የመሬት መንቀጥቀጥ /ርዕደ መሬት/ አደገኛ ከሆኑት የተፈጥሮ አደጋዎች ውስጥ አንዱ ነው። በሚሊየኖች የሚቆጠር እድሜ ያስቆጠሩት እነዚህ ከመሬት ንዝረት ጋር የተገናኙ ክስተቶች የመሬትን መልክዓ ምድር መልክ አስይዘዋል፤ በአንፃሩ ደግሞ ተመራማሪዎችን እና የተቀረውን ዓለም በፍርሃት፣ ሽብር እና ጭንቀት ውስጥ ያስገቡ ናቸው።
የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች ታሪክ የተመሠረተው ከተፃፉ ምንጮች፣ ከጅኦሎጂያዊ አፈጣጠር፣ ከሰው ልጅ ስልጣኔዎች የተወሰዱ ቅሬቶችን በማገናኘት ከሚደረግ ጥልቅ ጥናት የተወለደ ነው። ይህን መሰሉ ጥናት የመሬትን የቀደመ ታሪክ በተመለከተ እውቀት ይሰጠናል።
ጥንታዊ ስልጣኔዎች ሕንፃዎችን ወደ ትቢያ የለወጡ እና ማህበረሰብን ያጠፉ እጅግ አደገኛ የመሬት መናወጦችን ሰንደው ለትውልድ አስተላልፈዋል። ቀደምት በመሆን ከተመዘገቡት ርዕደ መሬቶች መሀል በ1823 ቅ.ዓ በቻይና የደረሰው ርዕደ መሬት ተጠቃሽ መሆኑን የብሪታኒካ መረጃ ያሳያል።
ስለዘመናዊው የመሬት ንዝረት ጥናት ደግሞ የሳይንስ መፈጠር የተደራጀ ግንዛቤ አስገኝቷል። በ1920ዎቹ ላይ ደግሞ የመሬትን የንዝረት እንቅስቃሴ የሚለካ የሬክተር ስኬል በስራ ላይ ውሏል። ይህም ስለ መሬት እንቅስቃሴ እና ባህሪ በማጥናት ተመራማሪዎች የመሬት ንዝረት ማእከሎችን እንዲያመላክቱ አስችሏል። እንዲሁም በታሪክ የተመዘገቡ ክስተቶችን የንዝረት መጠን መገመት እንዲችሉ አድርጓል።
ታሪካዊ ርዕደ መሬቶች
የርዕደ መሬቶች ታሪክ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ላይ ሁለንተናዊ ተፅእኖ ያሳደሩ በርካታ ክስተቶች ወደ ተሰነዱባቸው የጥንት ታሪክ ማስረጃዎች ይወስደናል። በጥንት ታሪክ ውስጥ ከታወቁት መካከል ፖምፔይ እና ሄርኩላኒየም የተባሉ ከተሞች 71 ዓ.ም ላይ ቬሱቪየስ ተራራ ላይ በፈነዳው እሳተ ጎሞራ ከመውደማቸው በፊት በርዕደ መሬት ታሪክ ውስጥ እጅግ ከታወቁ ክስተቶች አንዱን ተጋፍጠው ነበር። ይህ አውዳሚ የመሬት መናወጥ እነዚህን ከተሞች በአመድ እና በትቢያ ከምር አዳፍኖ እንደቀበራቸው ተፅፏል። የመሬት መንቀጥቀጡን ተከትሎ የተከሰተው የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ ደግሞ የእሳት ቃጠሎ እንዲስፋፋ እና ለአያሌ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኖ ከተሞቹን ወደ አመድነት ቀይሯቸዋል።
ከጥንታዊዎቹ እና እጅግ አውዳሚ ከተባለላቸው አብነት ለመጠቆም ያህል በ107 ዓ.ም የዛሬዋን ቱርክ የመታውን የአንፆኪያ የመሬት መንቀጥቀጥ እናገኛለን። በግምት ከ260 ሺህ በላይ ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኖ ነበር። ሌላው በ357 ዓ.ም በሮም የተከሰተው አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲሆን ከፊሉን የከተማዋን ገፅታ ወደ ትቢያነት የለወጠ ነበር።
በ1144 ዓ.ም ሲሲሊን የመታውን እናውሳው፤ የካታኒያ ርዕደ መሬት ይሉታል፤ ካታኒያን እና ራጉሳ የተባሉትን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን አውድሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወትም ቀጥፏል። በ1659 ዓ.ም የፖርቱጋል መዲና የሊዝበን ከተማን የመታውና ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ የሚገመት ሕይወት አጥፍቶ ያለፈው ክስተት ባውዳሚነቱ በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።
የአልጀሪያዋን መዲና አልጀርስን እንዳልነበረች አፈራርሶ ወደ 20 ሺህ አልጀሪያውያንን የበላው የመሬት መናወጥም የተከሰተው በ1708 ዓ.ም ነበር።
በ1804 ዓ.ም የቬንዝዌላ መዲና ካራካስ ለከተማዋ ውድመት እና ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆን ህይወት መቀጠፍ ምክንያት በሆነ ከባድ ርዕደ መሬት ተመትታ እንደነበር ሂስትሪ ዶት ኮም ያስረዳል። በወቅቱ የተከሰተው አደጋ ከስፔን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት በአርበኛ ሲሞን ቦሊቫር ይመራ የነበረውን የትግል ሂደት ሕዝባዊ ድጋፍ እስከማሳጣት የደረሰ ውጤት ነበረው።
ትግሉ ግስጋሴ ላይ ባለበት ወቅት አደጋው ሲከሰት ሕዝቡ ሃይማኖታዊ ትርጉም በመስጠት የስፔንን መንግሥት መታገል የፈጣሪ ቁጣ እንዳስከተለ ተደርጎ ፕሮፓጋንዳ እንዲሰራጭ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበር የቬንዝዌላ ታሪክ ያሳያል።
በርዕደ መሬት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው ክስተት በሬክተር ስኬል 9.5 የተለካው በ1952 ዓ.ም በቺሊ የደረሰው አደጋ ነበር። ከ5 ሺህ በላይ ሕዝብ ጨርሷል። አያሌ ንብረትም አውድሟል።
በታሪክ ውስጥ በገዳይነቱ ወደር ያልተገኘለት ርዕደ መሬት ደግሞ የተመዘገበው በ1962 ዓ.ም ላይ ነበር። ይህም የተከሰተው በደቡብ እስያ ነበር። እስከ 240 ሺህ የሚገመት የሰው ሕይወት የወደመበት ርዕደ መሬት ነበር። ይህን ተከትሎም በ2013 ዓ.ም በቺሊ የደረሰው ወደ 225 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን የቀጠፈ ክስተት ታይቷል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሳንፍራንሲስኮን ያወደመው የ1898 ዓ.ም ርዕደ መሬት በታሪክ ከተመዘገቡ እውቅ ክስተቶች መካከል አንዱ ሁኖ በታሪክ ይወሳል። የንዝረት መጠኑ በሬክተር ስኬል 7.9 ይለካ ነበር። ወደ 3 ሺህ ውድመቶች እና በመላ ከተማዋ ከባድ ቃጠሎን ፈጥሮ እንደነበር ተዘግቧል።
ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ በደቡብ ካሮሊና ግዛት፣ ቻርልስቶን ከተማ በ1878 ዓ.ም ከ6.9 እስከ 7.3 ሬክተር የሚለካ ርዕደ መሬት ደርሶ ከባድ ውድመት ከማስከተሉም በላይ ንዝረቱ እስከ ቦስተን፣ ችካጎ እና ኩባ ተሰምቶ እንደነበር የአሜሪካ የርዕደ መሬት ጥናት ማእከል ያወሳል።
የ1898ቱ የሳንፍራንሲስኮው ክሰተት በርዕደ መሬት ሳይንስ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር በማድረግ ረገድ እመርታ አስገኝቷል። በ1956 ዓ.ም በአላስካ የደረሰው ዘግናኝ አደጋ ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥን በመቋቋም ረገድ የመዋቅራዊ ንድፍ የማዘመንን እድገት አስገኝቶ ነበር። ሁለቱም በአሜሪካ የተከሰቱት ርዕደ መሬቶች አደጋዎችን በሚጋረጡብን ጊዜ የዝግጁነትን እና ውጤታማ ምላሽ የመስጠትን አስፈላጊነት ያስገነዘቡ ነበሩ።
የ1996 ዓ.ም የሕንድ ውቅያኖሱ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሱናሜ ምድራችን ካጋጠሟት አይረሴ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች ተርታ ይጠቀሳሉ። ከ9.1-9.3 ሬክተር የሚለካው የመሬት መናወጥ ለበርካታ ሀገራት ከባባድ ውድመቶችን ያስከተለ እና እስከ 227 ሺህ 898 የሚደርስ ሞት ተመዝግቦበታል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን 2002 ዓ.ም በሔይቲ የተከሰተው እጅግ ዘግናኝ የርዕደ መሬት አደጋ ካየነው ትልቁ ነው። በሬክተር ስኬል 7.5 የሚለካው የመሬት መንቀጥቀጥ 316 ሺህ ለሚደርሱ ሔቲያውያን ሞት እንዲሁም ወሳኝ ለሆኑ መሰረተ ልማቶች ውድመት ምክንያት ሆኖ ያለፈ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት የሚደርስባት ጃፓን ደግሞ በ2003 ዓ.ም ላይ የደረሰባት ቶሆኩ የተባለው ርዕደ መሬት በታሪክ ውስጥ በአክሳሪነቱ ወደር ያልተገኘለት፣ ጃፓንን 360 ቢሊየን ዶላር ለሚገመት ውድመት የዳረገ አደጋ ነበር። በሬክተር ስኬል 9.0 የሚለካው የመሬት መንቀጥቀጥ እጅግ አደገኛ ሱናሜ ከማስነሳቱም በላይ በፉክሹማ የኃይል ማመንጫ ላይ የኒኩሌር አደጋ አስከትሎ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
የመሬት መንቀጥቀጥ ሁሌም የማያጣት ጃፓን ታዲያ ያገጠሟት ፈተናዎች ለመጪው ጊዜ የተሻለ ዝግጅት እንዲኖራት አድርገዋታል። የሕንፃ ምህንድስናውን በማዘመን ለመሬት መንቀጥቀጥ የማይበገሩ ሕንፃዎችን ገንብታለች። በመሆኑም አሁን ጃፓን በመሬት መንቀጥቀጥ የሚፈርስ ሕንፃ የለም ለማለት እስከሚያስደፍር ዘምናለች።
በተጨማሪም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በቱርክ የተከሰተው ከ8.0 ሬክተር በላይ የሚለካው ርዕደ መሬት ያስከተለው ውድመት ሌላኛው ነው። በአስር ሺዎች የሚገመት ሕይወት በመቅጠፍ እና ከ100 ሺህ በላይ ቤቶችን በማፍረስ ቱርክን አስደንግጧል። የተለያዩ ከተሞቿን እያፈራረቀ በመምታት ዓለምን አስደንግጧል። ይህም አደጋ ቱርክ የሕንፃ አሰራር አቋሟን እንድትፈትሽ ያደረጋት ነበር።
… ይቀጥላል
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም