ቱሪዝም ከትናንቱ ዛሬ …

0
147

አብኣኛዎቹ ባለሙያዎች እና የዓለም የቱሪዝም ድርጅት መረጃዎች እንደሚያመላክቱት   ቱሪዝም ሰዎች ከቀያቸው /አካባቢያቸው/ ተነስተው ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ወይም ከ24 ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡

ጎብኚዎች ለጉዟቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው፤ ከእነዚህም አንዱ ሰዎች  አዕምሯቸው በሥራ ወይም በሌላ ምክንያት ሲደክም ከመኖሪያ አካባያቸው ርቀው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ አዕምሮን ዘና የሚያደርጉ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ የመስህብ ሃብቶችን  በመጎብኘት መዝናናት ነው::በዚህና በሌሎች ጉብኝትን ዓላማ አድርገው በሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች  በጉብኝት መዳረሻ አካባቢዎች ጎብኝዎች በሚቆዩበት ጊዜ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች ከዘርፉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ተጠቃሚ ሊሆኑ ከሚችሉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች የተለያ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ቪዚት ኢትዮጵያ የተሰኘው ድረ ገጽ  ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ የጉብኝት መዳረሻዎች ቀዳሚውን ሥፍራ እንደምትይዝ  እንዲሁም በቅርስነት ባስመዘገበቻቸው ቅርሶች ብዛት ከአፍሪካ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ንደሆነች አስፍሯል::

ይሁን እንጂ፣ ሀገራችን እንደ መስህብ ሀብቷ ብዛት እና አይነት ተጠቃሚ እንዳልሆነች መረጃዎች ይጠቁማሉ::

ይህም ሆኖ በሀገሪቱ ለጉብኝት ክፍት የሆኑትን ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች ለመጎብኘት ከሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኝዎች የሚፈልጉትን የመጓጓዣ፣ የማስጎብኘት፣ የማደሪያ፣  የስጦታ ዕቃዎች አቅርቦት…በማቅረብ እና አገልግሎቱን በመስጠት የበርካቶች ሕይወት ከዘርፉ ጋር ተቆራኝቷል:: በዚህ ተጠቃሚ ከሆኑት የሀገሪቱ ክፍሎች የአማራ ክልል ተጠቃሽ ነው፡፡

ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ከሀገራችን አልፎ ክልላችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ… ግንባር ቀደም ሚና ያለው ቱሪዝም የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ እንቅስቃሴው በእጅጉ ተገድቦ ቆይቷል:: ለአብነትም ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው  የላሊበላ ከተማ ቱሪዝም በኮሮና ወረርሽኝ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እና በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት በመቀዛቀዙ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫናን ፈጥሯል።

ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ከ40 ሺህ በላይ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ይጎበኟት የነበረችው የላሊበላ ከተማ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ የጎብኝዎች ቁጥር በዓመት ወደ 776 ወርዶ እንደ ነበር  የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ አስታውሰዋል:: የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ከተገታ በኋላ ግን  ዘርፉ  በ2015 እና በ2016 ዓ.ም መጠነኛ መነቃቃት ማሳየቱን አንስተዋል::

ይህን ጅምር እንቅስቃሴ ለማስቀጠልም በተደረገው ጥረት በ2017 ዓ.ም ለገና በዓል የመጡትን ሳይጨምር በአምስት ወራት ላሊበላን 930 የውጪ ሀገር ቱሪስቶች መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል:: ፍሰቱም ካለፈው ዓመት የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ሕርያቆስ ፀጋዬ በሰጡት መረጃ በ2016 ዓ.ም በነበረው የፀጥታ ችግር የተነሳ አንፃር ለገና በዓል ይመጣሉ ተብሎ ሲጠበቁ ከነበሩ ሁለት ሚሊዮን እንግዶች ሩብ ያህሉ ብቻ መምጣታቸውን አስታውሰዋል::

ይሁንና አሁን ላይ  አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ /ሰኔ 30/ የጎብኚዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ሌላዋ የጉብኝት መዳረሻ እና በቱሪዝም የጉዞ መስመር ላይ የምትገኘው የባሕር ዳር ከተማም  የቱሪስት ፍሰት መቀዛቀዝ ዳፋዉ ደርሶባታል።ይህ ሁኔታ ያሳሰበዉ የከተማዋ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያም  የተፋዘዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ከስምንት ዓመት በፊት የተጀመረውን “ጥርን በባሕር ዳር” መርሃ ግብር በደመቀ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን  አስታውቋል::መምሪያ ኃላፊው አቶ ጋሻው እንዳለው እንደሚሉት ከተማዋን በተለይም የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ፕሮግራም ይዘው እንዲጎበኟት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል:: በከተማዋ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሁነቶች በብዛት የሚከበርበት ወር ተመርጦ “ጥርን በባሕር ዳር” በሚል ጥር ወርን በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሯን ቀጥላለች፡፡

ለእንግዶች በሚመች መልኩ የጥር ወር ማድመቂያ መርሐግብሮች ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ኃላፊው አስታውሰዉ ዘንድሮም ከጥር 01 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2017 ድረስ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ እና የከተማዋን ገጽታ የሚገነቡ የተለያዩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሁነቶች እንደሚከናዎኑም አስታውቀዋል፡፡

በሂደቱ የንግድ ባዛርና ኤግዚቢሽን፣ የኪነ ጥበብ በዓልና ፌስቲባል፣ የቱሪዝም መዳረሻ መሠረተ ልማቶች ጉብኝት፣ የብስክሌት ሽርሽርና ባሕር ዳርን የማስዋብ ዘመቻ በጥር ወር ከሚካሄዱ  መርሃ  ግብሮች መካከል እንደሆኑም ነው ያብራሩት:: በተመሳሳይ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል በተለመደ ድምቀቱ ለማክበር የከተማዋ ወጣቶች  በርካታ ሥራዎችን  አከናውነዋል፡፡

በተመሳሳይ በጎንደር ከተማም የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው:: ለአብነት  የጥምቀት በዓልን በታላቅ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓት ለማክበር ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ዮሴፍ ደስታ አስታውሰዋል:: በዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ ለማክበር ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደተሠራም ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል:: ለዚህም የጥምቀት በዓል የሚከናወንበት እና ታቦታቱ የሚያርፉበት የፋሲለደስ የባሕረ ጥምቀት ስፍራ የጥገና ሥራ 95 በመቶ መከናወኑን አረጋግጠዋል።

የበዓሉን ስፍራ ውበትና ጽዳቱን የሚያስጠብቁ እና በዓሉን ለመታደም የሚመጡ ምዕመናንን፣ ሊቃውንትን፣ ቀዳሾችንና አባቶችን እንዲሁም ሌሎች አንግዶችን ቦታ የሚያስይዙና ሰላሙን የሚያስጠብቁ ወጣቶች ቀድመው  ዝግጅት ማድረጋቸውንም ዋና ሥራ አሥኪያጁ  ገልጸዋል። የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያዊ መሠረቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ መንፈሳዊ፣ ሃይማታዊና ባሕላዊ ትውፊት ሥርዓት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ዝግጁቱም ይህንን መሠረት ያደረገ እንደነበር አክለዋል።

መንግሥት በኮሪደር ልማት በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የመስቀል አደባባይ የቀደመ ታሪክ ጠብቆ በማልማት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ለማጎናጸፍ ያከናወናቸውን ተግባራት በማውሳት አባ ዮሴፍ አመስግነዋል። ጥምቀትን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችና ጎብኚዎች ከበዓሉ በተጨማሪ በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ለበኵር ጋዜጣ እንዳስታወቁት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ቱሪዝሙን ክፉኛ ጎድተውታል። የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቀዛቀዝ በተለይም ህልውናቸው ሙሉ በሙሉ በቱሪዝም ገቢ ላይ ለተመሠረተው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ አደጋ ሆኖ ቆይቷል:: አሁን በክልሉ እየተከበሩ ያሉት በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት የተዳከመውን የክልሉን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ያላቸው አበርክቶ ጉልህ ነው።

በክልሉ እስካሁን በጥናት የተለዩ 300 የሚሆኑ ዓመታዊ ክብረ በዓላት በድምቀት እንደሚከበሩ አቶ መልካሙ ተናግረዋል።

ለአብነትም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ፣ የጥምቀት በዓል በጎንደር እና በምንጃር ሸንኮራ፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ የቃና ዘገሊላ፣ አስተሪዮ ማርያም በመርጦ ለማርያም፣ በግሸን ደብረ ከርቤ እና በደረስጌ ማርያም፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ የግሽ ዓባይ (ሰከላ) ዓመታዊ የዘራብሩክ ክብረ በዓል፣ የመርቆሪዮስ ዓመታዊ በዓል በደብረ ታቦር እና በእስቴ መካነ ኢየሱስ በድምቀት የሚከበሩ በዓላት ሲሆኑ ለቱሪዝሙ መነቃቃት ትልቅ ድርሻ አላቸው። እነዚህ በዓላት ከታኅሳስ ወር ጀምሮ እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ በድምቀት የሚከበሩ እና ጎብኚዎችን የሚስቡ ታላላቅ ሁነቶች ናቸው።

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here