የውኃ ብክለትን የመግታት ጥሪ

0
121

ከሀይቅ፤ ከማጠራቀሚያ ጉድጓዶች እና ከወንዞች ተጠልፎ ረጅም ርቀት በሚጓጓዝ ያልታከመ ውኃ ያልተለመዱ እና ወራሪ ዝርያዎች ተሰራጭተው የከፋ አደጋ ከማስከተላቸው በፊት ለመግታት ጥሪ መቅረቡን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ዘግቧል፡፡

በእንግሊዝ የኒውካስትል እና የስተርሊንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባካሄዷቸው ምርምሮች ያልታከመ ውኃ ከተለያዩ ቋቶች ተጠልፎ ሲጓጓዝ ወራሪ እና ያልተለመዱ ዝርያዎች ይሰራጫሉ፡፡ በመሆኑም ውኃ ማስተላለፊያዎቹ በሚደርሱበት ቀጣና ዝርያዎቹ ተስፋፍተው ጉዳት ስለሚያስከትሉ የሚመለከታቸው አካላት አስቀድመው የመከላከል ርምጃ እንዲወስዱ ባለሙያዎቹ አሳስበዋል፡፡

ካልታከመ ማጠራቀሚያ እና ከወንዝ የሚወጣ ውኃ ከእንስሳት እንደ “ዛንደር፣ ሙስል” የተሰኙ የዓሣ ዝርያዎች ከዓረም እምቦጭ እና መሰሎች ወራሪ እና ጐጂ መሆናቸው በአብነት ተጠቅሰዋል፡፡

አጥኚዎቹ እንዳረጋገጡት ወራሪ ዝርያዎች ለብዝሃ ህይወት እና ለምጣኔ ሀብት እድገት ዓለም አቀፍ ስጋት ናቸው፡፡ ለዚህም በስነ ምህዳር ላይ ተፅእኖ ሳያደርሱ ቀድሞ መፍትሄ መሻት ተገቢ መሆኑን ነው አፅንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት- ባለሙያዎቹ፡፡ ባልታከመ ውኃ ዝውውር ላይ ቁጥጥር ማድረግ ከጀመሩ አገራት ፈር ቀዳጆች እንግሊዝ እና ስኮትላንድ ስማቸው ተጠቅሷል፡፡

ከኒውካስትል ዩኒቨርሲቲ ጥናት ካካሄዱት ተመራማሪዎች ዶ/ር አቫዋይን ያልታከመ የውኅ ዝውውር በተጨባጭ የሚያስከትለውን ጉዳት ጠቁመው በአገር ዓቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ፓሊሲ ላይ ለውጦችን ማካተት እንደሚገባ ነው ያሰመሩበት፡፡

ከስተርሊንግ ዩኒቨርሲቲ የጥናቱ ተባባሪ ተመራማሪ ዶ/ር ዛራፓቲስን በበኩላቸው ባልታከመ ውኃ ዝውውር የሚዛመቱ ወራሪ እና ባእድ ዝርያዎች መስፋፋትን ለመግታት እፅዋቱን እና እንስሳቱን ለይቶ ለማጥናት አገራት በገንዘብ መደገፍ እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

በመጨረሻም የተመራማሪዎቹ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወራሪ እና ያልተለመዱ ዝርያዎች የፀዳ ውኃ የሚሰራጭበትን ስልት እየነደፈ መሆኑ ነው በማጠቃለያነት ያሰፈረው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here