በአራቱም የዓለም ማዕዘን ያለ የእግር ኳስ ደጋፊ እና ተመልካች ለአፍታ እንኳ ትኩረት የማይነፍገው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ፉክክር ይበልጥ አጓጊ እየሆነ መጥቷል። ባልተጠበቁ ሁነቶች እና ድራማዊ ክስተቶች እየታጀበ ከሳምንት ሳምንት እየቀጠለ ነው። ከየትኛውም የአምስቱ ታላላቅ ሊግ የበለጠ ጠንካራ ፉክክር እየተስተዋለበት ይገኛል።
እንደ ፕሪሚየር ሊጉ ድረ ገጽ መረጃ ከሆነ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት 22ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ድረስ በሂሳባዊ ስሌት አምስት ክለቦች ሻምፒዮን ለመሆን ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። ሊቨርፑል፣ አርሴናል፣ ኖቲንግሀም ፎረስት፣ ቸልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ እየተፎካከሩ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የ22ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ድረስ ሊቨርፑል 50 ነጥብ በመያዝ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ይገኛል። አርሴናል በ44 ነጥብ ይከተላል። ኖቲንግሀም ፎረስትም በአርሴናል የግብ ልዩነት ተበልጦ በእኩል 44 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። ቸልሲ በ40 እና ማንቸስተር ሲቲ በ38 ነጥብ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ኢፕሲዊች ታውን፣ ሊሲስተር ሲቲ እና ሳውዝ አምፕተን ታች ግርጌ ላይ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል በአዲሱ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት እየተመራ አስደናቂ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ነው። በተለይ ደግሞ ባለቀ ሰዓት ግቦችን በማስቆጠር እና በማሸነፍ ትክክለኛ የዋንጫ ቡድን መሆኑን እያሳየ ነው። በ22ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከመደበኛው ዘጠና ደቂቃ በኋላ በጭማሪው ሰዓት ከሜዳው ውጪ ብሬንትፎርድን ሁለት ለባዶ ያሸነፈበት መርሀ ግብር ለአብነት የሚጠቀስ ነው። በዚህ መርሀ ግብር 37 ሙከራዎችን በማድረግ በ2005 እ.አ.አ በቸልሲ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበሩም የሚታወስ ነው።
እስከ መጨረሻዎች ሽርፍራፊ ሴኮንድ በመታገል እና አጋጣሚዎችን በመጠቀም በዚህ ዓመት ከሊቨርፑል የተሻለ ክለብ የለም። ቀዮቹ ዘንድሮ ሜዳ ላይ ምርጥ ከሚባሉ የዓለማችን ክለቦች መካከል ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋሉ። ታታሪነታቸው፣ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ፈጣን መሆን፣ አስፈሪ የፊት መስመር ጥምረት ያላቸው በመሆኑ እና ጠንካራ የኋላ ክፍል መያዛቸው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል።
የአርኔ ስሎት ቡድን ከባለፉት 21 ጨዋታዎች ውስጥ በአንዱ ብቻ ነው የተሸነፈው። በአሥራ አምስት ጨዋታዎች አሸንፏል፤ በአምስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል። ሊቨርፑል ዘንድሮ በርካታ ግቦችንም ያስቆጠረ ቀዳሚው ክለብ ጭምር ነው። በአማራጭ የተጫዋቾች ስብስብ የተሞላው የአንፊልዱ ክለብ ሙሀመድ ሳላህ፣ ሊዊስ ዲያዝ እና ኮዲ ጋክፖ እስካሁን ብቻ 32 ግቦችን አስቆጥረዋል። ይህም ሳላህን፣ ፌርሚኖን እና ማኔን ይዞ ከነበረው ከቀድሞው ስብስብ ጋር እየተነጻጸረ ይገኛል።
ሊቨርፑል በሁሉም የሜዳ ክፍል አማራጭ ተጫዋቾችን መያዙ ዓመቱን በሙሉ በወጥነት እንዲጓዝ አስችሎታል። የፊት መስመሩን ብቻ እንኳ ብንመለከት በመሀመድ ሳላህ፣ በሊዊስ ዲያዝ እና በኮዲ ጋክፖ ምትክ ዳርዊን ኑኔዝ፣ ፌድሪኮ ኬሳ፣ ዲያጎ ጆታ እና ሀርቬ ኢሊዮት የፊት መስመሩን መምራት ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለዋንጫ ፉክክሩ ትልቅ አቅም ይፈጥርላቸዋል።
በተጨማሪም ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በሙሉ ጤንነት ላይ መገኘት ቡድኑ በወጥ አቋም እንዲጓዝ አድርጎታል። በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከአንፊልድ ሮድ እንደሚለቅ እየተነገረ ያለው ሙሀመድ ሳላህ 18 ግቦችን ከመረብ በማገናኝት እና 13 ግብ የሆኑ ኳሶችን ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ በማቀበል ለክለቡ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
ኦፕታ አናሊስት በትንታኔው ከብሬንትፎርድ ጨዋታ በፊት ሊቨርፑል 86 ነጥብ አምስት በመቶ ዋንጫውን የማሸነፍ ግምት እንዳለው አስቀምጦ ነበር። ከጨዋታው በኋላ ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ ዋንጫው ለሊቨርፑል መሆኑን ግምት ተሰጥቶታል። የርገን ክሎፕ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በሰባተኛ ዓመቱ ማሳካቱ አይዘነጋም። ታዲያ ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ግን በመጀመሪያው የውድድር ዓመት በዋንጫ ታጅቦ ያጠናቅቃል የሚል ግምት ገና ከወዲሁ አግኝቷል። የመርሲሳይዱ ክለብም በውድድር ዘመኑ መጨረሻ 20ኛ ዋንጫውን በማንሳት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያለውን ክብረ ወሰን ይጋራል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ የነበረው አርሴናል ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ አቅሙ ተዳክሞ ተስተውሏል። አርሴናል በ44 ነጥብ ሊቨርፑልን እየተከተለው ቢሆንም ገና ከወዲሁ ግን እየተንገዳገደ ነው። አማራጭ እና ጨራሽ የፊት መስመር ተሰላፊ ባለመያዙ ቡድኑ በተደጋጋሚ ዋጋ ሲከፍል ተስተውሏል።
አርሴናል ዘንድሮ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ በላይ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ባደረገው ጨዋታ ሁለቱን ብቻ ነው ያሸነፈው። በአጠቃላይም 13 ነጥብ ብቻ ነው የሰበሰበው። የሰሜን ለንደኑ ክለብ በደረጃ ሰንጠረዡ ከወገብ በታች ካሉ ክለቦች ጋር ደግሞ ካደረጋቸው ጨዋታዎች 31 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል።
እስካሁን 12 ጨዋታዎችን አሸንፏል፤ ስምንቱን ጨዋታ ነጥብ ሲጋራ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፏል በአንድ ጨዋታ አቻ ሲለያይ ቀሪውን ግን አሸንፏል። አርሴናል ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ክለብ ነው። ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርገው ሽግግርም ፈጣን እና ጥሩ ነው። በተደጋጋሚም የተጋጣሚን የግብ ክልል ይጎበኛል። ይሁን እንጂ ግብ ለማስቆጠር ግን ዐይን አፋር እንደሆነ በየጨዋታው እየተመለከትን ነው። በእንቅርት ላይ… እንዲሉ ጋብሬል ጀሱስ እና ቡካዮ ሳካ ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ መሆናቸው እንዲሁም ጋብርኤል ማርትኔሊም ጥሩ ብቃት ላይ አለመሆኑ ችግሩን አባብሶታል። የመድፈኞቹ ስብስብ ጥልቀት እና አማራጭ የሌለው በመሆኑ ብዙ ተጫዋቾች ያለተፈጥሯዊ ቦታቸው ነው እየተጫወቱ የሚገኙት። ለአብነት የተከላካይ አማካኙ ቶማስ ፓርቴ በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ የቀኝ ተመላላሽ ሆኖ መጫወቱ አይዘነጋም።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም የጥር የዝውውር ወቅት ከመዘጋቱ በፊት አጥቂ ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተሰምቷል። ከወልቭሱ ማቲያስ ኩናህ፣ ከአርፒ ላይፕዚንጉ ቤንጃሚን ሴሴኮ እና ከናፖሊው ቪክተር ኦስሜህን ጋር ክለቡ በስፋት ስሙ እየተነሳ ነው። አርሴናል ትክክለኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን እና በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በዋንጫ ታጅቦ ለማጠናቀቅ በሁሉም የሜዳ ክፍል ቢያንስ ተጨማሪ ሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈርም እንዳለበት ስካይ ስፖርት አስነብቧል።
እንደ ስካይ ስፖርት ዘገባ አርሴናል በቀሪ ጨዋታዎች የማጥቃት ሚዛኑን በቀኝ ብቻ ሳይሆን በግራ በኩልም ማድረግ ይጠበቅበታል። የሚያገኛቸውን የግብ ዕድሎችም በትክክል መጠቀም እንዳለበት መረጃው ያስነብባል። የክለቡ እነዚህ ዋነኛ ችግሮች ከተፈቱ ዋንጫውን ለማሸነፍ በኦፕታ አናሊስት አሁን ላይ ከተሰጠው ስምንት ነጥብ ሁለት በመቶ ከፍ ይላል።
በዓመቱ መጀመሪያ የአምናው አሸናፊ ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮም ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳል ተብሎ ቅድመ ግምት ተሰጥቶት ነበር። ውድድሩ ተጀምሮ ሳምንታት ሲነጉዱ ግን አቋሙ ተንሸራቶ መጥፎ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በተከታታይ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ በማሽነፍ መጥፎ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል። በተለይ ሀላንድ፣ ፎደን፣ ዲብሮይን እና ጉንዶጋንን የመሳሰሉት በወጥ አቋም ላይ አለመገኘታቸው ቡድኑ እንዲንገዳገድ አድርጎታል።
ውኃ ሰማያዊ ለባሾች ክፍተታቸውን ለመሙላትም በጥር የዝውውር ወቅት ተጫዋች ለማስፈርም እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ግብጻዊውን ኮከብ ኦማር ማርሙሽን ከኢንትራክት ፍራንክፈርት ለማስፈረም ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተዘግቧል። በቀጣይም ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርሙ ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።
በኢትሀድ መጥፎ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ያለው ፔፕ ጓርዲዮላ ከ30 ዓመት የትዳር አጋሩ ጋር በቅርቡ ተለያይቷል። በእግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ እና ለቤተሰቡ ጊዜ አለመስጠቱ ለፍቺ እንዳበቃው ተዘግቧል። በዚህ ሁሉ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ የሚገኘው ስፔናዊው አሰልጣኝ በተከታታይ ለአምስተኛ ጊዜ ዋንጫውን የማንሳት እድሉ ጠባብ ነው ተብሏል። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ግን ይዞ ያጠናቅቃል ሲል ኦፕታ አናሊስት አስነብቧል፡፡
ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በተሻለ ጥልቅ ስብስብ የያዘው ቸልሲ አጀማመሩ ጥሩ እንደነበር የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ የሚመራው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በ40 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከሊቨርፑል በ10 ነጥብ ይርቃል። ምንም እንኳ በሂሳባዊ ስሌት ከዋንጫ ፉክክሩ ባይወጣም በኦፕታ አናሊስት ቅድመ ግምት ግን ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቅቃል ተብሏል።
በዚህ ዓመት ክስተት የሆነው ኖቲንግሀም ፎረስት በ44 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። በዚህ አቋሙ ከቀጠለ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የአውሮፓ ተሳትፎን የማረጋገጥ እድል ይኖረዋል። ኒውካስትል ዩናይትድ፣ በርንማውዝ እና አስቶንቪላም የአውሮፓ ተሳትፎን ለማረጋገጥ እልህ አስጨራሽ ትግል እንደሚያደርጉ ይገመታል።
ሳውዝ አምፕተን፣ ኤቨርተን፣ ወልቭስ፣ ኤፕስዊች ታወን እና ሊሲስተር ሲቲም የመውረድ ስጋት ያለባቸው ክለቦች ናቸው። ማን ዋንጫውን ያሳካል? የትኞቹ ክለቦችስ የአውሮፓ ተሳትፎን ያሳካሉ? የትኞቹ ይወርዳሉ? በውድድር ዘመኑ መጨረሻ አብረን የምናየው ይሆናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም