አቢያታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ

0
170

አቢያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ 207 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ለፓርኩ መመስረት በስምጥ ሸለቆ ቀጣና የሚገኙት አቢያታ እና ሻላ ሐይቆች ዋነኛ መሰረቶች ናቸው፡፡

ፓርኩ  ከባህር ወለል ከ1540 እስከ 2075 ሜትር ከፍታ መካከል እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡ አጠቃላይ ስፋቱ 88 ሺህ 700 ሄክታር ሲሆን የአብያታ እና ሻላ ሀይቅን የሚለያቸው ሦስት ኪሎ ሜትር የሚረዝም ኮረብታንም ያጠቃልላል፡፡

የቀጣናው የዓየር ንብረት ደረቅ የሚባል ሲሆን ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ ዝቅተኛው 500 ከፍተኛው 700 ሚሊ ሜትር፣ የዓየር ንብረቱ ዝቅተኛው 50፣ከፍተኛው 400 ዲግሪ ሲልሺየስ ተለክቷል፡፡ ከፍተኛ ዝናብ የሚጥልባቸው ወራትም ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት ናቸው፡፡

ፓርኩ ሰፊ ሳር ለበስ ሜዳን ያቀፈ ነው፡፡ በዋናነት የዓእዋፍ ጥበቃን መሰረት አድርጐ መቋቋሙም ነው በድረ ገፆች የሰፈረው፡፡ በመሆኑም የአቢያታ ሀይቅ ለዓእዋፍ መዋያ እና የምግብ ምንጭ መገኛ ሆኖ ሲያገለግል የሻላ ሀይቅ ግን  ጐጆአቸውን የቀለሱበት ማደሪያቸው እንደሆነ ነው የተመላከተው፡፡  ሻላ ሀይቅ ጥልቀቱ 260 ሜትር ሲሆን በኢትዮጵያ ካሉ ሀይቆች ቀዳሚ ነው ፡፡ በዳርቻው በርካታ ፍል ውኃዎችንም ይዟል፡፡

በፓርኩ በአጠቃላይ 457 የዓእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ በቀጣናው ከሚገኙት መካከል “ኋይት ፔሊካን እና ፍላሚንጐ” የተሰኙት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡

ከአጥቢ የዱር እንስሳት የሜዳ ፍየል፣ ዝንጀሮ፣ “ኩዱ” ቀበሮ እና ከርከሮ እንደሚገኙ ነው በድረገፆች የሰፈረው፡፡ በፓርኩ ውስጥ በልዩ ሁኔታ ተከልሎ ጥበቃ የሚደረግለት የሰጐን ማርቢም ይገኛል፡፡ ይሄ በአገራችን ካሉ ብሔራዊ ፓርኮች ተጠቃሽ መለያ፣ መገለጫውም ነው፡፡

ፓርኩን በቀጣይ በዘለቄታ ጠብቆ ለማቆየት የተለያዩ ሁነቶች በስጋትነት ተጋርጠውበታል፡፡ ከነዚህ መካከል በአጐራባች ቀጣና የኗሪዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ለመተዳዳሪያ የእርሻ ቦታ መስፋፋት የፓርኩን ክልል እያጠበበው መምጣቱ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኗሪዎች ሰፈራ በዙሪያው እየተበራከተ ወደ ቀጣናው ለከሰል ምርት እና ለማገዶ እንጨት ፍለጋ ጣልቃ መግባት  ስጋትነቱ በባለሙያዎች ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም የፓርኩን ዘለቄታዊነት ለማስቀጠል የሚመለከተው አካል ፈጥኖ ማስተካከያ እና የርምት ርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት ነው በማደማደሚያነት ለንባብ የበቃው፡፡

ለዘገባችን በመረጃ መንጭነት ናሽናል ፓርክወርልድ ዋይድ፣ አብሶሊውት ኢትዮጵያ እና ሪሰርች ጌት ኔት ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here