የመድን ሕግ የሚባለው የመድን ውልን የሚዳኝ ሕግ ነው፡፡ የመድን ሕግ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮችን አካቶ የያዘ እንደሆነ አቢሲኒያ ሎው (Abyssinia Law) ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመድን ውል በመድን ሰጪው (Insurer) እና በመድን ገቢው (Insured) መካከል የሚደረግ የሁለትዮሽ ውል ነው፡፡ በዚህም መድን ሰጪው በውሉ ላይ “የተጠቀሰው አደጋ በደረሰ ጊዜ በመድን ገቢው ላይ የሚደርሰውን የምጣኔ ሀብት ኪሳራ በውሉ ላይ ከተጠቀሰው መጠን ሳይበልጥ የመካስ ግዴታን ይቀበላል፡፡ በአንጻሩ መድን ገቢው በውሉ ላይ በተጠቀሰው ጊዜ እና መጠን የመድን መግቢያ ክፍያ (አረቦን) ለመድን ሰጪው የመክፈል ግዴታን ይወስዳል፡፡
ጉዳት የመድረስ ነገር ሲታሰብ በማንኛውም አጋጣሚ ሊፈጠር የሚችልና ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የሚኖር ነው፡፡ በመሆኑም በመድን ሕግ ጉዳትን አስቀድሞ እንዳይደርስ መከላከል ባይቻልም በጉዳቱ ሳቢያ የሚደርሱ የምጣኔ ሀብት ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል፡፡ ይህም የተበታተነ ሀብትን በማሰባሰብ ኢንቨስትመንት እና ቁጠባ እንዲያድግ ለሥራ እንቅስቃሴ ከአደጋ በፊትም ሆነ በኋላ ፍርሀትን እና ስጋትን ሊያስወግድ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ሃርቬይ ሩቢን ያዘጋጀው የኢንሹራንስ መዝገበ ቃላት ለመድን በሰጠው ትርጓሜ የመድን ውል በመድን ገቢው እና በመድን ሰጪው መካከል የሚደረግ እና በሕግ አስገዳጅነት ያለው የሁለትዮሽ ውል ሲሆን በውሉም መድን ሰጪው ከመድን ተቀባዩ ለመድን መግቢያ የሚከፈለውን ክፍያ እየተቀበለ በውሉ ላይ የተገለፀው አደጋ በመድን ተቀባይ ላይ በደረሰ ጊዜ የተወሰነ ገንዘብ ለመክፍል የሚደረግ ስምምነት ነው የሚል ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ትርጓሜ መረዳት የሚቻለው የመድን ውል በመድን ገቢ እና በመድን ሰጪው (ኢንሹራንስ ኩባንያ) መካከል የሚደረግ ስምምነት ሲሆን ይህ ውል በእነዚህ ተዋዋይ ወገኖች ላይ ተነፃፃሪ መብት እና ግዴታዎችን ያቋቁማል፡፡
በሀገራችንም በ1952 ዓ.ም በወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ (የነባሩ የንግድ ሕግ 3ኛ እና 4ኛ መጽሐፍ ኢንሹራንስ እና ባንክን የሚመለከተው ያልተሻረ በመሆኑ) አንቀጽ 654 ንዑስ ቁጥር አንድ ላይ “የኢንሹራስ ውል ፖሊሲ ማለት ኢንሹራንስ ሰጪ የሚባለው በአንድ ወይም በብዙ የተመደበውን የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕሪምየም) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ነው” በማለት ትርጉሙን አስቀምጧል፡፡
ከትርጉሞች መረዳት የሚቻለው መድን ወይም ኢንሹራንስ ማለት አንድ ሰው ባልተጠበቀ አደጋ ለመጣበት ሕጋዊ የፍትሐብሔራዊ ተጠያቂነትን፣ በንብረቱ፣ በሕይወቱ ወይም በአካሉ ላይ ለደረሰው ጉዳት አስቀድሞ ከኢንሹራንስ ድርጅት ጋር በገባው ስምምነት መሠረት የሚከፈለው የካሳ ክፍያ ስምምነት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት የኢንሹራንስ ድርጅቱ አስቀድሞ በተስማማው መሠረት የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) በመሰብሰብ አደጋው በደረሰ ጊዜ ጉዳቱ ለደረሰበት ሰው ካሳ የሚከፍልበት እና ከጉዳቱ እንዲቋቋም የሚያደርግ መንገድ ነው፡፡
የመድን አስፈላጊነት
መድን ወይም ኢንሹራንስ እጅግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ጠቀሜታዎቹ ውስጥ አንደኛው በአንድ ሰው ላይ የሚደርስን የፍትሀብሔር ተጠያቂነትን፣ የንብረት ጉዳትን፣ ሞትን ወይም የአካል ጉዳትን መሠረት አድርጎ የሚደርስን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን በካሳ መልክ የኢንሹራንስ ድርጅቱ ስለሚከፍለው በተቻለ መጠን ያ ሰው ጉዳቱ ሳይደርስ ወደ ነበረበት የኢኮኖሚያዊ አቅሙ መመለስ ማስቻሉ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ጉዳት አድራሹ ወይም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የከፋ ኪሳራ ውስጥ እዳይገቡ የሚያደርግ እና ማኅበረሰቡም ከጉዳቱ በላይ በጉዳቱ ምክንያት ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይደረግ ያደርጋል፡፡
ሌላው የመድን አስፈላጊነት የመድን ድርጅቶቹ ጉዳትን በተመጣጠነ ሁኔታ ማከፋፈላቸው ነው፡፡ ይህም ማለት የኢንሹራንስ ድርጅቶቹ ተመሳሳይ የጉዳት ስጋት ካለባቸው ሰዎች ተመጣጣኝ የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕሪምየም) በመሰብሰብ ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳ ይከፍላሉ፡፡
መድን ለኅብረተሰቡ ብሎም ለሀገር ቁጠባን በማሳድግ እና ኢንቨስትመንትን በመደገፍም የላቀ ጠቀሜታ ያበረክታል፡፡ የኢንሹራንስ ድርጅቶቹ ከኢሹራንስ ገቢዎች በቋሚነት የሚሰበስቡት ክፍያ (ፕሪምየም) ለሰዎች በቁጠባ መልክ የሚቀመጥላቸው ነው፡፡ ይህም ቁጠባን ያበረታታል፤ ያሳድጋል፡፡ ቁጠባ ባደገ ቁጥር ደግሞ ለኢንቨስትመንት መሠረት ይሆናል፡፡
የመድን አይነቶች
መድን ወይም ኢንሹራንስ የፍትሀብሔር ተጠያቂነትን፣ የንብረት፣ የሞትን፣ የአካል እና ሌሎች ጉዳዮችም ዋስትና የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ መድንን ወይም ኢንሹራንስን የዘርፉ ምሁራን በተለያዬ መልኩ ከፋፍለዋቸዋል፡፡ በዋናነትም የሕይወት፣ የንብረት እና የፍትሀብሔር ተጠያቂነት መድን በማለት፡፡ ነገር ግን ከዚህም በላይ ዘርዘር በማድረግ የሚከፋፍሉ ምሁራንም አሉ፡፡ እነዚህም የጤና፣ የተሽከርካሪ፣ የሕይወት፣ የእሳት ቃጠሎ፣ የጉዞ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የሥራ አጥነት፣ የትራንስፖርት፣ የተሸከርካሪ አደጋ እና የሕጋዊ ኃላፊነት መድን ናቸው፡፡ በሀገራችንም የተለያዩ የመድን አይነቶች በመድን /ኢንሹራንስ/ ድርጅቶች ይሰጣሉ፡፡
የሦስተኛ ወገን መድን
በተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አንድም ጉዳት አድራሹ ባለመታወቁ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳት አድራሹ ቢታወቅም ጉዳቱን ያደረሰው ተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የሌለው በመሆኑ ተጎጂዎቹን ለባሰ ስቃይ እና እንግልት የሚዳርጋቸው ጉዳይ ነው፡፡
እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አስገዳጅ በሆነ መልኩ በሕግ ተደንግጎ መኖር እጅጉን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በሀገራችን ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችል ሕግ ወጥቶ በሥራ ላይ ውሎ ይገኛል፡፡ የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2002 ባሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኝ ሕግ ነው፡፡
ሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሚሸፍነው ጉዳት እና የሚሸፈኑት የጉዳት አይነቶች ተሽከርካሪው ለሚያደርሰው ግጭት፣ የእሳት ቃጠሎ ወይም ፍንዳታ፣ የተሸከርካሪው ጭነት፣ አካል ወይም መሣሪያ ወድቆ ለሚያደርሰው ጉዳት እና ከተሽከርካሪው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የሚደርስ ማንኛውንም ጉዳት ያካትታሉ። በአዋጁ አንቀጽ አራት ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ በተገለፀው መሠረት በሀገራችን ያለው የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ፖሊሲ መድን የተገባለት ተሽከርካሪ ለሚያደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ኪሳራ መከፈል የሚገባውን ካሳ እና አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ወጪ የሚሸፍን ነው፡፡
ነገር ግን የመድን ገቢው ወይም ቤተሰብ (የትዳር ጓደኛ፣ ልጅ፣ አባት፣ እናት ወይም የሚያስተዳድረው ማንኛውም ሰው) ላይ የሚደርስ ሞት፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት፣ በመድን ገቢው ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው በሥራው ላይ እያለ በሚደርስ የግጭት አደጋ ወይም የሞት ወይም የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ጉዳት፣ መድን በተገባለት ተሸከርካሪ ላይ በኪራይ ወይም በክፍያ በሚጓጓዝ ንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት እና ከኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውጪ የደረሰ የተሸከርካሪ አደጋ ተከትሎ የመጣ ኃላፊነትን እንደማይሸፍን እና ካሳ እንደማይከፍል ከአዋጁ አንቀጽ ሰባት ሰፍሯል፡፡ በሌሎች ሕጎች ግን ጉዳት አድራሹ ወይም ተሽከርካሪው የመድን ሽፋን ካለው መድን የሰጠውን ኩባንያ ካሳ የመጠየቅ መብታቸው እንደ ተጠበቀ ነው።
የተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና
የተሸከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና በተገባለት ተሽከርካሪ ላይ ድንገተኛ ለሚደርስ ግጭት ወይም መገልበጥ ወይም በእሳት ፣ ከውጭ በደረሰ ፍንዳታ ፣ በውስጣዊ አካል መቀጣጠል፣ በመብረቅ፣ በሌብነት ወይም በሌብነት ሙከራ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ወይም ጥፋት የካሣ ክፍያ መድን ይፈፅማል፡፡
ነገር ግን በተፈጥሮ ክስተቶች ምክንያት ማለትም በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአውሎ ንፋስ፣ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በመሳሰሉት ሳቢያ በተሽከርካሪው ላይ ለደረሰ ጉዳት ወይም ጥፋት በኢንሹራንሱ /መድን/ አይሸፈንም፡፡
የተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና ውል ላይ በሚደረግ ተጨማሪ ስምምነት መሠረት በአደጋው ጉዳት ለሚደርስባቸው ተሣፋሪዎች፣ በሽፍታ ሆን ተብሎ በተሽከርካሪው ላይ በሚደርስ ጉዳት፣ ከሀገር ድንበር ወሰኖች ውጭ በሚደረግ ጉዞ የሚደርሱ ጉዳቶችን የመድን ሽፋን እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል፡፡ የተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና ውል በተሽከርካሪው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም ጥፋት ተጨማሪ የሦስተኛ ወገን ኃላፊነትን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 799/2002 በተደነገገው መሠረት በሰው ላይ ለሚደርስ የአካል ጉዳት ወይም ሞት እና በንብረት ላይ ለሚደርስ ውድመት ካሳ ይከፍላል፡፡
የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ በኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ በ2002 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የወጣው አዋጅ ቁጥር 799/2002 እንደሆነ አቢሲኒያ ሎው (Abyssinia Law) ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም