የአእምሯዊ መብቶች ባለስልጣን ሰነድ እንዳሰፈረው የሰው ልጅ የአእምሮ ሥራ ውጤት በሕግ እውቅና ተሰጥቶት ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ያም የአእምሯዊ ንብረት መብት በመባል ይታወቃል፡፡
አእምሯዊ ንብረት የሰው ልጅ የአእምሮ ውጤት በሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ያለ ሕጋዊ መብት እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 320/1995 በትርጓሜው አመላክቷል፡፡ ሕጋዊ መብቶቹም የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ማረጋገጫ/ፓተንትን/፣ የንግድ ምልክትን፣ የምስክር ወረቀትን፣ የቅጂ መብትን እንደሚጨምር አመላክቷል፡፡ የሁለት ቃላት ጥምረት የሆነው «አእምሯዊ ንብረት» በብራንድ፣ በኢንዱስትሪያዊ ንድፍ፣ በፓተንት(ፈጠራ) አነስተኛ ፈጠራ ማለትም የግልጋሎት ሞዴልን ይጨምራል ፤ በሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ለፈሰሰ መዋዕለ ነዋይ ጥበቃ የሚያደርግ ሕጋዊ መድበል ነው፡፡ ይህ ሕጋዊ መድበል ጥበቃ የሚያደርገው ግዙፍነት ሳይኖራቸው ዋጋ ላላቸው የተለያዩ አእምሯዊ ንብረት እሴቶች ነው፡፡
አእምሯዊ ንብረት ስንል ሃሳቦች፣ ፈጠራዎች፣ ምስሎች፣ ስዕሎች፣ ቅቦች፣ ሃውልቶች፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ በቃላት፣ በእይታ፣ በሙዚቃ፣ በቲያትር የተገለጹ ሥራዎች ወይም በአጭሩ ማንኛውም የአእምሮ ሥራ (በአጠቃላይ ተግባራዊ መረጃ) ውጤቱ የንብረት መብት ያቋቋመ ይሁን አይሁን ግብሩ ከሚገለጽበት ልዩ ቁሳዊ ነገር ውጪ ህልውና ያለውን ነገር የሚገልፅ የሕግ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ አእምሯዊ ንብረት እሴቶች ግዙፍነት ሳይኖራቸው ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም መጠበብ ወይም ፈጠራ ያለሕግ ጥበቃ ፍፁም የሆነ ባለቤትነት አያስገኝም፡፡
የአእምሯዊ ንብረት እሴቶች የሕግ ከለላ ካላገኙ በስተቀር ለፈጠሯቸው ወይም ላመነጯቸው ሰዎች መጠቀሚያ የመሆናቸው እድል ያነሰ ነው፡፡ ምክንያቱም ንብረታዊ እሴቶቹን ለመፍጠር ከሚጠይቀው ወጪ ይልቅ እነሱን ለመቅዳት የሚያስፈልገው ዋጋ እጅግ ያነሰ ፣ በቀላሉ በሌሎች ሊወሰዱ የሚችሉ በመሆናቸው እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ነው፡፡ስለዚህ የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በአእምሯዊ ንብረት እሴቶች ላይ ያሉ ሕጋዊ መብቶች በመሆናቸው ከአእምሯዊ ንብረት እሴቶች የተለዩ ናቸው፡፡
የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ከአእምሯዊ እሴቶች የመጠቀም ሂደትን ለማመቻቸት እና ለማሳካት የተዘረጉ ሕጋዊ ሁኔታዎች ሲሆኑ የንግድ ምልክት፣ የንድፍ፣ የግልጋሎት ሞዴል፣ የፓተንት ወይም የቅጂ እና ተዛማች መብቶች እውቀትን ወደ ንብረት መብት በመለወጥ እና ባለቤቱ ሌሎች ሰዎችን ከመብቶቹ የገበያና የንግድ አገልግሎት በመከልከል የሱ ብቻ የሚያደርግበት መሳሪያዎች ናቸው፡፡
የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ግዙፋዊ ህልውና የሌላቸው፣ በአምስቱ የስሜት ህዋሳት መኖራቸው የማይታወቅ፣ በመጠን፣ በዓይነት እና በአካል የማይያዙ ወይም በያዙት ቦታና አንፃራዊ አዋሳኞች የሚገለጹ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ያላቸው ቁልፍ ቦታ እንዳይታይ ሁነኛ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል፤ አሁንም ነው፡፡ በመሆኑም የንብረት መብት ጥያቄ በሕግ እውቅና እንዲያገኝ እያንዳንዱ የአእምሮ ሥራ ውጤት ተጨባጭነት ባለው መልክ ተለይቶ እንዲወሰን መመዘኛ ማስቀመጥ የሕጉ ኃላፊነት ነው፡፡
ለምሳሌ ሥራዎቹ ሊታዩ፣ ሊደመጡ፣ መኖራቸው ሊታወቅ በሚቻልበት አኳኋን፣ የመወከያ ዘዴ ፣ የምዝገባ ሥርዓቶች እንደ ፓተንት መግለጫ ፣ የመብት ወሰኖች፣ ሥዕሎች ስለፈጠራው በቂ ማብራሪያና መመሪያ ማስቀመጥ የመሳሰሉትን ሊጨምር ይችላል፡፡ የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በምዝገባ ሥርዓት አማካይነት ወይም ሥራዎቹ በመውጣታቸው ብቻ የሕግ ጥበቃ ሊያገኙ የሚችሉ ናቸው፡፡
በሥራው መውጣት ብቻ ስለሚገኙ መብቶች፦
በሥነ ጥበብ እና ሳይንሳዊ መስኮች የሚወጡ ሥራዎች ሥራው በመውጣቱ ብቻ ጥበቃ የሚያገኙ ናቸው፡፡ ይህም እውን የሚሆነው ሁለት መመዘኛዎች ተሟልተው ሲገኙ እንደሆነ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ያመለክተናል፡፡ እነሱም የሥራው ወጥ/ኦሪጂናል/ መሆን እና መቀረፅ ወይም ግዙፍነት ማግኘት ናቸው፡፡ የአዋጁም ኀይለ ቃል የሥራው ዓላማ እና የጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ሥራው ወጥ/ኦሪጂናል/ ከሆነ እና ከተቀረፀ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ሥራውን በማውጣት ብቻ የሥራ አመንጪው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንደሚያገኝ መረጃው አመላክቷል፡፡
በምዝገባ ሥርዓት ስለሚገኙ መብቶች
በምዝገባ ሥርዓት መብት የሚገኝባቸው የአእምሯዊ ንብረት መብቶች በኢንዱስትሪያዊ ንብረት ፈርጅ ስር ያሉትን ይይዛል፡፡ እንዱስትሪያዊ ንብረት ከመነሻው ቴክኖሎጂዎችን ፣ እንዱስትሪዎችን እና የንግድ ሥራዎችን ወደፊት ለማራመድ ተብሎ የተፈጠሩ እንደ ፈጠራዎች/ፓተንቶች/ ኢንዱስትሪያዊ ንድፎች፣ የንግድ ምልክቶች፣ የአገልግሎት ምልክቶች፣ የትእምርተ አካባቢዎችን /Geographical Indications/ ይጨምራል፡፡ የምዝገባ ሥርዐት ለአንዳንዶቹ ቀላል ለአንዳንዶቹ ደግሞ ውስብስብ እና ጥብቅ የቅበላና የምርመራ ሥነ ሥርዓቶች ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡
የማመልከቻ ቅበላና የምርመራ ሥነ ሥዓቶች በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ እንዲሁም በፓተን አዋጅ ተካተው ይገኛሉ፡፡ የንግድ ምልክት ማመልከቻ ቅበላና ምርመራ ሥነ ሥርዓቶች እንደፓተንት የጠበቁና የተወሳሰቡ ባይሆኑም ሙሉ ምርመራ የሚደረግባቸው ሆነው እናገኛቸዋልን፡፡ በዚህም መሠረት ከማመልከቻ ቅበላ (ፎርማሊቲ) እስከ መብቶቹ ተገቢነት (ሥረ ነገር) ፍተሻ የሚደረግባቸው ናቸው፡፡ አዋጅ ቁጥር 123/1987 አጭር ርዕስ እንደሚጠቁመው የኢትዮጵያ የፓተንት ሥርዓት የአስገቢ ፓተንትን ጨምሮ የፈጠራ ፓተንት፣ አነስተኛ ፈጠራ እና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርቲፊኬት መብቶችን ይዞ አጠቃላይና ልዩ የቅበላና ምርመራ ሥነ ሥርዓቶች አሉት፡፡
በጥቅሉ ማንኛውም የፈጠራ ፓተንት መመዘኛ የፓተንት ሥርዐቱ የተመሠረተበትን መርሆና ፖሊሲ እውን ለማድረግ የሚያገለግል በመሆኑ በቂና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው፡፡ ነገር ግን በቴክኖሎጂ መስክ የሚደረግ የፈጠራ እንቅስቃሴ እምብዛም በማይታወቅባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ጥብቅና ውስብስብ የፓተንት ቅበላና ምርመራ ሥርዓቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አያሌ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አነስተኛ ፈጠራዎችን ማበረታታት የፓተንት ሥርዓቱ አይነተኛ ባህሪይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የፓተንት ሥርዓትም በዚሁ መንፈስ የተቀረፀ ስለሆነ የአነስተኛ ፈጠራ ሰርቲፊኬት አማራጭ አለው፡፡ ይህ አማራጭ በአንድ በኩል ለፓተንት ጥበቃ ብቃት የሌላቸው የፈጠራ ሥራዎች ውድቅ ከሚሆኑ ይልቅ ለማበረታታት፤ በሌላ በኩል ለፓተንት ጥበቃ ብቃት የሌላቸው የፈጠራ ሥራዎች ፓተንት እየተሰጣቸው የፓተንት ሥርዓቱን ደረጃ ዝቅ እንዳይል ለመከላከል ነው፡፡ እነዚህን ታሳቢ አድርጎ የሚፈፀመው ምርመራ አነስተኛ ፈጠራው ተግባራዊ (ቴክኒካዊ) ግብር ያለው መሆኑ፣ ለጠቅላላው መልካም ጠባይና ሰላም ተፃራሪ አለመሆኑ፣ የመብት ወሰኑ በግልፅ እና በትክክል የተሞላ መሆኑ፣ መግለጫውና የሥዕል አደራደሩ በአግባቡ መሆኑና ገላጭ መሆኑ ሲረጋገጥ ሰርቲፊኬት ይሰጣል፡፡ የግብይት ወረታቸው ቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭ የሆኑ የኢንዱስትሪያዊ ንድፎችም ቀላል እና ፈጣን የምዝገባ ሥርዓት አላቸው፡፡
በአእምሯዊ ንብረት መብቶች በተለይ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ 410/96 እና የተሻለው አዋጅ 872/07 የቅጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎች ወጥና ግዙፍነት ካገኙ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንደሚሰጣቸው ይገልፃል፡፡ የቅጅ መብትን የሚያስገኙ ሥራዎችን በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ አለማስመዝገብ መብት የማያሳጣ ቢሆንም በሥነ-ጽሁፍ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በሥነ-ጥበብ፣ በኮምፒዩተር ፕሮግራም እና በመሰል ዘርፎች የሚገኙ የፈጠራ ሥራዎችን ማስመዝገብ በርካታ ጠቀሜታዎች አለው፡፡ ከጠቀሜታዎቹም የተወሰኑት የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ሕጋዊ የንብረት ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የመብት ዝውውርን ለመፈጸም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፡፡::
( ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም