የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በጥር ወር የሚከበሩ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የከተማዋ ነዋሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል::
የከተማ አስተዳደሩ ሰሞኑን በጥር ወር በከተማዋ ስለሚከበሩ በዓላት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በከተማዋ ከጥምቀት በዓል በኋላ ጥር 12 ቃና ዘገሊላ ፣ ጥር 13 የአቡነ ዘራብሩክ ፣ጥር 15 የታንኳ ቀዘፋ ውድድር፣ ጥር 18 የሰባሩ ጊዮርጊስ እና ጥር 21 አስትሪዮ ማርያም ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ ይከበራሉ::
እነዚህ በዓላት የከተማው አስተዳደር በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ አስተማማኝ ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር በጸጥታ መዋቅሩ እና በሁሉም ማሕበረሰብ ርብርብ ዘውትር የሚያከናውነው ተግባር መሆኑን አሳውቋል::
በመሆኑም ክብረ በዓላቶቹ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን ተጠብቆ በሰላም እንዲከበሩ እና እንዲጠናቀቁ የእምነቱ ተከታዮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች ፣ሴቶች ፣የንግዱ ማኅበረሰብ፣ በከተማዋ የሚገኙ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪዎች የበኩላቻውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጉን ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያትታል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም