የ“888 ሕግ”

0
132

አንድ ወዳጄን የጊዜ አጠቃቀም ጠየቅሁት። እንዲህ አጫወተኝ። “በቃ ምሽት 11 ሰዓት ከቢሮ እንደወጣሁ ሻይ ቡና ለማለት ካፌ እቀመጣለሁ። ቤት ስራ ስለሌለኝ ቶሎ አልገባም። ሻይ ቡና እያልን ጓደኞቼ ጋር ስናወራ አንድ ሰዓት ይሆናል። ከዚያ ቤቴ ገብቼ ያንም ይህንም ስል ይመሻል። ኢንተርኔት እጠቀማለሁ። ቴሌቪዥን ከፍቼ ዜና ሳይ ይመሻል። እስከ አራት ሰዓት ቲክቶክ፣ ፌስቡክም ሳይ እቆያለሁ። እንቅልፌ ሲመጣ እተኛለሁ። አንዳንድ ቀን ሌሊት 11 ሰዓት እነቃለሁ፤ እንደነቃሁ ዓለም እንዴት አደረች ብዬ መረጃ ከኢንተርኔት አያለሁ። በምን ፍጥነት እንደሆነ አይገባኝም ስልኬን ስጎረጉር ሁለት ሰዓት ይሆናል። በፍጥነት ታጥቤ ወደ ቢሮ እገባለሁ” ይላል ጓደኛዬ። ብዙዎች በዚህ አኗኗር ውስጥ አለንበት።

ስለ ስራ ማውራት ስለሁሉም የሰው ልጅ ማውራት ነው። ይብዛም ይነስ ሳይሰራ የሚኖር የለም። እንደስራው ብዛት እና ማነስ  የሚያገኘውም የገቢ መጠን ይለያያል። አሜሪካ እና ኢትዮጵያ አሁን ያሉበት የኢኮኖሚ አቅም ልዩነት የስራ አፈጻጸም እንጂ ሌላ አይደለም። ለምን አልሰራንም የሚለው ሌላ ሰፊ ምክንያቶች ቢኖሩትም፤ እውነታው ግን በመስራት የከበሩ እንዳሉ ሁሉ ባለ መስራት የተዋረዱ ሀገራት አሉ።

የስራ ጉዳይ ከሀገር ዝቅ ሲል በግለሰቦችም መካከል ትልቅ ልዩነት የሚፈጥር ነው። የሚሰሩ እጆች ጦም አያድሩም። ሀብት እና ጥሪትም የሚያስቀምጡ እነሱ ናቸው። በሰበብ እና ምክንያቶች የሰነፉ እጆች ለልመና መዘርጋታቸው አይቀሬ ነው። በምድር እንኳን ለትውልድ የሚተላለፍ ሀብት ይቅርና ለወራት የሚበሉትም የላቸውም።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ እንዳንሰራ የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ። ስራ ራሱ የለም፤ ሰላም ይቸግረናል፣ ድጋፍ የለም፤ ገንዘብ እና ገበያ የለም፤ ክፍያው አበረታች አይደለም። የመንግሥት ፖሊሲ እና አሰራር ሰራተኛን የሚያግዝ አይደለም። የስራ አካባቢያችን ምቹ አይደለም። ሌሎችንም ምክንያቶች ጠቅሰን ለመስራት እንዳልቻልን በማስረጃነት ልናነሳ እንችላለን። ይሁን እንጂ ማንም እነዚህን ችግሮች በመቁጠር አልተለወጠም፤ ከችግሮቹ በላይ መውጫ ቀዳዳ በመፈለግ እንጂ።

ስራ ባይኖርም ቢያንስ ስራ ያለን ሰዎች በአግባቡ መስራት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ እንነጋገር። የሐበሻ ጊዜ አጠቃቀም በሚል የዓለም መሳቂያ፣ መሳለቂያ ነን። የስራ ባህላችን ሰነፎች የሚያስብለን ነው። ሰበብ በመደርደር እና ምክንያቶችን በማስቀመጥ ላለመስራት የምናቅድ ነን። ትንሽ ሰዓት ሰርተን ረጂሙን ጊዜ በወሬ እና አሉባልታ የምናሳልፍ ነን። በማህበራዊ ሚዲያው ቀልባችን ተጠልፎ ስራችንን ያጠፋብን ብዙ አለን። ዛሬ መስራት የሚገባንን የምናሳድር፣ ለሰው የምንገፋ፣ ጉልበት የምንቆጥብ ብዙ ሰነፎች አለን። ይህ ጽሑፍ እኛን የሚመለከት ነው።

ስለ ስራ ስናወራ ዋናው መዋኛው ሐይቅ ጊዜ መሆኑን አንረሳም። የጊዜ አጠቃቀማችን ነው ለዛሬም ሆነ ለነገ ትልቅ መሰረት ያለው። ጊዜ ራሱን በነጻነት ሰጥቶናል። እኛ  ደግሞ በመኖር  ጠዋት ማታ፣ ትናንት ዛሬ፣ ነገ ከርሞ ፣ ሰኞ ማክሰኛ ብለን ከፋፍለነዋል። የሰው ልጆች አኗኗር የጊዜ አጠቃቀም ውጤት ነው። “አካሄዱን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል” እንደሚባለው፤ የሰውን አኗኗር በማየት ሕይወቱን መገምገም፤ የኢኮኖሚ አቅሙን ማወቅ ይቻላል። ገንዘብ በስራ ይገኛል። ትናንት ቢያመልጠን ነገ ሰርተን እናገኛለን። ዛሬ ቢርበን ነገ ሰርተን እንበላለን። ድጋሚ የማይገኝ ነገር ጊዜ ነው። ልጅነት ካለፈ፤ ወጣትነት ካለፈ፤ ጎልማሳነት ካለፈ፤ ሽምግልና ካለፈ አይመለስም። ጊዜ በዚህ መጠን ቆራጥ፣ ወደ ፊት ገስጋሽ መንገደኛ ነው። በወጣትነት እድሜ ያልሰራነውን ገንዘብ በእርጅና ዘመን አናገኘውም። በልጅነት ያልቦረቅን ሰዎች በወጣትነት ልንቦርቅ አንችልም።

ለሁላችንም እኩል ራሱን እንደ ጊዜ በፍትሐዊነት የሰጠን የለም። ሀያ አራት ሰዓት ለሁሉም ተሰጥቷል።  ሳላሪ ድረ ገጽ አራት በመቶ  የተቋማት ሰራተኞች ስልካቸውን በስራ ቦታ ለጽሑፍ መልእክት እና ለድምጽ ጥሪ ይጠቀማሉ። ሠላሳ አምስት በመቶ ደግሞ በኢንተርኔት ጌሞችን ይጫዎታሉ፤ እቃ ይገዛሉ። አርባ ሦስት በመቶ የሚሆኑትም እንዲሁ ስራቸውን ትተው ጓደኞቻቸው ጋር ይጻጻፋሉ፤ ያወራሉ ብሏል።  ይህ ጥናት ዓለም አቀፍ መረጃ ነው።

ከኢትዮጵያ ሰራተኞች በተሻለ የስራ ስነ ምግባር ባለባቸው የዓለም ሀገራት ነው እንዲህ እየሆነ ያለው። በካሜራ ዕይታ ውስጥ ሆነው በሚሰሩ ሰራተኞች ነው ይህ መረጃ የተገኘው። በእኛም ሀገር በግል እና የመንግስት ተቋማት ውስጥ ስራን መበደል በጣም የተለመደ ነው። ለሽንት እንኳን መነሳት የማያስችል ስራ ውስጥ የሚሰሩትን በማክበር ነው ሰነፎችን የምጠቅሰው። የስራ ሰዓት በብዙ ምክንያቶች ይባክናል። በተለይ በመንግስት ተቋማት ዘንድ ይህ ክፍተት በጉልህ ይነሳል። ደንበኛን ማጉላላት፣ ማመላለስ፣ ማርፈድ፣ ማልመጥ፣ መጥፋት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

ማህበራዊ ሚዲያ እና በይነ መረብ ስራን ከሚያውኩ ተግባራት መካከል አንዱ ነው። ደንበኞችን አቁመው ጓደኞቻቸው ጋር የሚያወሩ፣ ስለሳምንቱ ቀናቸው የሚያወሩ፣ የቤት ጉዳያቸውን የሚያቅዱ፣ ገበያ ሲሄዱ ስለሚገዙት የሚያስቡ ሰራተኞች አይታጡም። ስብሰባዎች አሁን የስራ አካል ሆነዋል። በዚህም በብዙ ተቋማት በስብሰባ ምክንያት ስራ ይበደላል። ጊዜ ይባክናል፤ ገንዘብ ይጠፋል፤ ተገልጋይ ይንገላታል። የስራ ባህልም ደካማ ነው። ብዙዎቻችን ለረጂም ሰዓታት ትኩረት አድርገን መስራት አንችልም፤ ራሴን፣ ወገቤን፣ ልቤን እንላለን። ግላዊ ጉዳዮችም ጊዜን ያባክናሉ፤ ስራን ይበድላሉ። “ጤፍ ተወደደ አሉ፤ ወይ እድላችን” ብለው ንግግር የጀመሩ ሰራተኞች የወደ ፊት ሕይወታቸው አሳስቧቸው ስራውን ችላ ሊሉት ይችላሉ። ልጇ የታመመባት እናት በተደጋጋሚ ቢሮ ላትገባ ትችላለች። ሐሳቧ እየተሰረቀ ስራውን በሚገባ አትሰራም። የሰው ልጅ አዕምሮ አንድ ነገር ላይ ትኩረት ሲያደርግ ይበልጥ አቅሙን ይጠቀማል። የስራ እቃዎች ማለትም ኮምፒዩተር፣ ማሽኖች፣ ስልኮች፣ ኢንተርኔት፣ ወንበር መኖር እና አለመኖር ስራን ተጽዕኖ ያሳድርበታል።

በጠዋቱ በተነቃቃ መንፈስ ቢሮ የገባ ሰራተኛ ኮምፒውተሩ ተበላሽቶ ቢጠብቀው የመስራት አቅሙ ይገታል። የተነቃቃው ወኔው ይቀዘቅዛል። ጉዳዩ ቀላል ይመስላል እንጂ በሰራተኛው አዕምሮ የሚያሳድረው ጫና ከባድ ይሆናል። ሐሜት፣ ወሬ እና ሌሎች ስራዎችን በኢንተርኔት መፈለግ በተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ የሚያደርጓቸው ናቸው ሲል ኢንድድ ድረ ገጽ ጽፏል።

ትሩዝ ዌልነስ ድረ ገጽ “888” የሚል የጊዜ አጠቃቀምን ሕግ ለተሻለ የስራ አፈጻጸም መፍትሔ አድርጎ አቅርቧል።

የ 888 ሕግ በአንድ ቀን ውስጥ ያሉ 24 ሰዓታትን ለሦስት  እኩል በመከፋፈል ስራን በትጋት߹ በጥራት߹ በውጤታማነት የመፈጸም ፍልስፍና ነው፡፡ ምርታማነትን ያሳድጋል߹ ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸውን ጉዳዮች እንድናስቀድምም እድል ይሰጣል፡፡ በሰለጠነው ዓለም ሁለንተናዊ ጤንነትም ለማምጣት የሚያግዝ የጊዜ አጠቃቀም ሕግ ተደርጎ ይሰራበታል፡፡

በዚህም መሰረት ሀያ አራቱን ሰዓታት በሦስት ይከፍለዋል። ስራ፣ መኝታ፣ እና የራስ መንከባከቢያ በሚል አስቀምጦታል።  የሰው ልጅ ውጤታማ ለመሆን ለስምንት ሰዓታት በቁርጠኝነት ይሰራል። ጤናውን ለመጠበቅ እና የደከመ ሰውነቱን እና አእምሮውን ለማደስ ስምንት ሰዓታት ይተኛል። ቀሪውን ስምንት ሰዓታት ደግሞ ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ እና የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ያውላል። ጤናውን እና ንጽሕናውን ይጠብቃል፤ የሚያስደስቱትን ተግባራት ይከውናል። ለሌሎች መልካም አገልግሎት የሚሰጥበት፣ነፍሱን እና ስሜቱን የሚያስደስትበት ተግባራትን ይከውንበታል።

ኢንድድ ድረ ገጽ ለጥሩ የስራ ክንውን እና ጊዜ አጠቃቀም ያወጣውን የ“888 ሕግ” መጠቀም ግለሰባዊ ጥንካሬን የሚሻ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ የቢሮ ስራ ለስምንት ሰዓታት የተገደበ ነው። ጥያቄው ይህንን ስምንት ሰዓት እንጠቀምበታለን ወይ፤ ቢሮ ገብቶ መውጣት ወይስ ሌሎች ከስራ ውጪ ያሉ ተግባራትን መከወን ነው የሚቀለን የሚለው ነው። ብዙዎቻችን ጠዋት ቢሮ እንገባለን። በትክክል ሰዓታችንን የምንጠቀምበት ምን ያህሎቻችን እንደ ሆንን የምናውቀው ራሳችን ነን። ከላይ የጠቀስናቸው በስራ ቦታ ጊዜ አባካኝ ተግባራት እንዳያዘናጉን መጠንቀቅ፤ ችግሮችን መለየት፤ ራስን ወደ ተግባር ማስገባትን ይጠይቃሉ። የቢሮ ስራችን በአልባሌ ተግባራት መባከኑ ጉዳቱ በመጀመሪያ እኛ ራሳችን ላይ ነው። በስራ ቦታ የሚፈጠር መዘናጋት ተቋሙን፣ ቤተሰብን እና ሀገርን የሚጎዳ ተግባር ነው።

ስምንት ሰዓቱን ቢሮ ውለን እንደወጣን ቀጣዩ ስምንት ሰዓት ምንድን በመስራት ነው ጊዜያችን የሚያልፈው? ሁለተኛው የጊዜ  ምዕራፍ ነው። ምናልባትም ይህ ጊዜ በሀገራችን በከንቱ ከሚባክኑት መካከል አንዱ ነው።

ራሳችንን ለመቀየር ትልቁ የጊዜ አቅም ይህ ነበር። ሦስተኛው የጊዜ ምዕራፍ ጥሩ እንቅልፍ  የምንተኛበት ነው። ሁለተኛውን ምዕራፍ በእቅድ ስለማንጠቀምበት አንደኛውን (የስራ) እና ሦስተኛውን (የመኝታ) ሰዓታችንን  ያዛባብናል። ሁለተኛው ምዕራፍ አደገኛ ጊዜ ነው። ለሚጠቀሙበት ብዙዎችን የሚለውጥ ነው። ለሚያላግጡበት ደግሞ ችግርን የሚያስታቅፍ ነው። ሁለንተናዊ ጤንነት፣ ጤናማ ቤተሰብ፣ ደስተኝነት የምንገነባበት ነው። ምናልባትም በሚያስደስቱን ፍላጎቶቻችን ሕይወት ቀያሪ ስራ ለመስራት የምንችልበት ሊሆን ይችላል። ሙዚቃ የሚወድ ሰው አቅሙን ማሳደጊያ እናም ጥሩ ሙዚቀኛ ለመሆን የሚዘጋጅበት የጊዜ ምዕራፍ ሁለተኛው ነው፤ ከእንቅልፍ በፊት፤ ከስራ በኋላ ያለው።

የ“888 የጊዜ አጠቃቀም ሕግ”ን ተግባራዊ ማድረግ ቢቻል በስራችን ጥሩ ትኩረት ማድረግ እንችላለን። በሕይወታችን ሚዛናዊ የስራ እና ረፍት ያለበት አኗኗር እንድንከተል ያስችለናል። አንዱን ስራ ከሌላ ጋር በማቀላቀል የሚደርስብንን ጭንቀት የሚቀንስልን ይህ ሕግ ነው። ጥሩ ውሳኔ ለመስጠት፤ ሥራን በሥነ ምግባር ታንጾ ለመሥራት እና የሥራ ውጤታማነትንም ለማሻሻል ይረዳናል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥር 19  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here