የትውልድ ተስፋ

0
144

የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 36 ንኡስ ቁጥር አንድ  “ሁሉም ሕፃናት በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካላቸው ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔ እና ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነጻ የመሆን መብቶች አሏቸው” በማለት አስፍሯል።

ይሁን እንጅ በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም እጦት ጥቁር ጠባሳ ከጣለባቸው ማሕበራዊ ተቋማት መካከል የትምህርት ዘርፉ አንዱ ነው። ይህን ተከትሎም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ የነገ ሀገር ተረካቢዎች  ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ ሆነው መማር እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ ቢሰፍርም ዛሬ ይህ መብት ተነፍጓቸው ከቤታቸው የዋሉት በርካቶች መሆናቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።

በችግሩ ውስጥ ካሉ የክልሉ ዞኖች አንዱ ሰሜን ሸዋ ነው፡፡ የዞኑ ትምህር መምሪያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም በጦርነቱ ሳቢያ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ቀለም የሚቀስሙባቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች በተለያዬ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል ጉዳትን አስተናግደዋል። ብዙዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን ተከትሎም በተለይ ሴት ታዳጊዎች ያለዕድሜ ጋብቻ እና  አስገድዶ መደፈር ተፈጽሞባቸዋል፡፡    ለተለያዩ ጾታዊ ትንኮሳዎች እንዲሁም ለስደት ሰለባ እስከመሆንም ደርሰዋል።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ  አቶ ፀጋዬ እንግዳወርቅ እንደሚሉት  በዘርፉ ላይ የተጋረጠው ፈተና ተሻጋሪ አስተሳሰብ ያለውና ሀገሪቱን በተሻለ ቁመና መረከብ የሚችል ትውልድ የመፍጠር ሂደቱን እያደናቀፈ ነው፡፡ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ከተማሪዎች ምዝገባ ዝግጅት ጀምሮ ያለው አጠቃላይ አፈጻጸም  አጥጋቢ የሚባል አይደለም።

ኃላፊው ለዚህም ማሳያዎችን አንስተዋል፤  በዞኑ ባሉት 1ሺህ 36 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በተያዘው የትምህርት ዘመን 98 ሺህ 346 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ እስከ  ትምህርት ዘመኑ  አጋማሽ በነበረው የተግባር ምዕራፍ ምዝገባ የጀመሩት ትምህርት ቤቶች 908 ናቸው።  በነዚህ ቅድመ መደበኛ ትምህር ቤቶች የተመዘገቡትም 61 ሺህ 487 ተማሪዎች  /62 ነጥብ 5 በመቶ/ ናቸው፡፡

ከተመዘገቡት መካከልም ትምህርት መከታተል የጀመሩት  43 ሺህ 169 ተማሪዎች እንዲሁም ማስተማር የጀመሩ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 711 ብቻ ናቸው።  13  ወረዳዎች የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ምዝገባ አስጀምረዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ መካከለኛ እና ዝቅተኛ የአፈጻጸም ደረጃ ያላቸው ናቸው።

በሌላ በኩል ዞኑ ካሉት 1 ሺህ 19 አንደኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች መካከል  የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመር የተንቀሳቀሱት  898  ናቸው። በትምርት ዘመኑ መባቻ 378 ሺህ 34 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ 175 ሺህ 535/ 46 ነጥብ 43 በመቶ/ ተማሪዎችን ብቻ ነው መመዝገብ የተቻለው።

በዞኑ ካሉት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል መማር ማስተማር  የጀመሩት 711 ሲሆኑ ከተመዘገቡት መካከል ደግሞ በትምህርት ገበታቸው ላይ የተገኙት 128 ሺህ 860 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን አቶ ፀጋዬ አብራርተዋል። በአንደኛ ደረጃ ይመዘገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ 6 ሺህ 284  የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች መካከል የተመዘገቡት 1 ሺህ 595 መሆኑንም ነው የጠቀሱት። በዞኑ ሁሉንም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ  ማስጀመር የቻሉትም 12 ወረዳዎች ብቻ ናቸው።

ኃላፊው እንዳሉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህት ቤቶች አፈጻጸምም ተመሳሳይ  ነው።  መመዝገብ ከነበረባቸው  95 ሺህ 36  ተማሪዎች ውስጥ 30 ሺህ 888 ተማሪዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት። ማስተማር በጀመሩ  53 ትምህትርት ቤቶች ደግሞ 28 ሺህ 983   ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረዋል። በ18 ወረዳዎች የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ማስጀመር ችለዋል። ነገር ግን 66 ሺህ 53 ተማሪዎች በዚህ ዓመት መማር እያለባቸው ከትምህርት ተነጥለዋል መባሉ በዘርፉ ላይ ያንዣበበው አደጋ የከፋ ለመሆኑ ማሳያ ነው።

በአጠቃላይ በዞኑ ባሉ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች 571 ሺህ 416  ተማሪዎች ለመመዝገብ ቢታቀድም  የተመዘገቡት ግን 267 ሺህ 910 ተማሪዎች/ 47 በመቶ/ ብቻ ናቸው፡፡   ከነዚህ መካከል ደግሞ ትምህርት የጀመሩት 201 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

መምሪያ ኃላፊው አቶ ጸጋዬ እንግዳወርቅ እንዳሉት ለመማር ማስተማሩ ተግባራዊ አለመሆን በጦርነቱ ምክንያት መምህራን ወደ ትምህርት ቤት አቅንተው ማስተማር አለመቻላቸው፣ ወላጆች  ልጆቻቸውን አምነው ወደ ትምህርት ቤቶች አለመላካቸው፣  የታዳጊዎች የመማር ፍላጎት  መቀነስ፣ ወደ ትምህርት ቤት ያቀኑትም ቢሆኑ  በሚፈጠር የሰላም መደፍረስ  ምክንያት ተረጋግተው መማር አለመቻላቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡  “ሕጻናት ዛሬ ላይ በትምህርት ተኮትኩተው ካላደጉ እድገት አይታሰብም ” ያሉት አቶ ጸጋዬ፤ ትምህርት እና ፖለቲካ መሥመራቸው ለየቅል በመሆኑ በነዚህ ተቋማት ላይ የሚደርስ ጥቃት ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል።

እንደ መምሪያ የተስተጓጎለውን የትምህርት ሂደት ለማስተካከል የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ኃላፊው አንስተዋል፡፡ በዚህም አሁን ላይ መጠነኛ ውጤት መመዝገቡን ነግረውናል። በተለይ በሁለተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ዘመቻ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ችግሩ አሁንም ሙሉ በሙሉ ባለመወገዱ የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠይቀዋል። በተለይ ወላጆች በአንድ በኩል አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የጎላ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ችግሩ ጎልቶ ከታየባቸው አካባቢዎች መካከል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ተጠቃሽ ነው። በወረዳው በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ተነጥለው ስድስት ወራትን አስቆጥረዋል። በትምህርት ቤቶች ላይም በተለያዬ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል ጉዳት መድረሱን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዞኑ በአረርቲ ከተማ በኵር በስልክ ያነጋገረችው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በትምህርቱ ጠንክሮ የተሻለ ሀገራዊ አበርክቶ እንዲኖረው ራእይ ወጥኗል። ይህንኑ ለማሳካትም አቅሙ በፈቀደ መጠን ጥረት እያደረገ እንደሆነ ነው የነገረን። ይህ የብዙ ተማሪዎች ፍላጎት መሆኑንም ጠቁሟል። አስተያየቱን የሰጠን ተማሪ አሁን በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም የጸጥታ ችግር በማንኛውም ጊዜ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩና በየእለቱ የግጭት ወሬ በመስማቱ ምክንያት ሙሉ ትኩረቱን ትምህርት ላይ ለማድረግ መቸገሩን ገልጾልናል።

የዛሬ ተማሪዎች የነገዋ የኢትዮጵያ ነጸብራቅ መሆናቸውን የሚናገረው ተማሪው ሀገርን በተሻለ አቅም ሊረከብ የሚችል ትውልድ ለማፍራት ፍጹም ሰላም ሊሰፍን እንደሚገባ ጽኑ ፍላጎት አለው። ሁሉም የሚመለከተው አካል ለዚህ ተግባር መረባረብ እንዳለበትም ጠይቋል።።

(ደጀኔ በቀለ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here