤ ትዳር ውስጥ መሥጠት መሠጠት መሆኑን ተገንዝቦ “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ” ሳይሆን መሸነፍ መጀመር ከቁስ የበለጠ ራስን አሳልፎ መስጠት እና መኖር መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸውም መክረወዋል፡፡
በትዳር ውስጥ በፍቅር፣ በገንዘብ፣ በጊዜ ውሳኔዎች ሁሉ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ ማድረግ ካልተቻለ በሚፈጠረው ጭቅጭቅ የራስ ሰላም ከመደፍረስ አልፎ ትዳርን የሚፈሩ እና የስነ ልቦና ጫና እና የደህንነት ሥጋት ያደረባቸው ልጆችን ስለሚፈጥር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
“በትዳር መካከል በጎ ነገር አስባለሁ” ሲባል በመውደቅም ሆነ መነሳት ወቅት መዋደድን ማጠናከር፣ ትዳር ሁል ጊዜ አዲስ ነገር የሚማሩበት ትምህርት ቤት መሆኑን መገንዘብ እና ችግርንም ደስ ብሎ መሸከም ማለት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
አብዛኛው የትዳር ጣልቃገብነት የሚከሰተው ቁሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር፣ በዓለምአቀፋዊነት (የአኗኗር እና የባሕል ቀውስ) ለውጥ ስላለ እና 99 ከመቶ አካባቢ እምነት (ሃይማኖት) ያለው በመሆኑ በትዳር ላይ ያሉ ሰዎች “በሃይማት አስተሳሰብ ውስጥ ነው ያለነው!” ብሎ ራስን መጠየቅ እንደሚገባ እንስተዋል፡፡
“የትዳር ዓላማ መረዳዳት ነው” ሲባል መረዳዳቱ በገንዘብ ሳይሆን በሕይወት መተጋገዝ እና የማንንም እሳቤ ሳይጨምሩ ሃሳብን ተረዳድቶ ማሳለፍ ተገቢ መሆኑን ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም