በጎንደር በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማቱ አዲስ የሥራ ባህል መፍጠሩን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ፡፡
ምሽት ጭምር እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማው ማኅበረሰብ እያደረገ ያለው ትብብር እና ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ከንቲባው በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ለቀጣይ የልማት ሥራዎች ከፍተኛ መነሳሳትን ከመፍጠር ባለፈ በርካታ የልማት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚቻል ተሞክሮ፣ ልምድ እና አቅም የተገኘበት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ፒያሳን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ቅርስ በሆነው በአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ዙሪያ የሚከናወነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የከተማው የኮሪደር ልማት ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም በራሱ በጀት በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች የኮሪደር ልማቱን ለማስፋት የሚያስችል አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጥናትና ዲዛይን ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በጎንደር እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማውን ታሪካዊነት እና የቱሪስት መዳረሻነት በሚያጎላ መንገድ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡
ከንቲባዋ በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ በጎንደር ከተማ እየተካሄዱ የሚገኙ የፒያሳ የኮሪደር ልማት እና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ዓለም አቀፍ ቅርስ የጥገና ሥራ ጎብኝተዋል፡፡ በወቅቱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ልምድ እና ተሞክሮ በማስፋት በጎንደር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከጠበቁት በላይ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጎንደር ከተማ ጋር የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት ከተመሰረተ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርብ የኮሪደር ልማቱን ለማሳካት እያደረጉት ላለው ድጋፍ በከተማ መስተዳድሩ እና በሕዝቡ ስም ምሰጋና ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም