ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ሕዝቡን ለምሬት ዳርጓል

0
201

የንግድ እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ እና ምጣኔ ሀብቱ የተሻለ እድገት እንዲያመጣ ነዳጅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ነገሮች ሁሉ እየዘመኑ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በነዳጅ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው የሁሉም ነገር መሠረት ሆኗል።

ልማትን ያለ ነዳጅ ለማከናወን እጅግ አስቸጋሪም ያደርገዋል። ነዳጅ በበቂ ሁኔታ ካልቀረበ እና የቀረበውም በትክክለኛው መንገድ ለተገልጋዩ ካልደረሰ ጦሱ የከፋ ነው። ሥራዎች ይቆማሉ። ይህም ዜጎች ሠርተው ለመኖር፣ ነግደው ለማትረፍ ቀርቶ በልተው ለማደርም ይቸገራሉ። ነዳጅ ለትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት መሠረት ለሆነው ግብርና ሳይቀር ዋና ግብዓት ሆኗል፤ ለዚህም ማሳያው አርሶ አደሩ የውኃ መሳቢያ ሞተር (ፓምፕ) ተጠቅሞ ለሚያለማው መስኖ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ያለ ነዳጅ የመስኖ ልማት ወደፊት አይራመድም።

የዚህን መሠረታዊ ምርት ግብይት እና ስርጭት ጤናማ ለማድረግ ታዲያ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። በአማራ ክልል በነዳጅ አቅርቦት፣ ሥርጭት እና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል። የፀጥታ አካላት፣ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች፣ የንግድ መምሪያ ባለሙያዎች፣ የታክሲ ማሕበራት ተወካዮች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል። በውይይቱም ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር እንደተስፋፋ በማንሳት ይህም ፈጣን መፍትሔ ይሻል ተብሏል። ማኅበረሰቡ ጭምር በንቃት በመሳተፍ ሕገ ወጥ ድርጊትን መከላከል እንዳለበት ነው የተብራራው።

በውይይቱ እንደተባለው ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ሕዝብን ያማረረ ወንጀል ነው። ይህም ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ ዜጎችን ለከፍ ችግር ዳርጓል፤ ወንጀሉን ለመከላከል ታዲያ ሁሉም ማኅበረሰብ ጥፋተኞችን ሲያይ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት መተባበር ይገባል።

ለአማራ ክልል የሚመደበው የነዳጅ ግብይት መጠን የክልሉን ስፋት እና ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት፣ በመንግሥት ተቋም ሥም ወደ ማደያዎች እየመጡ በጀሪካን ጭምር ለመቅዳት የሚጠይቁ ባለ ሁለት ጎማ ሞተር ሳይክሎች እና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች መበራከታቸው፣ ይህም ማደያው ላይ ትርምስ እየፈጠሩ መሆኑ፣ አርሶ አደሮችም በትክክለኛ መንገድ እና ለትክክለኛ ዓላማ ነዳጅ እንዲያገኙ አሠራር አለመቀመጡ፤ አርሶ አደሮችን ተከትለው ሕገ ወጥ ጀሪካን ይዘው በሚሰለፉ ሕገ ወጦች ላይ ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ይገባል፤ ነጃጅ የጫኑ ቦቴዎችን ለማሳለፍ በየመንገዱ የቆሙ የታጠቁ ኃይሎች ከመጠን በላይ ክፍያ መጠየቃቸው እና መሰል ችግሮች ተነስተዋል።

ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ለማስቆም የሚመለከተው አካል ፈጣን መፍትሔ መስጠት እንዳለበት ተወያዮቹ ጠይቀዋል። በየመንገዱ ሹፌሮች እየታገቱ ተሽከርካሪም እየተያዘ ሰው እና ንብረት ለማስለቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠየቃል። ይህን ችግር ለማስቆም ታዲያ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። ሕገ ወጥ ማደያዎች ሲገኙ ደግሞ የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ   የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ከንግድ ተቋማት፣ ከታክሲ ማሕበራት ተወካይ እና ከሌሎች ተቋማት ተወክለው በውይይቱ ላይ የተገኙ አካላትም የተለያዩ ሐሳቦችን አንስተዋል። ባራገፉት ነዳጅ ልክ ሳያስተናግዱ “አለቀ” ብለው የሚዘጉ ማደያዎች መኖራቸው፣ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እንደ ሰበብ በመቁጠር ነዳጅ በወቅቱ አለማምጣት እና የጫኑትን ነዳጅም የመሰወር ድርጊት መኖር፣ ተሽከርካሪዎች  ለማደያ ሠራተኞች ገንዘብ በመክፈል ያለ ወረፋ በመግባት መስተናገድ፣ የተቀዳው ነዳጅ በትክክል ሥራ ላይ  ስለ መዋሉ  ክትትሉ አናሳ መሆን፣ የነዳጅ ማደያዎች ከታሪፍ በላይ የመሸጥ ፍላጎት መኖር፣ የጸጥታ አካላት ሕገ ወጥ ነዳጅ የሚያዘዋውሩ ተሽከርካሪዎችን ይዞ ወደ ሕግ የማቅረብ ውስንነቶች፣ እየቀዱ ከመስመር የሚወጡ (ከአገልግሎት ውጪ መሆን) አሽከርካሪዎች መኖራቸው እና የቀዱትን ነዳጅ ለተፈለገው አገልግሎት አለማዋል በንግድ ተቋማት፣ በታክሲ ማሕበራት እና በሌሎችም ተወያዮች የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ናቸው።

በየመንገዱ በውኃ መያዣ ኘላስቲክ (በኃይላንድ) እየተሰፈረ በውድ ዋጋ የሚሸጥ ሕገ ወጥ ነዳጅም ለሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይቱ በማሳያነት ተነስቷል። የነዳጅ ማደያዎች ሕግን ተከትለው  እና የግብይት ሥርዓትን ጠብቀው ነዳጅን ቢያሰራጩ ኖሮ እነዚህ ችግሮች  እንደማይፈጠሩ ተናግረዋል።

በዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት ውስጥ የማደያዎችም ድርሻ እንዳለበት በመረዳት ነዳጅ ሲራገፍ ጀምሮ ለተጠቃሚው እስኪደርስ በጥብቅ መከታተል ተገቢ ነው። ተወያዮቹ  ከተሽከርካሪዎች የመቅዳት አቅም በላይ የሆነ ተጨማሪ በርሚል ጭነው የሚቀዱ፣ ሕግ ሊያስከብር ቆሞ ነገር ግን ብር እየተቀበለ መኪና እያስገባ ነዳጅ የሚያስቀዳ የጸጥታ አካል በተጨባጭ ማየታቸውንም በውይይቱ አንስተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ላይ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን በመከታተል ለሕግ የማቅረብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ማደያዎች ባር ኮድ (መለያ) ላልለጠፈ ባጃጅ ነዳጅ ከቀዱ የሕገ ወጥ ተባባሪ መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸውም ብለዋል። ከዚህ አካሄዳቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ያስጠነቀቁት ምክትል ኮማንደር ዋለልኝ ሁሉም የባጃጅ አሽከርካሪዎች የባጃጅ ባር ኮድ እንዲለጥፉ አሳስበዋል።

መምሪያ ኃላፊው እንዳሉት ሕጋዊ የሆኑ አሽከርካሪዎችን ብቻ ነዳጅ መስጠት፣ ሕገ ወጦችን ደግሞ ከማደያ ማስወጣት ግድ ይላል። ለሕዝብ አገልግሎት በመስጠት ሽፋን ነዳጅ ከቀዱ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ አልበው በመሸጥ ቁመው የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ላይም ክትትል በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን በትኩረት ይሠራል ብለዋል። በነዳጅ ሥርጭቱ ላይ የትኛውም የፀጥታ አካል በሕገ ወጥ መንገድ እጁን አስገብቶ ቢገኝ እና ተባባሪ ቢሆን እርምጃ እንደሚወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ሕገ ወጦችን እየተቆጣጠርን ነው ያሉት መምሪያ ኃላፊው ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ደግሞ የሕገ ወጥ ምንጮችን ከሥሩ ማድረቅ ተገቢ መሆኑን አክለዋል። ችግር ባለባቸው የነዳጅ ማደያዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እና ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን ተቋማቱም ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መልዕክት አስተላልፈዋል። የማደያ ሠራተኞችን አስገድዶ ነዳጅ የሚቀዳ የፀጥታ ኃይል ካለ እና ጥቆማ ከተሰጠ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈንታው ፈጠነ የነዳጅ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን ጠቁመው “ይልቁንም ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር መኖሩ ማኅበረሰቡን በእጅጉ ምሬት ውስጥ አስገብቶታል” ብለዋል። መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ በድጎማ የሚያቀርበውን ነዳጅ በአግባቡ ባለመጠቀም እና በመደበቅ እየተፈጠረ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ፈንታው ችግሮች መኖራቸውን አስታውሰው ችግሩን ለመፍታት ከውይይት ባለፈ የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለችግሮች መፍትሔ እየተሰጠ ነውም ብለዋል። ለአብነትም ከ250 ሺህ ሊትር በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ የተያዘ ነዳጅ መኖሩን ጠቅሰዋል። አንድ ሊትር ቤንዚል እስከ 650 ብር  በከተማዋ ይሸጥ እንደነበርም አስታውሰዋል። ይህም የሆነው የቀረበውን ነዳጅ ለታለመለት ዓላማ፣ በቁጠባ እና በተቀመጠው ስርዓት ማስተዳደር እና መምራት አለመቻል መሆኑን ገልፀዋል። ሕገ ወጦች በበርሚል፣ በጀሪካን፣ በሐይላንድ እና በጆንያ ሳይቀር ሌላ ዕቃ አስመስለው ሲንቀሳቀሱ እንደተያዙ ገልፀዋል።

አርሶ አደሮች ለመስኖ ሥራቸው ማግኘት የሚገባቸውን ነዳጅ ባለማግኘታቸው ምክንያት ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ጊዚያቸውን በማሳቸው ላይ ማሳለፋ ሲገባቸው በየቢሮው ሲንከራተቱ የዋሉበት ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ላይ ግን ከግብርና ቢሮ ጋር በመነጋገር ለችግሮቹ መፍትሔ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው አክለውም “በሕገ ወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ማደያዎችን እየለየን ነው፤  ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ሕገ ወጦችን እየዘጋን፣ ሕግን እና ሕዝብን አክብረው ከሚሠሩ ማደያዎች ጋር እንቀጥላለን” ነው ያሉት።

እንደ ክልል ከአቅርቦት አኳያ መሻሻሎች ቢታዩም  ጉድለቶች እንዳሉም ተናግረዋል። በተለይም መሠረታዊ ችግሩ የነዳጅ ማደያ ባለሀብቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው የሚፈጠሩ ችግሮች እንዳሉ አመላክተዋል።

ነዳጅ መንግሥት ባስቀመጠው ዋጋ  አለመሸጥ ዜጎችን ለከፋ ችግር ዳርጓል። ነዳጅን በሌሊት በድብቅ ለሌላ አካል አሳልፈው የሚሰጡ እና  በኃይል እንዲሁም በጉልበት የሚቀዱ አካላት እንዳሉም አመላክተዋል። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉት በክልሉ ያለውን የፀጥታ ችግር ታሳቢ አድርገው ገንዘብ ለማግኘት እጃቸውን ለማስገባት የሚሞክሩ መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ሕጋዊ ሆነው ሕዝብን የሚያገለግሉ ባጃጆች እና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ሁሉ ነዳጅን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር በሕገ ወጥ ሥራ የተሰማሩ እንዳሉ ደርሰንበታል ነው ያሉት።

ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች እና አውቶብሶች ሳይቀሩ የሕዝብ መጫኛ ወንበሮቻቸውን ነቅለው በትላልቅ በርሚሎች ሕገ ወጥ ነዳጅ በመጫን ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። በሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር የተጠመዱ ማደያዎች መገኘታቸውንም ገልጸዋል።

ችግሮቹን ለመፍታትም የነዳጅ ማደያ ባለሀብቶች፣ የተሽከርካሪ ማሕበራት፣ የፀጥታ አመራሮች ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሕግን  እና ሥርዓትን አክብረው እስካልሠሩ ድረስ በነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ እየተከሰተ ላለው የኑሮ ውድነት አባባሽ ሆኖ እንዳይቀጥል በፍጥነት መታረም እንዳለበት ተናግረዋል። ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተረባርቦ ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ለክልሉ ተደራቢ ችግር ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በሕዝብ ስም የክልሉን የነዳጅ ግብይት ድርሻ ጭነው እያመጡ በየጫካው እየተደበቁ የሚሸጡ የማደያ ባለቤቶችን ተከታትሎ ለመያዝ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ችግር በታየባቸው የነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ያነሱት ምክትል ኃላፊው ለአብነትም በሦስት የነዳጅ ማደያዎች ላይ ረዘም ላለ ወራት ከነዳጅ ትስስር እንዲወጡ መደረጉን ጠቁመዋል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። እነዚህን ማደያዎች ከነዳጅ ትሥሥር ሙሉ በሙሉ እስከማስወጣት የሚደርስ ቁርጠኛ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here