ሶሪያ -የስልጣኔዎች እና የጦርነት ምድር

0
154
Syria: The destruction of the Temple of Bel, or Baal, by the Islamic State in Iraq and the Levant, Palmyra, August 2015. (Photo by: Pictures from History/Universal Images Group via Getty Images)

~ ካለፈው የቀጠለ

የአሁኗ ሶሪያ ከጥንታዊ ሶሪያ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ውስጥ በጣም ትንሹን ትሸፍናለች። የታሪክ ተመራማሪዎች ታላቋ ሶሪያ ማለት ይቀናቸዋል። ምክንያቱም የጥንቷ ሶሪያ ዛሬ ሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስ እና እስራኤል ተብሎ እስከተከፋፈለበት 20ኛው ክፍለዘመን ድረስ ያለው እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ጫፍ ድረስ ያለው፤ ሰዎች የሰፈሩበት ምድር ሁሉ ሶሪያ ይባል ነበር። ለዚህም ነው የጥንት ታሪክ አጥኚዎች ታላቋ ሶሪያ የሚሏት። ግሪኮች የሶስት አህጉራት መሸጋገሪያ የመሬት ድልድይ ለማለትም ነበር ሶሪያ የሚለውን ስም እንደ ሰጡት የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ።

ከቦታ አቀማመጧ አንፃር በርካታ ኃያላን የጦርነት መቀጣጠሪያ ያደርጓት ስለነበር የበርካታ የውጊያ ሰልፎች  መኬያሄጃ፣ የጦርነት ምድር ሆና ለዘመናት ከመዝለቋ ባሻገር ራሷን በራሷ ማስተዳደር ብርቅ ሆኖባት ቆይታለች።

ከ2ሺ ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በተለያዩ ጌቶች ተገዝታለች። ይሁን እንጂ የመጨረሻው የኦቶማን ቱርክ የ400 ዓመታት ቅኝ ግዛት ሰላም እና ብልፅግና እንዲናፍቃት አድርጓል። ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉስቁልና ውስጥም የገባችበት ነበር። ሆኖም ከዚህ ነፃ ለመውጣት ያደረገችው ትግል በመጨረሻ ከፈረንሳይ የሞግዚትነት ዘመን ወጥታ ሙሉ ለሙሉ ነፃ የሶሪያን ሪፐብሊክ ለመመስረት መብቃቷን ባለፈው እትም አስነብበን ነበር ያቆምነውን፤ ይህ የመጨረሻ ክፍልም ከነፃነት በኋላ ያለችውን ሶሪያ ያስቃኛል፤ መልካም ንባብ።

 

ከነፃነት ማግስት

ሶሪያ በ1938 ዓ.ም ከፈረንሳይ ነፃ ስትወጣ ሙሉ እውቅና ብታገኝም ከነፃነት ቀጥሎ የነበሩት ዓመታት ሀገሪቱን በከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ አስገብተው ታይተዋል። ተደጋጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እጣ ፋንታዋ ሆነ። ከእስራኤል ጋር የሚደረጉ ግጭቶች መገለጫዎቿ ሆኑ። ቱርክን ጨምሮ በሌሎች ጎረቤት ሀገራት የሚቃጡ የውጭ ጥቃቶች ስለነበሩ እነዚህን የውጭ ጥቃቶች ለመከላከል በሚል ሶሪያ እንደ መፍትሄ በማሰብ በ1953 ዓ.ም ከግብፅ ጋር ህብረት በመፍጠር የተባበረ የአረብ ሪፐብሊክ ለመፍጠር ሞከረች። ጥምረቱ ግን ብዙ አልቆየም እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ ብቻ ቆይቶ ፈረሰ፤ እናም በዚህ ዓመት የሶሪያ አረብ ሪፐብሊክ እንደተመሰረተ ታሪክ ያስረዳል።

1950ዎቹ ለነፃዋ ሶሪያ የደስታ እና የእፎይታ ጊዜ አልነበሩም፣ ይልቁንም ከወትሮው በባሰ ሁኔታ ብዙ አመፆች፣ አብዮቶች፣ መፈንቅለ መንግሥቶች እና አለመረጋጋት ተጠናክረው የቀጠሉበት ነበር። ምእራባውያኑ አዳፍነዋቸው በሄዷቸው ችግሮች የተነሳ በየጊዜው እየታመሰች አንድነቷን የጠበቀች ታላቋን ሶሪያ መገንባት የሚያስችለውን ሀዲድ መያዝ ተስኗት የታየችበት ወሳኝ ወቅት ነበር።

ከ1930ዎቹ ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ክልል በንቃት ይንቀሳቀስ የነበረው የአረብ ሶሺያሊስት ባዝ ፓርቲ በ1955 ዓ.ም የባዝ አብዮት ተብሎ በሚታወቀው መፈንቅለ መንግሥት የሶሪያን የመንግሥት ስልጣን ተቆጣጠሮ ሀገር መምራት ጀመረ። በዚህ ዘመን በ1959 ዓ.ም  በስድስት ቀኑ ጦርነት ወቅት እስራኤል በደቡባዊ ምእራብ ሶሪያ ያለውን የጎላን ተራሮች አካባቢ በመቆጠር ሶሪያን ዛሬ ድረስ ለቀጠለው የድንበር ግጭት ዳረጓታል። እንዲህ ከውስጥም ከውጭም እየታመሰች ወደ 1960ዎቹ ተሻገረች።

 

የሐፌዝ አል አሳድ ዘመን

ከአላዊ አናሳ ማህበረሰብ ውስጥ የተነሳው የሶሪያ መከላከያ ሚንስትር የነበረው ሐፌዝ አል አሳድ በ1962 ዓ.ም የጊዜያዊ መንግሥቱን መሪ ሳላህ ጀዲድን በመገርሠሥ የሶሪያን ዙፋን ተረከቦ በ1992 ዓ.ም እስኪሞት ድረስ ለ30 ዓመታት ሶሪያን በተማከለ መንግሥት ስር ጨቁኖ ገዝቷል።

ሐፌዝ አል አሳድ የተገኘበት አላዊ አናሳ ማህበረሰብ፤ በፈረንሳይ የሞግዚት አስተዳደር ወቅት ትልልቅ የስልጣን ቦታዎችን የማግኘት እድል ይሰጠው ነበር። በኋላም በሀገሪቱ ቁልፍ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን  እንደያዙ ቀጥለው የአሳዶች አገዛዝ መንበርን በብቸኝነት ተቆጣጠሩ።  በፕሬዚደንት ሐፌዝ አል አሳድ ዘመን ሶሪያ ለመረጋጋት  ሞክራ ወታደሯ በእስራኤል የተወሰዱባትን ግዛት ለማስመለስ ተንቀሳቅሶም ነበር።

ሐፌዝ አል አሳድ ከውስጥ የገጠሙትን የሙስሊም ወንድማማቾች አመፅ ወታደሩ በጭካኔያዊ ሀይል   እንዲያኮላሽ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር። የሶሪያ ኃይሎችም ከ25ሺ በላይ ሕዝብ ገደሉ። ይህ እልቂት ለበለጠ የተቃውሞ ምክንያት ሆነ። በሕዝቡ ልብ ውስጥ እየተብላላ የሚፈነዳበትን ጊዜ ይጠብቅ ነበር። በ2003 ዓ.ም የተቃዉሞ ሰልፍም ላይ ደመቅ ብሎ መስተጋባቱንም ያስታውሷል።

በሽር አል አሳድ

በጨቋኝ አገዛዝ ሕዝቡን በመግዛት ሶሪያን ለ30 ዓመታት የመራው ሐፌዝ አል አሳድ በ1992 ዓ.ም ላይ በሞት ይህችን ዓለም ተሰናበተ። በአባቱ እግር የ34 ዓመቱ ጎልማሳ በሽር አል አሳድ ተተክቶ የሶሪያ ፕሬዚደንት ሆነ። በርግጥ ከበሽር በፊት አልጋው ለታላቅ ወንድሙ ባሴል ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም በድንገት በ1986 ዓ.ም በመኪና አደጋ በመሞቱ ጊዜው  የበሽር ሆነ።

የፕሬዝዳንትነት ዘመኑን የጀመረው 600 የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ነበር። ይህ አድራጎቱ በሶሪያውያን ዘንድ አዲሱ መሪ ተስፋ የተጣለበት መስሎ እንዲታይ አደረገው። ተጨማሪ ነፃነቶችን እንደሚያጎናፅፍ እና ከአባቱ የተሻለ እንደሚሆንም ተጠበቀ። ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በኋላ በሽር አል አሳድ የለውጥ አቀንቃኝ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ማስፈራሪያ እና እስራትን ይጠቀም ገባ። በዚህ ሁኔታም ሳለ በ1999 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ በሙሉ ድጋፍ ተመረጠ። ይሁን እና ዳግም መመረጡን በመቃወም  አለመረጋጋት እየጨመረ ሄደ።

የበሽር አስተዳደር በሰብአዊ መብት ጥሰት እየተወነጀለ ይበልጥ በምእራባውያን ጥርስ ውስጥ እየወደቀ መጣ። የተቃውሞው መጠን እየጨመረ ሲሄድ የበሽር አስተዳደር በኃይል ለማክሸፍ በሚያደርጋቸው እርምጃዎች፤ እንዲሁም ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉት እየተከሰሰ እና ለበርካታ ማእቀቦች እየተዳረገ ቀጠለ።

የአረቡ ፀደይ

በቱኒዚያ እና በግብፅ የተነሳው የአረቡ ፀደይ አመፅ ሰደድ ሶርያም ደርሶ ነበር። ነገር ግን በበርካታ የአረቡ ዓለም ሀገራት የተለያዩ ለውጦችን ያስገኘው የአረቡ ፀደይ ሶሪያ ላይ ሲደርስ ሌላ መልክ ያዘ።

የበሽር አል አሳድ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች እና የሶሪያ መንግሥት ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገቡ። የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ። አማፂያኑ አሌፖን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ተቆጣጠሩ። ፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ ዋና ከተማዋን ደማስቆን አስከብሮ ራሱን ያዳነ መሰለ። ሶሪያ ታመሰች፤ አለመረጋጋት ግጭት እና ሽብር የየለት ገጠመኝ ሆነ። የተፈጠረው ስንጥርም አይ ኤስ አይ ኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን እንዲፈጠር በር ከፈተ። ይህም ቡድን የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ጣለው።

አሸባሪዎችን ይደግፋል በሚል አሜሪካ እና አጋሮቿ በሽር አል አሳድ እንዲወገድ አማፂውን በመደገፍ እንዲሁም ሩሲያ በሽር አልአሳድን በመደገፍ ጎራ ለይተው የሶሪያን እጣፋንታ መቀመቅ ውስጥ ከተውት ከራረመ። በሽር አል አሳድ የመውደቅ እድሉ እየጠበበ በመሄዱ የሶሪያውያን አበሳ በዛ። ሶሪያውያን በሚሊዮኖች ተሰደዱ፤ በሚሊዮኖች ሞቱ ቤት ንብረታቸውን አጥተው ፍዳቸውን አይተዋል። በሽር አል አሳድ በተቃዋሚዎቹ ላይ የሚፈፅመው ኢሰብአዊ ድርጊት ገደቡን አልፎ ሕዝቡ በአማፂያኑ በኩል አምርሮ ከታገለ ከብዙ እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በ2017 ዓ.ም ተሳክቶ ለዘመናት ሶሪያን በብቸኝነት የገዛት የአሳዶች ዘመን ያከተመበት የበሽር አል አሳድ መኮብለል በመላው ዓለም ተሰማ። የሶሪያውያን ተስፋ ዳግመኛ ያቆጠቆጠ መሆኑን በሚያሳብቅ መልኩ ምድረ ሶሪያ ፈነደቀች። አዲስ ጅማሮ ሆነ። እኛም ለሶሪያ መልካሙን ሁሉ ተመኘን፤ አበቃን።

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here